ሪፖርት | ኃይቆቹ ከናፈቃቸው ድል ጋር ተገናኝተዋል

የዓሊ ሱሌይማን ብቸኛ ጎል ሀዋሳ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ድል እንዲቀዳጅ አስችላለች።

በ11ኛ ሳምንት በመቻል ሁለት ለምንም የተረቱ ሀዋሳ ከተማዎች ላውረንስ ላርቴ ፣ ሰዒድ ሀሰን ፣ በቃሉ ገነነ ፣ መድሃኔ ብርሃኔ እና ተባረክ ሄፋሞን አሳርፈው በረከት ሳሙኤል ፣ አቤኔዘር ኦቴ ፣ ዳዊት ታደሠ ፣ ኢዮብ ዓለማየሁ እና ኤፍሬም አሻሞን በአሰላለፋቸው አካተው ጨዋታውን ሲጀምሩ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው አቤል ሀብታሙ ፣ ስንታየሁ ወለጬ እና ያሬድ የማነህን በሔኖክ አየለ፣ ሙሴ ከቤላ እና ታፈሰ ሰርካ ምትክ አስገብተው ጨዋታውን ቀርበዋል።

Post1 (16)

የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ሲያስመለክት የነበረ ሲሆን ከጅምሩም በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች ሲደረጉበት ነበር። በ3ኛው ደቂቃ ወንድማገኝ ኃይሉ በመስመሮች መካከል በመገኘት የላከውን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ዓሊ ሱሌይማ አግኝቶት በግብ ዘቡ ፍቅሩ ወዴሳ አናት ልኮ ግብ ሊያደርገው ቢጥርም ወደ ላይ የሰቀሰቀው ምት በዝቶ ዒላማውን ስቶ ባይወጣበት በጊዜ መሪ ሊገኝ ነበር። ከሰሞኑን አቋማቸው በተሻለ ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ጥሩ የነበሩት ሀዋሳዎች በ15 እና 19ኛው ደቂቃ የቆመ ኳስን መነሻ ባደረጉ ተከታታይ አጋጣሚዎች ጥቃት ሰንዝረዋል። በቅድሚያ በረከት ወደ ግራ ካደላ ቦታ ያገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ሲመታው በመቀጠል ደግሞ ከተቃራኒ አቅጣጫ የተሻማውን ኳስ አቤኔዘር ኦቴ ከግብ ጋር ሊያገናኘው ነበር።

ጫናዎች የበዛባቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ20ኛው ደቂቃ በራሳቸው በኩል የመጀመሪያ ሙከራቸውን አድርገዋል። በዚህም የመሐል አጥቂው አቤል ሀብታሙ በአማካይ እና ተከላካይ መካከል በመገኘት አክርሮ የመታው ኳስ ከረጅሙ ግብ ጠባቂ መሐመድ ሙንታሪ ጀርባ የሚገኘው መረብ ላይ ማረፍ አልቻለም። ሙንታሪ ያወጣው ኳስ ደግሞ ከመዓዘን ሲሻማ ኢብራሂም ከድር በግንባሩ ለመጠቀም ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። በ22ኛው ደቂቃ ግን የተሻለ ሲንቀሳቀሱ በነበሩት ሀዋሳዎች ግብ አስተናግደው መመራት ጀምረዋል። በዚህም ዓሊ ሱሌይማን ሰለሞን ወዴሳ በረጅሙ የመታውን ኳስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ለመጠቀም በመጣር ግብ ክልሉን ለቆ የወጣውን ግብ ጠባቂ ፍቅሩ በመቅደም ኳስ እና መረብ አገናኝቷል።

Post3 (15)

ሀዋሳ ከተማዎች በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎችም መሪነታቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመያዝ ሲንቀሳቀሱ የነበረ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪኮችም ጨዋታው ሙሉ ለሙሉ ከቁጥጥራቸው ሳይወጣ ለመገልበጥ መጣጣራቸውን ይዘዋል። ኤልፓዎች ገና አጋማሹ ሳይገባደድ የማጥቃት ኃይላቸውን ለማደስ የተጫዋች ለውጥ አድርገዋል። ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረም የተጫዋች ለውጣቸው ፍሬ ሊያፈራ ተቃርቦ ነበር። በዚህም ናትናኤልን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ፀጋ ለአብነት ያመቻቸለትን ኳስ አብነት በቀጥታ መትቶት ሙንታሪ እንደምንም መልሶታል። በ70ኛው ደቂቃ ደግሞ ማታይ ሉል ከመዓዘን የተሻማን ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ኤልፓዎች ግብ ፍለጋ ነቅለው መውጣታቸውን ለመጠቀም ያሳቡት ሀዋሳዎች ፈጣኖቹን አጥቂዎቻቸው ከተከላካይ ጀርባ እያስገኙ ሁለተኛ ጎል ሲፈልጉ ውለዋል። በ74ኛው ደቂቃ የግቡ ባለቤት ዓሊ ከሳጥን ውጪ ሲሞክር በረከት ሳሙኤል ደግሞ በ87ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ሌላ ጥቃት ሰንዝሯል። ነገርግን የማጥቃት ውጥናቸው ሳይሰምር ቀርቷል። ኤሌክትሪኮች ያላቸውን ኃይል አሟጠው ቢያንስ አቻ ለመውጣት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው እጅ ሰጥተው ወጥተዋል።