ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ተጋርተዋል

ሦስት ብቻ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን በተመለከትንበት እምብዛም ለተመልካች ሳቢ ባልነበረው የምሽቱ መርሃግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ተጋርተዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሀዋሳ ከተማው ሽንፈት ባደረገው ብቸኛ ለውጥ ሄኖክ አየለ የአቤል ሀብታሙን ቦታ ይዞ ጨዋታውን ሲጀምር በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ግርማ በቀለ ፣ ተመስገን ብርሀኑ ፣ ምንተስኖት አካሉ እና ራምኬል ሎክ ጨዋታውን ሲጀምሩ ቡድኑ ከአዳማ ያለግብ በተለያየበት ጨዋታ የተሰለፉት ካሌብ በየነ ፣ ብርሀኑ በቀለ ፣ ስቴቨን ናያርኮ እና ሠመረ ሀፍተይ ደግሞ በዛሬው ጨዋታ በተጠባባቂነት የጀመሩት ነበሩ።

ጨዋታው ወደ ኢትዮ ኤላክትሪክ ሜዳ ባመዘነ እንቅስቃሴ የጀመረ ሆኗል። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የያዙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለመሰንዘር በመሞከር ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ደግሞ የተፈጠረባቸውን ጫና ለማርገብ በመጣር ተንቀሳቅሰዋል።

ሆሳዕናዎች 18ኛ ደቂቃ ላይ ቀዳሚውን ከባድ ሙከራ ሲያደርጉ ሄኖክ አርፌጮ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በፍቅሩ ወዴሳ ሲመለስ ራምኬል ሎክ በድጋሚ ወደ ግብ የላከው ኳስ ነጥሮ ወጥቶበታል። በቀጣይ ደቂቃዎች የነብሮቹ ጥቃት በመጠኑ ቀነስ ብሎ ጨዋታው በመሀል ሜዳ ፍልሚያ አመዝኖ ሲታይ በሌላኛው የቡድኑ ሙከራ 26ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አርፌጮ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ፍቅረየሱስ በግንባሩ ገጭቶት ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

እምብዛም ሳቢ ባልነበሩት ቀሪዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ደቂቃዎች የጨዋታ ሂደቱ በአመዛኙ በኤሌክትሪክ የሜዳ አጋማሽ ላይ ቢያደላም ሆሳዕናዎች ይህ ነው የሚባል የጠራ የግብ እድል ለመፍጠር ተቸግረው ሲስተዋሉ በአንፃሩ በኤሌክትሪኮች በኩል በአጋማሹ ፍፁም ደካማ የጨዋታ ደቂቃዎችን አሳልፈዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ፀጋ ደርቤ እና ሙሴ ካበላን ወደ ሜዳ ያስተዋወቁት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች አጋማሹን ከመጀመሪያው አንፃር በተሻለ መንገድ የጀመሩ ሲሆን ኳሱን በመቆጣጠር ወደ ማጥቃት ለመሸጋገር ሙከራዎችን አድርገዋል።በተለይም ፀጋ ደርቤ እና ያሬድ የማነ በተሰለፉበት የቡድኑ የግራ መስመር በኩል በአንፃራዊነት የተሻለ ጥቃቶችን ለመሰንዘርም ጥረዋል።

በጥራት ደረጃቸው ደከም ያሉ ሙከራዎችን መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ሀዲያዎች በ59ኛው ደቂቃ ግን ሁለት አደገኛ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። በቅድሚያ ተመስገን ብርሃኑ ከተከላካይ ጀርባ ያሳለፈለትን ኳስ ሪችሞንድ አዶንጎ አስቆጠረ ተብሎ ያመከናት እንዲሁም በሰከንዶች ልዮነት ራምኬል ከሳጥን ውስጥ አክርሮ የመታው እና ፍቅሩ ወዴሳ እና የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ እጅግ አስቆጭ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ኤሌክትሪኮች በተወሰነ ቅፅበቶች የማጥቃት ሚዛኑን የወሰዱ ቢመስልም በሁለተኛው አጋማሽም በጥቅሉ ሆሳዕናዎቹ የተሻሉ ነበሩ። ነገር ግን በ85ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ሊያገኙበት የሚችሉበትን እድል አምክነዋል። ፀጋ ደርቤ በግራ በኩል ሰብሮ ወደ ውስጥ ከገባ በኋላ ያሳለፈለትን ያለቀለት ኳስ ናትናኤል ሰለሞን ወደ ግብ ቢሞክርም ኳሷን የሆሳዕናው የግብ ዘብ ፔፕ ሰይዱ በግሩም ሁኔታ ሊያድንበት ችሏል።

ያለ ግብ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ በመጀመሪያ አጋማሽ በጥንቃቄ እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ይበልጥ አጥቅተው ለመጫወት ስለመሞከራቸው ተናግረው በቀጣዩ የዕረፍት ጊዜያት ይበልጥ ተሻሽለው ስለመቅረብ እንደሚያልሙ ሲናገሩ በአንፃሩ አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ደግሞ የአጨራረስ ችግሮች ዋጋ እንዳስከፈላቸው ገልፀው በጉዳት ያላገኟቸው ተጫዋቾች አለመኖር እንደጎዳቸው ገልፀዋል።