የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 1-0 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

👉”ዛሬ ቀረፃ ኖሮ ቢሆን ኖሮ ደጋፊዎቻችን እጅግ ይደሰታሉ ብዬ አስባለው” ዘርዓይ ሙሉ

👉”በዚህ ዓይነት መልኩ ይሄንን ውድድር ማድረግ አይቻልም” ገዛኸኝ ከተማ

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስላደረጉት እንቅስቃሴ…

የዛሬው እንቅስቃሴያችን እጅግ በጣም አሪፍ ነበር። እስካሁን አይተነው የነበረውን ነገር አግኝተን ነበር። በዚህ አስቸጋሪ ሜዳ ላይ እንደዚህ ኳስ ይዞ መጫወት፣ ተጋጣሚ ሜዳ መድረሳችን እና በመስመር ተከላካዮቻችን ተደጋጋሚ ጫና መፍጠራችን ሲታይ አንድ ጎል ያንሳል ትላለህ። የተሻሉ ኳሶችን አግኝተን ነበር። በእንቅስቃሴ ረገድ ግን እጅግ የተሻለ ነገር አሳይተናል። በጨዋታው ሙሉ ብልጫ ወስደን ነው የተጫወትነው። አራት ጨዋታ ካላሸነፈ ቡድን የታየው የራስ መተማመን ጥሩ ነበር። በአጠቃላይ መልበሻ ቤት የተነጋገርነውን ነገር ሜዳ ላይ በተግባር ያየንበት ነው። በሁሉም ነገር እጅግ በጣም ተደስቻለው።

ካለፉት ጨዋታዎች ተሻሽለው ስለቀረቡበት መንገድ….

ውጤት ስትፈልግ ሁል ጊዜ ጎል ትፈልጋለህ። ከዚህ በፊት ብዙ ጨዋታዎችን ማሸነፍ እየቻልን ወደ ኋላ ተጠግተን የተጫወትናቸው ጨዋታዎች አልተሳኩልንም። ዛሬ ግን ለማሸነፍ ያለን ብቸኛ አማራጭ ኳሱን ይዞ አጥቅቶ መጫወት ነበር። ሜዳ ላይም ያስገባናቸው ተጫዋቾች ለዚህ ጥሩ ነበሩ። የመስመር ተከላካዮቻችንም ወደ ፊት በተሻለ እየሄዱ ሲጫወቱ ነበር ፤ ይህንን ተከትል አጥቂዎቻችን ከበፊቱ በተሻለ አማራጮችን ያገኙ ነበር።

ከዚህ ቀደም ከሜዳ ውጪ ያለ አስተዳደራዊ ጉዳይ ብለው ስለሰጡት ሀሳብ…

የሚታይ ነው። በአንድ ሳምንት እንደዚህ ዓይነት የተሻለ እንቅስቃሴ መታየቱ ያ ጉዳይ እንደተቀረፈ ያሳያል። አንዳንዴ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ይከሰታሉ። ዞሮ ሁሌ ለማሸነፍ ስትጫወት ውጤታማ ትሆናለህ። እነዛ አካላትም ወደ አንተ ይመጣሉ። በአጠቃላይ ዛሬ ቀረፃ ኖሮ ቢሆን ኖሮ ደጋፊዎቻችን እጅግ ይደሰታሉ ብዬ አስባለው። ደጋፊዎቻችን ይህንን እድል አለማግኘታቸው ቢያሳዝነኝም ወደፊት ግን በእንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ እንቀጥላለን። ከዚህ ውጪ እኛም እንደ ሌላው ክለብ የሜዳ ጥቅም ሀዋሳ ላይ የምናገኝ ከሆነ ደጋፊዎቻችን በአግባቡ ኳሱን እያዩ ቡድናችንን ውጤታማ እናደርጋለን። ጠንክረን ሰርተን ሀዋሳን ወደ ነበረበት ቦታ እንመልሳለን።

አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ (ጊዜያዊ አሠልጣኝ) – ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ስለጨዋታው…

ጨዋታው ጥሩ ነበር። ተመጣጣኝ ፉክክር የተደረገበት ነው። ስህተቶችን ለመቀነስ ነበር የምንሞክረው ፤ ግን ስህተቶች ዋጋ እያስከፈሉን ነው። አሁንም በክፍተቶቻችን እና በጎደሉን ቦታዎች ላይ በደንብ መስራት እንዳለብን ነው የሚሰማኝ።

አጥቂው ናትናኤል በጊዜ ስለመቀየሩ…

እየተመራን ስለነበር ማጥቃት ነበረብን ፤ ግን ናትናኤል ጉዳት አስተናግዶ ስለነበር በአስገዳጅ ሁኔታ ቀይረነዋል።

ሦስት ነጥብ ማሳካት ስላለመቻላቸው…

ይሄንን ለመቅረፍ በተደጋጋሚ ሥራዎችን እየሰራን ነው። ተጫዋቾች ሥነ-ልቦና ላይ እየሰራን ነው። እንደገና የተጫዋቾች ለውጥም እያደረግን ነው። በዚህ ዓይነት መልኩ ይሄንን ውድድር ማድረግ አይቻልም። ከእንቅስቃሴ አንፃር ብዙ ለክፉ የሚሰጥ ነገር የለም። ነገር ግን የምናገኘውን ዕድል ተረጋግቶ የመጠቀም ነገር ነው ዋጋ እያስከፈለን ያለው።