የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ተጠባቂው ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ድሬዳዋ እና አርባምንጭ ድል ቀንቷቸዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በሦስት ጨዋታዎች ቀጥሎ ተጠባቂው የሀዋሳ ከተማ እና መቻል ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲፈፀም ድሬዳዋ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ በበኩላቸው ከተጋጣሚዎቻቸው ላይ ሦስት ነጥብን አሳክተዋል፡፡

04:00 ሲል የሳምንቱ አራተኛ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ እና አዳማ መካከል የተካሄደ ነበር፡፡ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ጨዋታውን ወደ ራሳቸው አድርገው በመቆጣጠር ጫና ለማሳደር የሞከሩት ድሬዳዋዎች 5ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ አቅጣጫ አምበሏ ታደለች አብርሃም ወደ ውስጥ የግል ጥረቷን ተጠቅማ በመግባት ያሻማችላትን ኳስ ሊዲያ ጌትነት ነፃ አቋቋም ላይ ሆና የደረሳትን ወደ ጎልነት ቀይራው የአሰልጣኝ እዮብ ተዋበን ቡድን መሪ አድርጋለች፡፡ ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት ግብ ካስተናገዱ በኋላ ሙከራዎችን ለማድረግ የዳዱት አዳማ ከተማዎች በተደጋጋሚ ግልፅ ዕድሎችን ለመፍጠር አስበው መንቀሳቀስ ቢችሉም በቀላሉ ግን የድሬዳዋን ግብ ክልል ለማለፍ ተቸግረው መመልከት ችለናል፡፡

ከዕረፍት ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያስተዋልን ቢሆንም በተለይ አዳማ ከተማዎች ወደ አቻነት ውጤት ለመምጣት በሔለን እሸቱ እንዲሁም ተቀይራ በገባችው ይታገሱ ተገኝወርቅ አማካኝነት የተደጋገሙ ሙከራዎችን አድርገው የነበረ ቢሆንም ወደ ጎልነት እንዳይለወጡ ግን በግብ ጠባቂዋ ሳራ ብርሀኑ ሊከሽፉ ተገደዋል፡፡ የሆነው ሆኖ በጥብቅ መከላከል በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት እና ሁለተኛ ጎል ለማግኘት ሽግግሮችን ያደርጉ የነበሩት የምስራቆቹ እንስቶች መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ሜላት ደመቀ እጅግ አስደናቂ ግብን አስቆጥራ ጨዋታው በድሬዳዋ 2-0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡ ለድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያውን ግብ ከመረብ ያገናኘችው ሊዲያ ጌትነት የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተሸልማለች፡፡

ተጠባቂ የሆነው እና በርካታ ተመልካቾችን ያስመለከተን የሀዋሳ ከተማ እና መቻል ጨዋታ በመጨረሻም ነጥብ በመጋራት ከድምዳሜ ደርሷል፡፡ በቀዳሚው የጨዋታው አጋማሽ ባለ ሜዳው ሀዋሳ ከተማ በሁሉም ረገድ ብልጫ ያሳየበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከመስመር መነሻቸውን አድርገው ወደ አጥቂ ክፍሉ በሚጣሉ ኳሶች የመቻልን የመከላከል ሂደት ለመስበር ገና በጊዜ ሀዋሳዎች ጅምራቸውን ማድረግ ቢችሉም ጠጠር ብሎ ለደቂቃዎች የዘለቀውን የመቻል የተከላካይ ክፍል ለማስከፈት ግን አላስቻላቸውም፡፡
 

የኋላ መስመራቸውን እየጠበቁ በመልሶ ማጥቃት ከረጃጅም ኳስ ሴናፍን ትኩረት አድርገው ቢንቀሳቀሱም 30ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል፡፡ በአንድ ሁለት ኳስን ሀዋሳ ከተማዎች ተቀባብለው የቀኝ መስመር ተከላካዩዋ ማዕደር ባዬ በቀጥታ ወደ መቻል የግብ ክልል ስታሻግር የግብ ጠባቂዋ እምወድሽ ይርጋሸዋ እና ተከላካዮች ዝንጉነት እሙሽ ዳንኤል ሾልካ በመውጣት ኳስን ከመረብ አዋህዳ ቡድኗን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ ከጎሉ መቆጠር በኋላ ምላሽ ለመስጠት ያላመነቱት መቻሎች ዕድሎችን ማግኘት ቢችሉም የሀዋሳን ተከላካይ ማለፍ አቅቷቸው ተስተውሏል፡፡ ይሁን እንጂ ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ ሦስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ ከቅጣት ምት መንደሪን ክንዲሁን ስታሻማው ቱሪስት ለማ በግንባር ገጭታ በማስቆጠር ሀዋሳን 2-0 አድርጋለች፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ አጀማመሩ የተቀዛቀዘ ቢመስልም ከደቂቃዎች መግፋት በኋላ ግን የሀዋሳ ከተማ ፍፁም ዝንጉነት የመቻሎች የበላይነትን የተመለከትንበት ነበር፡፡ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ በይበልጥ መነቃቃት ውስጥ የገቡት መቻሎች በተደጋጋሚ በፈጠሩት ጫና ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ግብ አግኝተዋል፡፡ 60ኛው ደቂቃ ላይ ገነት ኃይሉ ከቅጣት ምት ወደ ግብ ክልል የላከችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ፍሬወይኒ ገብሩ በአግባቡ ሳትቆጣጠር ቀርታ የለቀቀችውን ኳስ ቤተልሄም በቀለ ጎል አድርጋዋለች፡፡ ለሀዋሳ ተከላካዮች ፋታ የለሽ እንቅስቃሴን በማድረግ ወደ አቻነት ለመምጣት ጥረቶች ያልተለያቸው መቻሎች ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ሴናፍ ዋቁማ ኳስን እየገፋች ወደ ውስጥ ገብታ ሁለተኛ ጎልን በማስቆጠር ቡድኗን አቻ አድርጋ በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎሎችን ሳያስመለክተን 2-2 ተጠናቋል፡፡ ለመቻል የሁለተኛ አጋማሽ መሻሻል ቁልፍ የነበረችው ሴናፍ ዋቁማ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተመርጣለች፡፡

የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ በሆነው የአርባምንጭ ከተማ እና ልደታ ክፍለ ከተማ መርሀግብር በመጨረሻም በእንስት አዞዎቹ አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሆኗል፡፡ አሰልቺ ይዘትን የተላበሰው እና መሀል ሜዳ ላይ ብቻ በተበራከቱ የቅብብል ሂደቶች ረጅሙን ደቂቃ የዘለቀው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ቤተልሄም ሰማን እንዲሁን ከዕረፍት መልስ ቤተልሄም ታምሩ የግል አቅሟን ተጠቅማ ወደ ሳጥን ይዛ ገብታ ሁለተኛ ግብን በማስቆጠር የአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ቡድን አርባምንጭ ከተማ 2-0 እንዲያሸንፍ አስችለዋል፡፡ በጨዋታውም አንፃራዊ የተሻለ ብቃትን ስታደርግ የነበረችው አጥቂዋ ቤተልሄም ታምሩ የጨዋታው ኮከብ በመባል ሽሎማቷን ተቀብላለች፡፡