ሪፖርት | አዞዎቹ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ጎል ነጥብ ተጋርተዋል

በጨዋታ ሳምንቱ የማሳረጊያ መርሐ-ግብር አርባምንጭ ከተማ እና ለገጣፎ ለገዳዲ አንድ አቻ ወጥተዋል።

ምሽት 01፡00 ላይ የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በለገጣፎ ለገዳዲ እና አርባምንጭ ከተማ መካከል ሲደረግ ለገጣፎዎች በአዳማ ከተማ 3-0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም በሽር ደሊል ፣ አስናቀ ተስፋዬ ፣ ዮናስ በርታ እና ካርሎስ ዳምጠው የሚኪያስ ዶጂ ፣ መዝገቡ ቶሎ ፣ ፍቅሩ ዓለማየሁ እና ኦኬይ ጁልን ቦታ ተክተው ገብተዋል። አዞዎቹም በተመሳሳይ  ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር 2 አቻ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ አሸናፊ ፊዳ ፣ ቡታቃ ሸመና ፣ መሪሁን መስቀል እና በላይ ገዛኸኝ በበርናንድ ኦቼንግ ፣ አቡበከር ሻሚል ፣ እንዳልካቸው መስፍን እና ኤሪክ ካፓይቶ ተተክተው ጀምረዋል።

የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት አርባምንጭ ከተማዎች ብዙ ደጅ ሳይጠኑ በ7ኛው ደቂቃ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። የመልስ ውርወራ አግኝተው ሙና በቀለ ወደ ሳጥን ሲልከው በበላይ ገዛኸኝ ጫና የደረሰበት ዮናስ በርታ በሚገባ ማፅዳት ሳይችል ቀርቶ ሱራፌል ዳንኤል ደርሶበት መዳረሺያውን መረብ አድርጎታል።

በጊዜ መመራት የጀመሩት ለገጣፎ ለገዳዲዎች የኋላ መስመራቸው ላይ የአቋቋም እና የመናበብ ክፍተቶች ቢኖሩባቸውም ቀጥተኛ ኳሶችን በማዘውተር ግብ ሲፈልጉ ነበር። እስከ አጋማሹ መገባደጃ ድረስ ግልፅ የግብ ዕድል ባይፈጥሩም በመሐል በኢብሳ በፍቃዱ አማካኝነት አንድ ጥቃት ሰንዝረዋል።

በሚፈልጉት መንገድ ጨዋታው እየሄደላቸው የሚገኙት አዞዎቹ ያልተደራጀውን የጣፎ የኋላ መስመር እየተጫኑ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረዋል። በቅድሚያ መሪሁን መስቀሌ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ሲመታ በ22ኛው እና 24ኛው ደቂቃ ደግሞ ሱራፌል ዳንኤል እና ቡጣቃ ሸመና በተከታታይ የተከላካዮችን ስህተት ተጠቅመው የቡድናቸውን መሪነት ለማሳደግ ጥረዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ አህመድ ሁሴን የግብ ጠባቂውን መውጣት ተከትሎ የመታው ኳስ ሌላ ሙከራ ሆኖ አልፏል። ከላይ እንደገለፅነው ለገጣፎ ለገዳዲዎች በ45ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በካርሎስ ዳምጠው አማካኝነት አድርገው መክኖባቸዋል።

የማጥቃት ኃይላቸውን ለማደስ የተጫዋች ለውጥ አድርገው ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በ47 እና 48ኛው ደቂቃ በዮናስ በርታ እና መሐመድ አበራ አማካኝነት ከግብ ጋር ለመገናኘት ጥረው ዒላማውን ስቶባቸዋል። አርባምንጮች በበኩላቸው በ51ኛው ደቂቃ ወደ ቀኝ ካደላ የሳጥኑ መግቢያ ያገኙትን የቅጣት ምት በቡጣቃ አማካኝነት ሞክረውት የግቡን ቋሚ ታኮ ወጥቶባቸዋል።

አሁንም ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ያላቸውን አቅም በመጠቀም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መሄድ የቀጠሉት ጣፎዎች በ58ኛው ደቂቃ ጋብሬል አህመድ አክርሮ በመታው ኳስ አቻ ሊሆኑ ነበር። በተቃራኒው ጫና መፍጠራቸውን ገታ ያደረጉት አርባምንጮች በ63ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን ጥሩ ሙከራ አድርጎላቸው ነበር። ቀሪ የጨዋታው ደቂቃ የወረደ የሜዳ ላይ ፉክክር ቢያስመለክትም በጭማሪው ደቂቃ ግብ አስተናግዷል። በዚህም በረጅሙ የተመታን ኳስ ከተከላካዮች ተነጥሎ ወጥቶ የነበረው ኢብሳ በፍቃዱ በግንባሩ ግብ አድርጎት ቡድኑን አቻ አድርጓል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ተጠናቋል።