የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 0-1 ወላይታ ድቻ

👉”በከፍተኛ ቁርጠኝነት እና በተራበ ፍላጎት በመጫወታችን ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክተናል” ፀጋዬ ኪዳነማርያም

👉”ሽንፈት ያጋጥማል ግን ሽንፈቱ አሳማኝ ሲሆን ነው አንተም የምትቀበለው” ዮርዳኖስ ዓባይ

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው…

ጠንካራ ጨዋታ ነበር። በመጀመሪያ ድሬዳዋ ከተማዎች የመጡበትን ነገር ማወቅ ያስፈልጋል። በሜዳቸው አንድም ጨዋታ አልተሸነፉም። በጣም ጥሩ የሆነ ብቃት ያለው ትልቅ እና የደጋፊውን ስሜት እያረካ የመጣ ክለብ ነው። በተለይ አጥቂዎቹን መከታተል ያስፈልገን ነበር። ምክንያቱም ለእነርሱ ትንሽ ቀዳዳ ሰጠህ ማለት አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። እኛም ይህንን ስለምናውቅ አጥቂዎቹ ከነበራቸው ኳሊቲ እንዲወጡ አድርገናል። በመጀመሪያ ደረጃ እግዚአብሔር ይመስገን። እዚህ መድረሳችን በጣም ጥሩ ነው። በእንቅስቃሴ በተለይ ከኳስ ውጪ ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ ነበርን። የኋላ አራቱ ተከላካዮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቁ ነበር። በተረፈ እልህ እና ከፍተኛ ፍላጎት የነበረበት ጨዋታ ነው ተጫዋቾቼ ላደረጉት ነገር ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው። ከጠንካራ ቡድን ሦስት ነጥብ በመውሰዳችን በጣም ደስ ብሎኛል። በተጨማሪም ስንታየሁ ወደ ግብ አግቢነት በመምጣቱ የበለጠ ደስ ብሎኛል።

በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ነጥብ ስለማሳካታቸው….

እኛ ጋር ያለው የሰው ኃይል የታወቀ ነው። አቅማችንን እናውቃለን። በአቅማችን ልክ ነው እንደየተጋጣሚያችን የምንጫወተው። ድሬዳዋዎች ትንሽ ክፍተት ከሰጠካቸው ይቀጡካል ፤ በተጨማሪም የአየር እና የቆሙ ኳሶች የሚያሸንፉ ናቸው። ይህ ደግሞ በደጋፊ እየታገዘ ስለሚመጣ እኛ መጀመሪያ ኳሱን ለመከልከል ነበር ያሰብነው። በአጠቃላይ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እና በተራበ ፍላጎት በመጫወታችን ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክተናል። ይህ ሦስት ነጥብ ደግሞ እዚህ ድረስ ተጉዘው ለደገፉን እና እዛው ሶዶ በፀሎት ከጎናችን ለሆኑት ደጋፊዎቻችን ብናበረክተው ደስ ይለኛል።

አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጨዋታው…

ጨዋታው በደንብ ማሸነፍ የምንችለው ጨዋታ ነበር። ግን አንዳንዴ ግድየለሽነት እና ግለኝነት አንዳንዴ ዋጋ ያስከፍላል። ከእረፍት በፊትም ኳሱን ይዘን ስንጫወት ነበር። እነርሱ አንድ ኳስ አገኙ ያንን አገቡ።

ከባለፉት ጨዋታዎች አንፃር ዛሬ ስላደረጉት እንቅስቃሴ….

ያው ድካም ይኖራል። በሁለት ሦስት ቀን መጫወት ድካም አለው። ከድካሙ ወጥተን ለቀጣዩ ጨዋታ ለመድረስ ጥሩ እረፍት እና በቂ ዝግጅት ነው የምናደርገው። ይህንን ሁሉ አድርገን ነው የማንጠብቀውን ነገር የምናየው። እንቅስቃሴው ጥሩ ነበር ፤ እንቅስቃሴው የተሻለ የሚሆነው ግን ጎል ስታገባ ነው። ማግባትም ማሸነፍም እንችል ነበር ፤ ግን አልሆነም።

በሜዳቸው ስላስተናገዱት የመጀመሪያ ሽንፈት…

ሽንፈት ያጋጥማል ግን ሽንፈቱ አሳማኝ ሲሆን ነው አንተም የምትቀበለው። እኔ እንደዛሬ የተናደድኩበት ጊዜ የለም። ምክንያቱም አይገባንም ነበር። ልፋታችን ነው ገደል የሚገባው። ግን ይሄ ያልፋል። አሁን ወደ አዳማው ጨዋታ ትኩረታችንን አድርገን ወደ መንገዳችን ለመግባት እንሞክራለን።