ከፍተኛ ሊግ | የሦስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

በቶማስ ቦጋለ እና ጫላ አቤ

ዛሬ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከተደረጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች ሰባቱ በመሸናነፍ ሲጠናቀቁ ነቀምቴ ከተማ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ በመቶ ፐርሰንት አሸናፊነት ምድቦቻቸውን መምራት ቀጥለዋል።

የ04፡00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ ባቱ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻን ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም የግብ ዕድል በመፍጠሩም በኩል ባቱዎች እጅግ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በጨዋታው የተሻለው የግብ ሙከራ 28ኛው ደቂቃ ላይ ተደርጓል። እዩኤል ሳሙኤል በግራ መስመር ገፍቶ የወሰደውን ኳስ ወደ ግብ በቀጥታ ሲሞክር ኳሱ የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ኮምቦልቻዎች 45ኛው ደቂቃ ላይ ቃለፍቅር መስፍን ከረጅም ርቀት ሞክሮት በባቱ ተከላካዮች ተጨርፎ የወጣው ኳስ በአጋማሹ ብቸኛው የግብ ሙከራቸው ነበር።

ከዕረፍት መልስም በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሱት ባቱዎች 62ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር የሚችሉበት አጋጣሚ አግኝተው ነበር። የተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ፋሲል ባቱ ግብ ጠባቂውን ማለፍ ቢችልም ሳይጠቀምበት ቀርቶ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። በመጨረሻ ደቂቃዎች ይበልጥ የተነቃቁት ኮምቦልቻዎች በተሻለ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲጥሩ 73ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ሰለሞን ሀብቱ በግሩም ሁኔታ ቢሞክርም ኳሱ የላዩን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ጨዋታውም ያለግብ ተጠናቋል።

በምድብ ‘ለ’ ጅማ ላይ በተደረገው ቀዳሚ ጨዋራ ቦዲቲ ከተማ የዓመቱን የመጀመሪያ ድሉን በንብ ላይ አሳክቷል። ቦዲቲ በአማኑኤል ኦሌሳ እና ናትናኤል ዳንኤል የመጀመሪያ አጋማሽ ግቦች ቀዳሚ መሆን ሲችል የንቡ አማኑኤል ተሾመ 68ኛው ደቂቃ ያቆጠራት ግብ ልዩነቱን ከማጥበብ የዘለለ ፋይዳ ሳይኖራት ጨዋታው በቦዲቲ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በምድብ ‘ሐ’ ሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ የሆነው የጅማ አባ ጅፋር እና የደሴ ከተማ ጨዋታ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽ በጣም ውጥረት የተሞላበት እና ኃይል የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ነበር። በደሴ ከተማ በኩል ተደጋጋሚ በአማኑኤል ግዛቸው እና በማናዬ ፋንቱ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን መመልከት ችለናል። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ደግሞ በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ዕድሎችን ለመጠቀም በዱላ ሙላቱ እና በአሚር አብዱ አማካኝነት የግብ ሙከራዎች ተመልክተናል። በ15ኛው ደቂቃ ጅማ አባ ጅፋር ያገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት የደሴው ግብ ጠባቂ ምናለ በቀለ መመለስ ቢችልም የተመለሰው ኳስ ዱላ ሙላቱ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር። ሆኖም በ32ኛው ደቂቃ የተገኘውን ቅጣት ምት ያሬድ ሀሰን በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ደሴ ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ በአንፃሩ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር በእንቅስቃሴ ቀዝቀዝ ያለ እና የተወሰኑ የግብ ሙከራዎችን የተመለከትንበት አጋማሽ ሲሆን መደበኛው 90 ደቂቃ አልቆ በተጨማሪ ደቂቃ የደሴው ሀብታሙ ፍቃዱ ግብ በማስቆጠር ደሴ ከተማን ጣፋጭ ድል አስገኝቷል።

የ08፡00 ጨዋታዎች

በምድብ ‘ሀ’ የጅማ አባ ቡና እና ሰበታ ከተማ ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ የተሻለው የመጀመሪያ የግብ ሙከራ በጅማ አባ ቡናዎች ሲደረግ 4ኛ ደቂቃ ላይ በግራ መስመር የተሰጠውን የማዕዘን ምት አካሉ አበራ ሲያሻማ ያገኘው እስጢፋኖስ ብርሃኑ በግንባሩ በመግጨት ያደረገውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ሰበታዎች በአጋማሹ አንድ ሙከራ ብቻ ሲያደርጉ 33ኛው ደቂቃ ላይ ግራ መስመር ላይ የነበረው ዮናስ ሰለሞን ከረጅም ርቀት አክርሮ በመምታት ሙከራ ቢያደርግም የግቡን የቀኝ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ የተሻሻሉ የሚመስሉት እና ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ያደረጉት ሰበታዎች 56ኛው ደቂቃ ላይ የግብ ማስቆጠር አጋጣሚ ሲያገኙ ሳጥን ውስጥ ጥሩ ኳስ ያገኘው ኪዳኔ አሰፋ በደካማ አጨራረስ የግብ ዕድሉን አባክኗል። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም ያልታሰበ የመልሶ ማጥቃት ያደረጉት ጅማ አባ ቡናዎች በብዙዓየሁ እንደሻው የአጨራረስ ብቃት ታግዘው ግብ በማስቆጠር መሪ መሆን ችለዋል። በመጨረሻ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል የጠሩ የግብ ዕድሎች ሳንመለከትበት ጨዋታው በጅማ አባ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የምድብ ለ ሁለተኛ ጨዋታ ነቀምቴ ከተማ የመቶ ፐርሰንት አሸናፊነቱን ያስቀጠለበት ሆኗል። አምቦ ከተማን የገጠመው ቡድኑ ዳንኤል ዳዊት በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ግቦች መሪ መሆን ችሏል። ጫላ ከበደ 70ኛው ደቂቃ ላይ አምቦን ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተቃረበች ግብ ቢያስቆጥርም ጨዋታው በነቀምቴ 2-1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

በምድብ ‘ሐ’ ሆሳዕና ላይ የዕለቱ ሁለተኛ በሆነው የሶዶ ከተማ እና የኮልፌ ክ/ከተማ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም አመርቂ እንቅስቃሴ ያልታየበት ሲሆን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሚባል የግብ ሙከራ ሳይታይ 0-0 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ኮልፌ ተሽሎ በታየበት የጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ሌላ ገፅታ ይዞ በመምጣት ጨዋታውን በመቆጣጠር በእንቅስቃሴም ሆነ በግብ ሙከራ ተሽሎ ታይቷል። በአንፃሩ ሶዶ ከተማዎች በመከላከሉ እና መልሶ በማጥቃቱ ትኩረታቸውን ማድረግ መርጠዋል። በ75ኛው ደቂቃ ኮልፌዎች ያገኙትን ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ፊሊሞን ገ/ፃድቅ ግሩም በሆነ ሁኔታ በማስቆጠር መሪ መሆን ችለዋል። ከደቂቃዎች ቆይታ በኋላ በ81ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል የተገኘውን የግብ ዕድል ስንታየው ሰለሞን ተጠቅሞ የኮልፌ ክ/ከተማን ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል። በተቀረው ደቂቃ ሶዶ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የጣሩ ቢሆንም ሳይሳካላቸው ኮልፌ ክ/ከተማ ለሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዞ በማውጣት ምድቡን መምራቱን ቀጥሏል።

የ10፡00 ጨዋታዎች

ወልዲያ እና ሀላባ ከተማን ያገናኘው የምድብ ‘ሀ’ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ቢደረግም የተጠበቀውን ያህል ፉክክር ያልታየበት ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ አንድ ብቻ ፈታኝ ሙከራ ሲደረግ የወልዲያው ቢንያም ላንቃሞ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው በድሩ ኑርሁሴን በግንባሩ በመግጨት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት ወልዲያዎች 49ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በጋሻው ክንዴ በቀኝ መስመር ያደረገው ሙከራ የላዩን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶበታል። በሀላባዎች በኩል 72ኛው እና 88ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ማሞ አየለ ካደረጋቸው እና ግብ ጠባቂው ከመለሳቸው ሙከራዎች ውጪ የተሻለ የግብ ዕድል ሳይፈጠር ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።

በምድብ ‘ለ’ ይርጋጨፌ ቡና እና ካፋ ቡና በመጨረሻው ጨዋታ ተገናኝተዋል። በጨዋታው በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ተካልኝ መስፍን እና ዮሐንስ ኪሮስ ቀዳሚ የሆኑት ይርጋጨፌ ቡናዎች በካፋ ቡናው ዮናታን ከበደ 39ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ቢቆጠርባቸውም መሪነታቸውን ይዘው እስከፍፃሜ በመቀጠል 2-1 መርታት ችለዋል።

ሆሳዕና ላይ ቡራዩ ከተማ እና ነገሌ አርሲን ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ነጌሌ አርሲ በኳስ ቁጥጥር በመብለጥ እንዲሁም ቡራዩ ከተማ አፈግፍጎ በመጫወት የሚገኙ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመጠቀም ሲሞክሩ ታይተዋል። ሆኖም በሁለቱም በኩል ምንም ግብ ሳይቆጠር የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ችሏል። በሁለተኛው አጋማሽም ሁለቱም ቡድኖች እንደመጀመሪያው አጋማሽ አጨዋወታቸውን ሳይቀይሩ በነጌሌ አርሲዎች የጨዋታ ብልጫ የቀጠለ ቢሆንም ቡራዩ ከተማዎች በ68ኛው ደቂቃ ያገኙትን የመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድል በሙሉጌታ ካሳሁን አማካኝነት ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። ግቡ ከተቆጠረባቸው በኋላ ነጌሌ አርሲዎች በበለጠ መልኩ ጫን ብለው የተጫወቱ ቢሆንም ኳስን ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው ሽንፈት ለማስተናገድ ተገደዋል።