የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 1-1 ባህር ዳር ከተማ

👉 “ውጤቱ እንደ ጥረታችን ተጋርተን መውጣታችን የሚያስከፋ አይደለም ፤ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ” ሥዩም ከበደ

👉”ውጤቱን ተነጥቀናል ፤ በቃ! ተነጥቀናል ነው የምለው። የተመለከተ ይፍረደው!” ደግአረገ ይግዛው

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው …

አጠቃላይ ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ እኛ ጋር ብዙ ጊዜ እየተቸገርን ያለነው በመጀመሪያው አስር እና አስራ አምስት ደቂቃ ቀድመን የምናስተናግዳቸው ጎሎች ናቸው ፤ ብዙ ነገራችንን ሰልቦናል። ዛሬም ያንን ነገር ነው በብዛት አጠንክረን የሰራነው የተነጋገርነው እንደጠበቅነውም አሁንም በጊዜ እንኳንም ባይሆን በፊት አምስት ደቂቃ ሁለት ደቂቃ የነበረው አስራ አራተኛ ደቂቃ ላይ ነው የገባብን ፤ ግን ከእዛ ተነስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ቡድኔ ጥሩ ነገር ተንቀሳቅሷል በተለይ ከዕረፍት በኋላ። ከዕረፍት በኋላ ውጤት ለማግኘት ያደረግነው ተጋድሎ በአጠቃላይ ያደረግነው ቅያሪ በጣም አሪፍ ነገር ነው። በአጠቃላይ ውጤቱ እንደ ጥረታችን ተጋርተን መውጣታችን የሚያስከፋ አይደለም ፤ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ስለ ፊሊፕ ኦቮኖ ስህተት…

መቼም እግር ኳስ በስህተት የታጀበ ነው፡፡ የሚያናድህ ነገር ደግሞ ትንሽም የሚያበሳጨው በረኛን ጥሩ ነው ብዬ የማስበው እስከ አሁን ግን የህፃናት ልጅ ስህተት ነው የተሳሳተው። ያ ነው ዋጋ ያስከፈለን። ግን በጥረታችን ውጤቱን አግኝተነዋል። ጥሩ ነው አጠቃላይ ለተጫዋቾቼ ለነበራችው ሞቲቬሽን ቤንች ላይ ላሉት ፣ አውት ኦፍ ቤንች ላይ ያሉት የነበረው ህብረት ልነግርህ አልችልም። ይሄን ሳላመሰግን አላልፍም። ከሁሉም በላይ ደግሞ የቦርድ አባሎች ከጨዋታ በፊት ለሚያደርጉልን መነቃቃት እጅግ እጅግ ጥሩ ነው፡፡ ለቀጣይ እንቅስቃሴያቸን ምቾት ነው የሚሰጠን፡፡

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው ጥሩ ነው ፤ ጠንካራ ጨዋታ ነው። እነሱ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ያደረጉት ፤ እኛ ደግሞ ወደ መሪነት ለመሄድ ያደረግነው ጨዋታ ነው። ሆኖም ግን ያው ተጫዋቾቻችን በ90 ደቂቃ ውስጥ የሚችሉትን አድርገዋል። ምናልባት ሚገልጸው ከሆነ ስሜቴን ውጤቱን ተነጥቀናል።

ሙሉ ነጥብ ስላላሳኩበት ምክንያት…

ውጤቱን ተነጥቀናል ፤ በቃ! ተነጥቀናል ነው የምለው። የተመለከተ ይፍረደው!

ተጨማሪ ግብ ስላላስቆጠሩበት ምክንያት…

ያው እንግዲህ እንደሚታየው ጨዋታው ጠንካራ ጨዋታ ነው። ተጫዋቾቻችን ስሜት ውስጥ ሆነው ነው እየተጫወቱ ያሉት ፤ በእያንዳንዷ ደቂቃ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ትንሽ የሚፈትኑ ነበሩ። የግብ ዕድሎችንም አግኝተናል ይበልጥ ጉጉ ከመሆን አኳያ አባክነናል። የሚያጋጥም ነው ቀጣይም ሠርንባቸው የምንመጣ ነው የሚሆነው።

በመጨረሻ ደቂቃ ስላስተናገዱት ግብ…

በመጨረሻ ደቂቃ ያስናገድነው ግብ ተገቢ አይደለም። ዳኛው አምስት ደቂቃ ጨምሩ አምስት ደቂቃ የሚያስጨምር ምክንያት አልነበረም። አምስቱ ደቂቃ ካለቀ በኋላ ስምንተኛ ደቂቃ ላይ ነው ግብ ያስተናገድነውና ይሄ በእውነት ስሜት ይጎዳል። በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ እያስተናገድነው ያለነው ጫና በጣም ከባድ ነውና እኔ አሁን ‘ለማን አቤት ይባላል?’ ነው የምለው። ከባድ ነገር ነው ብትናገርም አንተ ጋር ነው ሁሉም ነገር ተጫዋቾቹ ምን ያህል ስሜታቸው እንደተጎዳ እየታየ ነው። ከእጃችን የገባ ነጥብ ነው የተነጠቅነው።