ከፍተኛ ሊግ | የ3ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

በቶማስ ቦጋለ እና ጫላ አቤ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ 11 ጨዋታዎችን አስተናግዶ ዘጠኙ በመሸናነፍ ሲጠናቀቁ ሻሸመኔ ከተማ ብቸኛው ተከታታይ ድል ያስመዘገበ ቡድን ሆኗል።

የ03:00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ በምድብ ‘ሀ’ ቀዳሚ ጨዋታ ዱራሜ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተገናኝተዋል። መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ 13ኛው ደቂቃ ላይ የንግድ ባንኩ ሀይከር ዱዋሮ ከተጋጣሚ ሳጥን አጠገብ ወደ ግብ በቀጥታ ሞክሮት ግብ ጠባቂው የመለሰው ኳስ የመጀመሪያው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር። 38ኛው ደቂቃ ላይ ባንኮች የተሻለ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ በቀኝ መስመር የነበረው ዓባይነህ ፊኖ ያቀበለውን ኳስ ሀይከር ዱዋሮ በግንባሩ ሲጨርፈው ያገኘው አቤል ማሙሽ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ኳሱ የግራውን ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ዱራሜዎች ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሲያገኙ ወንዱ ፍሬው ያደረገውን ያልታሰበ ሙከራ ግብ ጠባቂው መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ንግድ ባንኮች ተሻሽለው ሲቀርቡ በተደጋጋሚም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቀላሉ መድረስ ችለዋል። ይህ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶም 66ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። መነሻው ከቀኝ መስመር የሆነውን ኳስ የዱራሜው ተስፋሁን ተሾመ ለመመለስ ጥረት ሲያደርግ ኳሱ አቅጣጫ ቀይሮ በራሱ መረብ ላይ ሊያርፍ ችሏል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጅማ ላይ በምድብ ‘ለ’ የከምባታ ሺንሺቾ እና ጅንካ ከተማ ጨዋታ ያለግብ ሊጠናቀቅ ቢቃረብም 86ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ታደለ ጅንካ ከተማን የ1-0 አሸናፊ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ሆሳዕና ላይ የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በሆነው የኦሜድላ አና የገላን ከተማ ጨዋታ በሁለቱም በኩል ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴ በተደረገበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ያልነበረ ቢሆንም ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች ተመልክተናል።

በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ገላን ከተማዎች መጠነኛ የሆነ የጨዋታ ብልጫ ያሳዩ ሲሆን በግብ ሙከራም የተሻሉ ሆነዋል። በኦሜድላዎች በኩልም አልፎ አልፎ ያገኙትን ዕድል ለመጠቀም ሲጥሩ ታይተዋል። ጨዋታው በዚሁ ሁኔታ ቀጥሎ በ73ኛው ደቂቃ በገላን ግብ ጠባቂ እና በተከላካይ አለመግባባት የተገኘውን ኳስ ኦሜድላዎች በአጥቂያቸው ተመስገን መንገሻ ማስቆጠር ሲችሉ ግቧ የጨዋታው ብቸኛ ግብ በመሆኗ ኦሜድላ የሦስት ነጥብ ባለቤት መሆን ችሏል። ከግቧ በኋላም ገላን ከተማዎች ነጥብ ለመጋራት ተደጋጋሚ የሆነ የማጥቃት ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ማግኘት ተስኗቸው ጨዋታውን በሽንፈት ሊያጠናቅቁ ተገደዋል።

የ05:00 ጨዋታዎች

ረፋድ ላይ የምድብ ‘ሀ’ ሁለተኛ ጨዋታ በሰንዳፋ በኬ እና ቤንች ማጂ ቡና መካከል ተደርጓል። ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር የታየበት ሲሆን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ግን ቤንች ማጂዎች የተሻሉ ነበሩ። ያለማቋረጥ የማጥቃት ሽግግሮች እየታዩ በነበሩበት ሂደት 30ኛው ደቂቃ ላይ ጴጥሮስ ገዛኸኝ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ ቤንች ማጂን መሪ አድርጓል። በተረጋጋ የኳስ ቅብብል ወደ ፊት በመጠጋት የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት ሰንዳፋ በኬዎች በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራቸው 38ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ መሳይ ሰለሞን ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ውጪ አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ቤንች ማጂዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ጥቅጥቅ ብለው መጫወትን ሲመርጡ ሰንዳፋዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም የግብ ዕድል በመፍጠሩም በኩል እጅግ ተሻሽለው ቀርበዋል። በአምበላቸው ፍቃዱ እና ሳምሶን ሥዩም የግብ ሙከራ ሲያደርጉም 63ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የቤንች ማጂው ርጅብ ሚፍታ በትክክል ማቀበል ያልቻለውን ኳስ ያገኘው ማሙሽ ደበሮ በደካማ አጨራረስ የግብ ዕድሉን አባክኗል። ጨዋታውን በማረጋጋት በሚያገኙት ኳስ ፈጣን የማጥቃት ሂደት ሲከተሉ የነበሩት ቤንች ማጂዎች በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራ 71ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ አምበሉ ጌታሁን ገላዬ ከግራ መስመር በግሩም ሁኔታ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በፍጥነት ወደ ውጪ አስወጥቶ የማዕዘን ምት አድርጎታል። ራሱን ኳስ እሱባለው ሙሉጌታ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ሲያሻማ ሀሰን ሁሴን በግንባሩ በመግጨት የግብ ጠባቂውን እጅ በመጣስ ግብ አስቆጥሮ የክለቡን መሪነት አጠናክሯል። ሰንዳፋ በኬዎች ለባዶ ከመሸነፍ ያዳነች ግብ 84ኛው ደቂቃ ላይ በመሳይ ሰለሞን አስቆጥረው ጨዋታው በቤንች ማጂ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጅማ ላይ የተደረገው ሁለተኛ ጨዋታ እንደመጀመሪያው ሁሉ በ1-0 ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። በዚህም 38ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ጥሩነህ ያስቆጠራት ግብ ሻሸመኔ ከተማ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃንን አሸንፎ እንዲወጣ አስችላለች።

በምድብ ‘ሐ ‘የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ዳሞት ከተማን ከስልጤ ወራቤ አገናኝቷል። በስልጤ ወራቤ የደጋፊዎች ድባብ ደምቆ የጀመረው የመጀመሪያ አጋማሽ ፈጣን አጨዋወት የታየበት እና በተለይ የዳሞት ከተማ እንቅስቃሴ የተሻለ ሆኖ የተስተዋለበት አጋማሽ ነበር። ሆኖም ግን በሁለቱም በኩል ምንም ግብ ሳንመለከት ወደ እረፍት አቅንተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ስልጤ ወራቤዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ ይልቅ ተሽለው ቀርበዋል። በዚህም ጥሩ እንቅስቃሴ እና ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም የዳሞት ከተማው ተከላካይ ወርቁ አዲስ ባሳየው ድንቅ የሆነ የመከላከል አጨዋወት ወደግብነት እንዳይቀየር ማድረግ ችሎ ቆይቷል። ሆኖም መደበኛው ሰዓት ተጠናቆ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ስልጤ ወራቤዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት ሬደዋን ሙስጠፋ ወደ ግብ በመቀየር ቡድኑን አሸናፊ ማድረግ ችሏል።

የ08:00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ ቀዝቃዛ በነበረው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እና ጋሞ ጨንቻ የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ብዙም የጠሩ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ብርቱ ፉክክር ሲያስተናግድ በአጋማሹ የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራ 61ኛው ደቂቃ ላይ ተደርጓል ፤ በአቃቂ የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ የማይጠፋው በኃይሉ ወገኔ ከግራ መስመር ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው መልሶበታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በቀኝ መስመር አማኑኤል ተፈራ ላይ በተሰራ ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ንጋቱ ፀጋዬ አስደናቂ በሆነ ብቃት አስቆጥሮ ጋሞዎችን መሪ ማድረግ ችሏል።

የማጥቃት ሚዛናቸውን ወደ ግራው የሜዳ ክፍል ያመዘኑት አቃቂዎች 75ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆነዋል። ከግራ መስመር በኃይሉ ወገኔ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ተመስገን ኤርሚያስ በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል። መደበኛው ደቂቃ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩ የጋሞ ጨንቻው አማኑኤል ተፈራ ከረጅም ርቀት አክርሮ በመምታት ግሩም ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና መልሶበታል። ጨዋታውም 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በምድብ ‘ለ’ ጅማ ላይ የተገናኙት እንጅባራ ከተማ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጨዋታቸውን ያለ ግብ አጠናቀዋል።

የዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ የሆነው የየካ ክ/ከተማ እና የሮቤ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ሮቤ ከተማን ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ ለሽንፈት ዳርጓታል። በመጀመሪያው አጋማሽ በሮቤ ከተማ በኩል በርካታ የሚባሉ ግልፅ የግብ ሙከራዎችን ያባከኑ ሲሆን በየካ ክ/ከተማ በኩል አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት የግብ ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውለዋል። መደበኛው 45 ደቂቃ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ብስራት በቀለ ለየካ ግሩም ግብ አስቆጥሯል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሮቤ ከተማ አቻ ለመሆን የካ ደግሞ ውጤቱን ለማስጠበቅ የሚደረግ እንቅስቃሴ ያየንበት ሲሆን በጨዋታው ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ተመልክተናል። ሁለተኛው አጋማሽም ምንም ግብ ሳይገባ የካ ክ/ከተማ በጠባብ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል። በጨዋታው የግቧ ባለቤት የሆነው ብስራት በቀለ የየካ ክፍለ ከተማን የፊት መስመር በማገዝ ጥሩ እንቅስቃሴ አሳይቷል። በሮቤ ከተማ በኩል የመሀል ሜዳ ተጫዋቹ ሶፊያን ገለቱ በረጃጅም ኳስ ጥሩ ዕድል ሲፈጥር ታይቷል።

የ10:00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ ቡታጅራ ከተማ እና አዲስ ከተማ ክፍለከተማን ያገናኘው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ብዙም ፉክክር ባልነበረበት የመጀመሪያ አጋማሽ አንድ ብቻ የጠራ የግብ አጋጣሚ ተፈጥሮበታል። 31ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ ከተማው ጳውሎስ ከንቲባ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አህመድ አብዱ በአንድ ንክኪ ያልታሰበ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ትኩረቱን ኳሱ ላይ አድርጎ የነበረው ግብ ጠባቂው ምንተስኖት የግሌ አስወጥቶበታል። ቡታጅራዎች ክንዴ አብቹ ከረጅም ርቀት ካደረጋቸው ሁለት ፈታኝ ያልሆኑ ሙከራዎች ውጪ ተጨማሪ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረዋል። ከዕረፍት መልስ አዲስ ከተማዎች ተሻሽለው ሲቀርቡ በፈጣን የማጥቃት ሽግግርም 48ኛው ደቂቃ ላይ በከተማ ገረመው አማካኝነት ማስቆጠር ችለዋል።

ቡታጅራዎች በጥሩ ቅብብል ከራሳቸው የግብ ክልል መውጣት ቢችሉም የመጨረሻ ኳሳቸው ግን እጅግ ደካማ ነበር። ይባስ ብሎም ትኩረታቸውን በተነጠቁበት አጋጣሚ 68ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። አሸናፊ በቀለ ከረጅም ርቀት በኃይል የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው መልሶበታል። በመጨረሻ ደቂቃዎች ጨዋታውን በማረጋጋት ነጥብ ይዘው ለመውጣት የሞከሩት አዲስ ከተማዎች ተሳክቶላቸው ጨዋታውን 1-0 በሆነ ውጤት በመርታት ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

የምድብ ‘ለ’ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማን እና ጉለሌ ክፍለ ከተማን አገናኝቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ 27ኛ ደቂቃ ላይ በመሉቀን ታሪኩ ግብ ቀዳሚ መሆን የቻሉት አዲስ አበባ ከተማዎች ከዕረፍት መልስ በዘርዓይ ገብረሥላሴ ሁለት እንዲሁም በኤርሚያስ ኃይሉ አንድ ግብ አክለው ጨዋታውን 4-0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።