ሪፖርት | ድንቅ ግቦች ያሳየን ጨዋታ በመቻል አሸናፊነት ተጠናቋል

ሳቢ በነበረው የ13ኛው ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ መቻል ባህር ዳር ከተማን 3-2 በማሸነፍ የድሬዳዋ ቆይታውን በድል አጠናቋል

ባህር ዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ አንፃር ዛሬ ኦሴይ ማዉሊን በሀብታሙ ታደሰ ለውጦ ሲያስገባ በተመሳሳይ ከወልቂጤ ከተማ አቻ በተለያየው መቻል በኩል ደግሞ አሚን ነስሩ እና ከነዓን ማርክነህ አርፈው ኢብራሂም ሁሴን እና በረከት ደስታ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጥሩ ፉክክር ያስመለከተን ጨዋታ ቀዳሚው አጋማሽ በባህር ዳር ከተማ የማጥቃት ጫና የጀመረ ነበር። ቡድኑ ፈጠን ባሉ ቅብብሎች በሁለቱ መስመሮች በፍፁም ጥላሁን እና ዱሬሳ ሹቢሳ በኩል ወደ ግብ ለመድረስ ሲጥር ይታይ ነበር። ሆኖም የመቻሉ ፍፁም ዓለሙ 11ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ በጠንካራ ምት የመጀመሪያውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጎ በፋሲል ገብረሚካኤል ድኖበታል።

መቻሎች የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ በማቋረጥ ወደ በረከት ደስታ በሚልኳቸው ቀጥተኛ ኳሶች የመልሶ ማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ ይታይ ነበር። በጥሩ የማጥቃት ምልልስ በቀጠለው ጨዋታ 15ኛ ደቂቃ ላይ ሳለአምላክ ተገኘ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ኦሴይ ማዉሊ በግንባሩ ሞክሮ በግቡ አግዳሚ ሲመለስበት ፍፁም ጥላሁን በድጋሚ የገጨውን ደግሞ ግሩም ሀጎስ አውጥቶታል። በቀጣይ ደቂቃዎች ጨዋታው በፉክክሩ ቢቀጥልም ሙከራዎች ሳያሳየን ሲቆይ የጣና ሞገዶቹ 28ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት የገጠመው ያሬድ ባየህን በተስፋዬ ታምራት ለመተካት ተገደዋል።

ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሲቃረብ ሁለት ግቦችን አስመልክቶናል። በቅድሚያ 39ኛው ደቂቃ ላይ ባህር ዳሮች ከፉዓድ ፈረጃ የተነሳውን ቅጣት ምት ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ሳይቆጣጠረው ያገኙትን ዕድል በዱሬሳ ሹቢሳ አማካይነት ጎል ሲያደርጉት ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ መቻሎች አማካዩ በኃይሉ ግርማ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ባስቆጠራት ድንቅ ግብ አቻ መሆን ችለዋል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ በድጋሚ በጎል የታጀበ ሆኗል። 49ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ ኳስ እየነዳ በቀኝ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ወደ ውስጥ ያቀበለውን ኳስ እስራኤል እሸቱ የሚመታ መስሎ ኳስ በእግሮቹ መሀል ሲያሳልፍ በረከት ደስታ ተቀብሎ ግብ በማድረግ መቻልን መሪ አድርጓል። ሆኖም ባክር ዳር ምላሽ ለመስጠት ጥቃት መሰንዘር ሲጀምር 53ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ጥላሁን የግንባር ሙከራ አድርጎ በዳግም የዳነበት ሲሆን ከሁለት ደቂቃ በኋላ ግን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ከግብ ጠባቂው በረጅሙ የታላከውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን በግራው የሳጥን ክፍል ተቆጣጥሮ ሲያመቻችለት ኦሴይ ማዉሊ አክርሮ በመምታት ጎል አድርጎታል።

ቀድሞ ሦስተኛ ጎል ለማግኘት በሁለቱም በኩል ጥድፊያ የተሞላባቸው የማጥቃት ጥረቶች እና የቆሙ ኳስ ዕድሎችን በማሳየት በቀጠለው ጨዋታ ባህር ዳሮች በሙከራ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። ቡድኑ በፉዓድ ፈረጃ እና ኦሳይ ማዉሊ አማካይነት ከሳጥን ውጪ ጠንካራ ሙከራዎችን ሲያደርግ በተለይ የ68ኛ ደቂቃ የማዉሊ ሙከራ በዳግም ተፈራ ጥረት የዳነ ነበር። የማጥቃት ሙከራቸው በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ እየሆነባቸው የቆዩት መቻሎች በአንፃሩ 73ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ድንቅ ግብ አግኝተዋል። ተቀይሮ በገባ ሁለት ደቂቃዎች ውስጥ ከነዓን ማርክነህ ካሳጥን ውጪ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ በጣና ሞገዶቹ መረብ ላይ አርፏል።

በከነዓን ቅያሪ ያለተፈጥሯዊ ዘጠኝ ቁጥር መሀል ላይ በዝተው ጨዋታውን የቀጠሉት መቻሎች በቀሪ ደቂቃዎች አጠቃላይ እንቅስቃሴው ከሳጥናቸው እንዲርቅ ማድረግ ችለዋል። በዚህም ባህር ዳር ከተማ ድሬዳዋ ላይ የመጀመሪያ ሽንፈቱን እንዲያስተናግድ በማድረግ ጨዋታውን በ3-2 ድል ጨርሰዋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጠንካራ ጨዋታ እንደሚሆን መገመታቸውን አንስተው የያሬድ ባየህን መውጣት ተከትሎ የታየባቸው ትኩረት ማጣት ዋጋ አንዳስከፈላቸው በማንሳት ተጋጣሚያቸው ያሳየውን አቋም አድንቀዋል። የመቻሉ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው የጨዋታውን አስፈላጊነት እና ክብደት አስታውሰው የነበራቸው ተነሳሽነት ከመመራት ተነስተው ለማሸነፍ እንደረዳቸው ጠቁመው አሁንም ቡድናቸው ማሻሻል የሚገባቸው ነጥቦች እንዳሉት አብራርተዋል።