ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ12ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የነጠረ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾች እምብዛም ባልታዩበት የ12ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በአንፃራዊነት የተሻሉትን በመምረጥ ተከታዩን ምርጥ ቡድን ሰርተናል።

የተጫዋች አደራደር ቅርፅ : 4-4-2 (ዳይመንድ)

ግብ ጠባቂ


ፔፔ ሰይዶ – ሀዲያ ሆሳዕና

በሊጉ በስድስት ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረው የሀዲያ ሆሳዕናው ግብ ጠባቂ ፔፔ ሰይዶ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ በአዳማ ከተማ ጫናዎች በዝተውበት በነበረበት ጊዜ በአስደናቂ ቅልጥፍና ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን እያመከነ ቢያንስ አንድ ነጥብ እንዲገኝ አስችሏል።

ተከላካዮች


ሳሙኤል አስፈሪ – ወልቂጤ ከተማ

ታታሪው የመስመር ተከላካይ በሁሉም የወልቂጤ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ጥሩ አበርክቶ ሲሰጥ ይታያል። በመቻሉ ጨዋታ ተጫዋቹ ለጎሉ መገኘት ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ሲያበረክት በመከላከልም እርሱ በተሰለፈበት መስመር የነበረው ከነዓን እንዲሁም ተቀይሮ የገባው በረከት አንዳች ነገር እንዳይፈጥሩ አድርጓል።

ደጉ ደበበ – ወላይታ ድቻ

አንጋፋው የመሐል ተከላካይ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ወደ አሰላለፍ መጥቶ ቡድኑን በሚገባ እየጠቀመ ነው። ለመከላከል ቅድሚያ በሚሰጠው ስብስብ ውስጥም ትኩረት እና ቅንጅት የሚሻውን ከባድ ሥራ እየመራ የተጋጣሚን ጥቃቶች ሲያመክን ነበር። በጨዋታ ሳምንቱም ቀጥተኛ አጨዋወትን ሲከተል የነበረውን የድሬ የማጥቃት እንቅስቃሴ በሚገባ ተቆጣጥሮ ወጥቷል።

ቴዎድሮስ በቀለ – ኢትዮጵያ መድን

ቁመታሙ ተከላካይ ቡድኑ በፋሲሉ ጨዋታ አንድ ነጥብ ይዞ ሲወጣ የውጤት ረሀብ ውስጥ የነበሩትን የተጋጣሚ ተጫዋቾች የማጥቃት እንቅስቃሴ በጥሩ የውሳኔ አሰጣጥ ሲመክት ነበር። በአየርም ሆነ በመሬት ላይ ፍልሚያዎች ጥሩ አፈፃፀም የነበረው ቴዎድሮስ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የነበረው የመከላከል ተሳትፎ በምርጥ ቡድናችን እንዲገባ አስችሎታል።

አቤኔዘር ኦቴ – ሀዋሳ ከተማ

ባሳለፍነው ሳምንት ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ በቋሚነት ቡድኑን እንዲያገለግል ዕድል የተሰጠው አቤኔዘር የተዋጣለት ዕለት ሲያሳልፍ ተስተውሏል። ተጫዋቹ ዋነኛ ኃላፊነቱ የነበረውን የመከላከል ሥራ በአግባቡ ከመከወኑ በላይ በተሰለፈበት መስመር ወደ ላይኛው ሜዳ እየተጓዘ የማጥቃት አበርክቶ ሲሰጥ ውሏል።

አማካዮች


አብዱልባሲጥ ከማል – ሀዋሳ ከተማ

የተጫዋች አደራደር ለውጥ አድርገው የ12ኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ባደረጉት ሀዋሳዎች ስብስብ ውስጥ በመሐል ሜዳው ላይ መልካም የሚባል እንቅስቃሴ ሲያደርግ የተመለከትነው አብዱልባሲጥ ነው። ከወትሮ በተለየ ትንሽ የተሻለ የማጥቃት ነፃነት ተሰጥቶት የነበረው ተጫዋቹ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል እየተገኘ የቡድኑን የማጥቃት ቁጥር ሲያበዛ ታይቷል።

አማኑኤል ጎበና – አዳማ ከተማ

ምንም እንኳን አዳማ ከተማዎች በሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ ግብ ሳያስቆጥሩ ቢወጡም በእንቅስቃሴ የነበረውን ብልጫ ካስገኙ ተጫዋቾች አንደኛው አማኑኤል ነበር። ዘለግ ያለውን ደቂቃ ከኳስ ጋር ለታየው አዳማ ተጫዋቹ ወደ ፊት ጠጋ ብሎ ጥቅጥቅ ያለውን የሀዲያ የመከላከል ቅርፅ ለማስከፈት አማራጭ ለመሆን ሲጥር የነበረ ሲሆን ከኳስ ውጪም በሽግግሮች ለማጥቃት የወጠኑትን የተጋጣሚ ተጫዋቾች ሀሳብ ከመነሻው ሲያቋርጥ ነበር።

ወንድማገኝ ኃይሉ – ሀዋሳ ከተማ

ወደሜዳ ከተመለሰ በኋላ የቀደመ ምርጥ ብቃቱን ለማግኘት ሲቸገር የነበረው ወንድማገኝ በዚህኛው ሳምንት በአንፃራዊነት ጥሩ ጊዜ ነበረው። በመስመሮች መካከል እየተገኘ አደገኛ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክር የነበረው ወንድማገኝ ከወትሮ በተሻለ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ኳሱን ይዞ ለነበረው ሀዋሳ ቅጥጥሩን እድገት እንዲኖረው በማስቻል ቁልፍ ሚና ተወጥቷል።

ሱራፌል ዳኛቸው – ፋሲል ከነማ

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ጨዋታ የተጫወተው ሱራፌል ቡድኑ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ያለ ግብ ቢለያይም በግሉ አይነተኛ የግብ ምንጭ ለመሆን ከየትኛውም ተጫዋች በላይ ሲጥር ነበር። ምንም እንኳን ተጫዋቹ ባይሳካለትም ሁለት ከቅጣት ምት ሁለት ከክፍት ጨዋታ ለግብነት የቀረቡ ዕድሎችን ፈጥሮ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ሞክሮ መክኖበታል።


አጥቂዎች


ስንታየሁ መንግስቱ – ወላይታ ድቻ

የጎል ድርቅ በመታቸው የ12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አሳማኝ ብቃት ያሳዩ አጥቂዎችን ማግኘት ባንችልም በአንፃራዊነት በፈታኙ ጨዋታ የተቆጠረውን የድቻ ግብ ያስገኘው ስንታየሁ በቦታው መርጠናል። እርግጥ ተጫዋቹ ከግቡ ውጪ እምብዛም ሌላ የጠሩ ዕድሎችን ባይፈጥርም የግቡን ክብደት ሚዛን ላይ በማድረግ ተጫዋቹን ለመምረጥ ችለናል።

ዓሊ ሱሌይማን – ሀዋሳ ከተማ

ከኃይቆቹ ስብስብ በምርጥ ቡድናችን የተካተተው ሌላኛው ተጫዋች ዓሊ ሱሌይማን ነው። ከሙጂብ መጎዳት በኋላ የሳጥን አጥቂ የነበረው ዓሊ ፍጥነቱን ተጠቅሞ በተደጋጋሚ ከተከላካዮች ጀርባ ለመገኘት የሚጥር ሲሆን በኢትዮ ኤሌክትሪኩም ጨዋታ በተመሳሳይ መንገድ በመገኘት የግብ ጠባቂውን ፍቅሩ ስህተት ተጠቅሞ ቡድኑን ከናፈቀው ድል ጋር ያገናኘ ግብ አስቆጥሯል።

አሠልጣኝ


ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

በመቀመጫ ከተማው አልቀመስ ያለው እና ያለፉትን ስምንት ጨዋታዎች ያልተረታው ድሬዳዋ ከተማን ያሸነፉት የወላይታ ድቻ አሠልጣኝ ፀጋዬ ያለ ከልካይ የምርጥ ቡድናችን መሪ ሆነዋል። በተከታታይ ሁለት ፈታኝ ጨዋታዎችን ከውነው ሦስት ሦስት ነጥብ ያሳኩት ድቻዎች ባላቸው የስብስብ አቅም የተጋጣሚን ጠንካራ ጎን አክሽፈው ጥሩ በሆኑበት መንገድ ጨዋታውን የወሰኑበት ሂደት ለአሠልጣኙ ትልቅ አድናቆት እንዲቸራቸው አድርጓል።

ተጠባባቂ

መሐመድ ሙንታሪ
ዳንኤል ደርቤ
መልካሙ ቦጋለ
ሱራፌል ዳንኤል
ቡጣቃ ሸመና
በኃይሉ ተሻገር
ተመስገን በጅሮንድ
አቡበከር ወንድሙ