በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጀመሪያዋን የውጪ ዜጋ ተጫዋች ለማስፈረም የሙከራ ዕድል ሰጥቷል።
የ2015 ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ከተማ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በስድስት ጨዋታዎች አምስት አሸንፎ በአንዱ ብቻ በመረታት አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ክለቡ የሊጉ ውድድር ገና ጅማሮ ላይ ቢሆንም በሁለተኛው ዙር ራሱን ለማጠናከር ከወዲው እንቅስቃሴ ጀምሯል። በዚህም በኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ታሪክ የመጀመሪያ የውጪ ተጫዋች ለማስፈረም እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።
በዚህም ክለቡ ለኤርትራዊቷ ተከላካይ ሪም ገዛኢ የማነ የሙከራ ጊዜ የሰጠ ሲሆን ተጫዋቿም ከትናንት በስትያ ሀገራችን ገብታ የሙከራ ጊዜዋን እንደጀመረች ታውቋል። ለኤርትራ ከ20 ዓመት በታች እና ዋናው ብሔራዊ ቡድን ተጫውታ ያሳለፈችው ሪም ገዛኢ ለሀገሯ ክለብ ደንደንም ግልጋሎት ስትሰጥ ነበር። ምናልባት የሙከራ ጊዜዋት በተሳካ ሁኔታ ካገባደደች የውድድር አጋማሽ የዝውውር መስኮት ሲከፈት የመጀመሪያዋ የውጪ ዜጋ ተጫዋች በመሆን ፊርማዋን የምታኖር ይሆናል።
ንግድ ባንክ ከሪም ገዛኢ በተጨማሪ ዩጋንዳዊ የመስመር ተጫዋችም ለማምጣት ንግግር ላይ የሚገኝ ሲሆን በቅርቡ የወረቀት ሥራዎች ተጠናቀው ሌላኛዋ ተጫዋች ለሙከራ ወደ ሀገራችን እንደምትገባ ተጠቁሟል።