ሪፖርት | መድን እና ፋሲል ነጥብ ተጋርተዋል

ጥሩ ፉክክር የተደረገበት የኢትዮጵያ መድን እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማን ሁለት ለአንድ የረቱት ኢትዮጵያ መድኖች በአሰላለፋቸው ላይ ምንም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ በተቃራኒው በድሬዳዋ ከተማ በተመሳሳይ ውጤት የተሸነፉት ፋሲል ከነማዎች ደግሞ መናፍ ዐወል ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ሀብታሙ ገዛኸኝን በአስቻለው ታመነ ፣ ታፈሰ ሠለሞን እና ጉልላት ተሾመ ተክተው ጨዋታውን ቀርበዋል።

ተጠባቂው ፍልሚያ ገና ከጅምሩ ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን አስመልክቷል። በቅድሚያ በ5ኛው ደቂቃ የተሻማባቸውን የመዓዘን ምት አክሽፈው በፈጣን ሽግግር ወደ ፋሲል ግብ ክልል ያመሩት መድኖች ኪቲካ ጅማ ከአብዱልከሪም መሐመድ በተቀበለውና በግንባር በሞከረው ኳስ መሪ ሊሆኑ ነበር። ከደቂቃ በኋላ ለተሰነዘረባቸው ሙከራ ምልሽ ለመስጠት ያሰቡት ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው ሽመክት ጉግሳ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታውና ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በመለሰው ሙከራ ጥቃት ሰንዝረዋል። በ8ኛው ደቂቃ ግን ግብ ጠባቂያቸው ሜኬል ሳማኬ ባያድናቸው ኖሮ ዩጋንዳዊው አጥቂ ሲሞን ፒተር እጅግ የሰላ የግንባር ኳስ ሞክሮባቸው ነበር።

ወደ ግብ በመድረሱ ረገድ የተሻሉት ኢትዮጵያ መድኖች በፈጣን ቅብብሎቻቸው እና በፈጣኖቹ አጥቂዎቻቸው የግብ መንገድ ለማግኘት ታትረዋል። በ23ኛው ደቂቃም ሀቢብ ከማል ወደ መሐል ሰብሮ በመግባት የሞከረው ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ ያገኘው ባሲሩ ዑማር ጥብቅ ምት መትቶ ነበር። በመጠኑ ጫና የበዛባቸው ፋሲሎች ከጠቀስነው ሙከራ በኋላ በተከታይ ሦስት ዕድሎችን ፈጥረዋል። ሱራፌል ዳኛቸው ከቅጣት ምት ሁለቱን ሙከራዎች ሲያደርግ ሽመክት ደግሞ ሌላኛውን ከውኖ ለጥቂት ወጥቶባቸዋል። ሁለቱን ሙከራዎች ያደረገው ሱራፌል በ34ኛው ደቂቃ የግል ጥረቱት ተጠቅሞ ሳጥን ውስጥ በመገኘት ሌላ ሙከራ ሰንዝሮ ኳስ የውጪውን መረብ ነክቶ ወጥቶበታል።

የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከቀዳሚው በተለየ የግብ ሙከራዎች አልበረከቱበትም። በአንፃራዊነት ፋሲል ከነማዎች የተጋጣሚን ሳጥን በመጎብኘት ረገድ መሻሻል ቢያሳዩም የጠራ ዕድል መፍጠር ቀላል አልሆነላቸውም። ወደ ራሳቸው ሜዳ ወረድ ብለው የፋሲልን ጫና መመከት የተያያዙት መድኖች ደግሞ በአጋማሹ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙከራ ያደረጉት በ69ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህም በፈጣን ሽግግር የተገኘውን ዕድል ሀቢብ እና ሲሞን በወረደ ተግባቦት አጨራረሱን ሳያሳምሩት ቀርተዋል።

ዐፄዎቹ በ82ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህም ሽመክት በረጅሙ የተሻማውን ኳስ ተቆጣጥሮ ለሱራፌል ሲያመቻቸው በግሉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሱራፌል አክርሮ መትቶት የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ውጪ አውጥቶበታል። በቀሪ ደቂቃዎች ፋሲል ተጭኖ የተጫወተ ሲሆን መድን ደግሞ ግቡን እየጠበቀ በመልሶ ማጥቃት ብቻ አንዳች ነገር ለመፍጠር ጥሯል። ነገር ግን ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።