አዲስ አዳጊው ለገጣፎ ለገዳዲ አዲስ አሠልጣኝ ሲሾም ዋና አሠልጣኙ በምክትልነት እንዲሰሩ ውሳኔ አስተላልፏል።
በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ከፍተኛው የሊግ እርከን እየተሳተፈ የሚገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ እስካሁን 10 ጨዋታዎችን አከናውኖ በሊጉ የመክፈቻ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን ብቻ በመርታት በሁለቱ ነጥብ ተጋርቶ በ7ቱ ደግሞ ተሸንፎ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከውጤት ማጣት ጋር ተያይዞ ክለቡ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱን ወደ መቀመጫ ከተማው ጠርቶ ካነጋገረ በኋላ ሦስቱ ምክትሎች እንዲነሱ ማድረጉ ይታወሳል። አሁን ባገኘነው መረጃ መሰረት ደግሞ ክለቡ ዋና አሠልጣኙ ጥላሁን ተሾመ ወደ ምክትል ኃላፊነት ወርደው እንዲሰሩ በማዘዝ በቦታው አዲስ አሠልጣኝ መሾሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ የሆኑት አሸናፊ በቀለ ናቸው። ምንም እንኳን የወረቀት ስራዎች ባይገባደዱም አሠልጣኝ አሸናፊ ከክለቡ አመራሮች ጋር ከተስማሙ በኋላ ዛሬ ወደ ድሬዳዋ በመምጣት ከደቂቃዎች በፊት ከቡድኑ ተጫዋቾች ጋር ትውውቅ እንዳደረጉ ለማወቅ ተችሏል። አሠልጣኝ አሸናፊ በሀዲያ እና በጅማ አብረዋቸው የሰሩት እያሱ መርሐጽድቅን (ዶ/ር) በምክትልነት እንዳመጡና ከጥላሁን ተሾመ ጋር በጋራ እንደሚሰሩም ተመላክቷል።