ከፍተኛ ሊግ | የ4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች

በቶማስ ቦጋለ እና ጫላ አቤ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ትናንት እና ዛሬ በድምሩ 20 ጨዋታዎች ሲደረጉ የሦስቱም ምድቦች መሪዎች ተቀይረዋል።

የእሁድ ጨዋታዎች

የ03:00 ጨዋታዎች

በምድብ ‘ሀ’ እጅግ ብርቱ ፉክክር የታየበት እና ለተመልካች አዝናኝ በሆኑ ማራኪ የኳስ ቅብብሎች በታጀበው የሰደንዳፋ በኬ እና አቃቂ ቃሊቲ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ብዛት ያላቸው የጠሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ ሰንዳፋ በኬዎች ከቀደምት ሣምንታት እጅግ ተሻሽለው ለጨዋታው ቀርበዋል። አቃቂዎች የጨዋታውን የመጀመሪያ ፈታኝ ሙከራ 5ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ንጉሡ ጌታሁን ከፉዐድ ጀማል የተቀበለውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ቢሞክርም የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ሰንዳፋዎች በ 9ኛው ደቂቃ ጨዋታውን መምራት ሲጀምሩ መሳይ ሰለሞን ከናትናኤል አሸናፊ የተቀበለውን ኳስ በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ የባከኑ ደቂቃዎች ሲቀሩ ኪሩቤል ይጥና ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርግ የነበረው በኃይሉ ወገኔ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል የሚፈጠሩ የግብ ዕድሎችም እያነሱ መጥተዋል። 54ኛው እና 87ኛው ደቂቃ ላይም በጨዋታው ለተከላካዮች ፈተና የነበረው መሳይ ሰለሞን በግሩም አጨራረስ ተጨማሪ ሁለት ግቦች አስቆጥሮ ሐትሪክ ሲሠራ ጨዋታውም በሰንዳፋ በኬ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጅማ ላይ በተደረገው የዕለቱ ቀዳሚ የምድብ ‘ለ’ ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማ ምድቡን መምራት ያስቻለውን ድል አሳክቷል። እንጅባራ ከተማን የገጠመው ቡድኑ በአዲስዓለም ደሳለኝ ፣ አመርላ ደልታታ እና ጌትነት ተስፋዬ ግቦች 3-1 ማሸነፍ ችሏል። በዚህም ከአራት ጨዋታዎች ሙሉ 12 ነጥብ በመሰብሰብ የምድቡን መሪነት ከነቀምቴ ከተማ ተረክቧል።

ሆሳዕና ላይ የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የሆነው የዳሞት ከተማ አና የሮቤ ከተማ ጨዋታ በሮቤ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሮቤ ከተማ ከተከታታይ 3 ጨዋታ ሽንፈት በኋላ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።

ሁለት ግብ የተመለከትንበት የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ በእንቅስቃሴ ረገድ ፈጣን የሆነና በግብ ሙከራ የታጀበ ሲሆን በጨዋታው የመጀመሪያ 10 ደቂቃ የዳሞት ከተማ የበላይነት የታየበትና ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች እና የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው አጋጣሚ ይጠቀሳል። በ5ኛው ደቂቃ ሮቤ ከተማዎች ያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት  በአማን ወርቁ አማካኝነት የመጀመሪያ ግባቸውን አስቆጥረዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ሮቤ ከተማዎች ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ተጭነው በመጫወት እና ዳሞት ከተማዎች በበኩላቸው የሮቤ ከተማዎችን ጫና ለመቋቋም በማፈግፈግ የተጫወቱ ሲሆን በ13ኛው ደቂቃ ሮቤ ከተማዎች በጥሩ ቅብብል ያገኙትን ኳስ በድጋሚ በፊት መስመር ተጫዋቻቸው አማን ወርቁ በጨዋታው ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለት ግብ በማስቆጠር ሮቤ ከተማ 2-0 እዲመራ ማድረግ ችሏል። በዚህ እንቅስቃሴ ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር  ወደ መልበሻ ክፍል መግባት ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተነቃቅተው የገቡት ዳሞት ከተማዎች ውጤቱን ለመቀልበስ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን ባንፃሩ ሮቤ ከተማዎች በመጀመሪያ አጋማሽ ያስመዘገቡትን ውጤት ለማስጠበቅ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ተጫውተዋል። ዳሞት ከተማዎች ከሽንፈት ያላዳነቻቸውን ግብ በ83ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምን ሳምሶን ቁልጭ በማስቆጠር ጨዋታው በሮቤ አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።

የ05:00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ በሰበታ እና ቤንች ማጂ ቡና ጨዋታ በኳስ ቁጥጥሩ ሰበታዎች በመጠኑ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን የግብ ዕድል በመፍጠሩ በኩል ግን ቤንች ማጂዎች እጅግ የተሻሉ ነበሩ። በርካታ የግብ ዕድሎች በተፈጠሩበት ጨዋታ የመጀመሪያው የግብ ሙከራ 6ኛው ደቂቃ ላይ በአቦሎቹ ሲደረግ እሱባለው ሙሉጌታ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ትልቅ የግብ ዕድል ቢያባክንም በሁለት ደቂቃ ልዩነት ለሀሰን ሁሴን አመቻችቶ ሲያቀብል ሀሰንም በቀላሉ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ሰበታዎች የመጀመሪያውን የተሻለ ሙከራ 10ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ዮናስ ሰለሞን ከረጅም ርቀት በግሩም ሁኔታ አክርሮ የመታውን ኳስ የግቡ የላዩ አግዳሚ መልሶበታል። በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር የሚያደርጉት አቦሎቹ በተለይም በመስመር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ድንቅ ነበር። 42ኛው ደቂቃ ላይም ጄይላን ከማል ከግራ መስመር ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ያገኘው ኤፍሬም ታምሩ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ የክለቡን መሪነት አጠናክሯል።

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገው የመስመር ተጫዋቹ እሱባለው ሙሉጌታ 57ኛው ደቂቃ ላይ የግብጠባቂው መዘናጋት ተጨምሮበት ለአቦሎቹ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ሰበታዎች ጥሩ ጨዋታ ቢያደርጉም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ግን እጅግ ተቸግረዋል። ለባዶ ከመሸነፍ ያዳነቻቸውን ግብም 69ኛው ደቂቃ ላይ በገዛኸኝ ባልጉዳ ማስቆጠር ችለዋል። የጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው የአቦሎቹ ተጫዋች ዘላለም በየነ በድንቅ አጨራረስ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውም በቤንች ማጂ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱም ሰበታ ከተማን በአራቱ ሳምንታት ከ 42ቱም ክለቦች አንድም ነጥብ ያላገኘ ብቸኛው ክለብ አድርጎታል።

የምድብ ‘ለ’ የ05:00 ጨዋታ መሪ የነበረው ነቀምቴ ከተማ ሽንፈት አስተናግዷል። በጨዋታው የተሻ ግዛው 5ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ብቸኛ ጎል ደብረብርሀን ከተማን የ1-0 ድል አጎናፅፋለች።

ሆሳዕና ላይ በምድብ ‘ሐ’ የስልጤ ወራቤ እና የኮልፌ ክ/ከተማን ጨዋታ በርከት ባለ ደጋፊ ሲደገፍ የነበረው ስልጤ ወራቤ በጠባብ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። የመጀመሪያው አጋማሽ በጣም ውጥረት የተሞላበት እና ኃይል የተቀላቀለበት ጨዋታ እና ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የነበረበት ሲሆን በግብ ሙከራ ረገድ ስልጤ ወራቤ የተሻለ ሲሆን በ30ኛው ደቂቃ ሳዲቅ ሴቾ በማስቆጠር ስልጢ ወራቤ 1-0 በሆነ ውጤት እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይም ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታ እና ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ኮልፌ ክ/ከተማ ግብ ለማስቆጠር ፣ በስልጤ ወራቤ በኩል ደግሞ ውጤትን ለማስጠበቅ የተቻላቸውን ሲያደርጉ ተመልክተናል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ሰዓት አከባቢ በስልጤ ወራቤ በኩል የሰዓት ማባከን ሲስተዋል ነበር። ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ምንም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ስልጤ ወራቤን ጣፋጭ ድል አስገኝቷል። በአንፃሩ ኮልፌ ክ/ከተማ ከሦስት ተከታታይ ድል በኋላ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ቀምሷል።

የ08:00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ ቀዝቃዛ በነበረው እና በሚቆራረጡ ቅብብሎች የታጀበው የወሎ ኮምቦልቻ እና ጅማ አባ ቡና ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ 8ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ሀብቱ ከግራ መስመር ያሻማውና ሰለሞን ጌዲዮን በግንባሩ ገጭቶት የቀኙን ቋሚ ታክኮ የወጣው ኳስ በአጋማሹ የተሻለው ሙከራ ነበር።

ከዕረፍት መልስም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ሳያስመለክተን በመጠነኛ ፉክክር ሲቀጥል 69ኛው ደቂቃ ላይ የወሎ ኮምቦልቻው ሽመክት ግርማ ከረጅም ርቀት አክርሮ በመምታት ግሩም ሙከራ ቢያደርግም የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ የተሻለ ሙከራ ያልተደረገበት ጨዋታ ተቀዛቅዞ ቀጥሎ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከምሳ በኋላ ጅማ ላይ በተደረገው የምድብ ‘ለ’ ጨዋታ አምቦ ከተማ በጫላ ከበደ እና ገላን በዳዳ ጎሎች ንብን 2-0 አሸንፏል።

ሆሳዕና ላይ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የሆነው የደሴ ከተማ እና የሶዶ ከተማ ባገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የደሴ ከተማዎች የበላይነት የታየበትና በኳስ ቁጥጥሩም ተሽለው የታዩበት አጋማሽ ነበር ። ሶዶ ከተማዎች ጨዋታውን በማፈግፈግ እና ረጅም ኳስ በመጠቀም ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ታይተዋል። በ31ኛው ደቂቃ ላይ በሶዶው ግብ ጠባቂ ስህተት የተገኘችውን ኳስ በአከር ቻም አማካኝነት በማስቆጠር ደሴ ከተማን መሪ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል መግባት ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽም ምንም ግብ ያላየንበት አጋማሽ ሲሆን በጨዋታውም ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ቢታይም ሶዶ ከተማዎች ከሽንፈት ሊያድናቸውን የሚችለውን ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ማስቆጠር ተስኗቸው ሽንፈት ማስተናገድ ችለዋል። ደሴ ከተማዎችም ከእረፍት በፊት ባስቆጠሩት ብቸኛ ግብ ጣፋጭ ድል አስመዝግበው ምድባቸውን መምራት ጀምረዋል ።

የ10:00 ጨዋታዎች

በምድብ ‘ሀ’ የዕለቱ የመጨረሻ የአዲስ ከተማ እና ዱራሜ ከተማ ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር ሲታይ በአዲስ ከተማዎች በኩል ይታይ የነበረው የመጫወት ፍላጎት ከወትሮው በተለየ ተቀዛቅዞ ነበር። በተደጋጋሚ ከተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ዱራሜዎች 22ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። እስራኤል ከበደ በቀኝ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት ሲያሻማ ያገኘው አለኝታ ማርቆስ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል። ትኩረታቸውን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት አዲስ ከተማዎች ይባስ ብሎም 41ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። ከግራ መስመር መነሻውን ያደረገውን ኳስ ያገኘው አብርሃም አልዲ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ የክለቡን መሪነት አጠናክሯል።

ከዕረፍት መልስ 51ኛው ደቂቃ ላይ መሪሁን መንቴ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ወደግብ ያደረገውን ጥሩ ሙከራ የግቡ የላዩ አግዳሚ መልሶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ብዙም ጠንካራ ፉክክር ሳንመለከትበት ጨዋታው በዱራሜ ከተማ 2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የምድብ ለ የመጨረሻ ጨዋታ ሀምበርቾ ዱራሜ እና ኦሜድላን ሲያገናኝ የዳግም በቀለ የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለት ጎሎች ሀምበርቾን መሪ ሲያደርጉ ታምራት እያሱ ከዕረፍት መልስ ለኦሜድላ ያስቆጠረው ጎን ሀምበርቾን የ2-1 ከማስገኘት የመለሰ አልሆነም።

በምድብ ‘ሐ’ የዕለቱ አራተኛ ጨዋታ የሆነው አምበርቾ ዱራሜ እና ኦሜድላን ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሀምበርቾ ዱራሜ በሙሉ የበላይነት የተጫወቱ ሲሆን በአንፃሩ ኦሜድላዎች የተጋጣሚን ጨዋታ ለማበላሸት እና ረጃጅም ኳሶችን ለመጠቀም በማሰብ ተጫውተዋል። ሆኖም በ29ኛው ደቂቃ ቃልአብ በጋሻው የመታውን ኳስ በመጭረፍ ዳግም በቀለ ሀምበርቾ ዱራሜን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በ49ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ዳግም በቀለ በግንባር በማስቆጠር አንበሪቾ ዱራሜን 2-0 እንዲመራ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው በዚሁ እየቀጠለ ባለበት ሁኔታ በ73ኛው ደቂቃ ታምራት አዲሱ ግሩም የሚባል ግብ በመቀስ ምት በማስቆጠር  ለኦሜድላ የመጀመሪያውን ግብ የሆነና ውጤቱንም ወደ 2-1 ማጥበብ የቻለበት ነበር። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በአንበሪቾ ዱራሜ አሸናፊነት ተጠናቋል።

የሰኞ ጨዋታዎች

የ04:00 ጨዋታዎች

በዛሬው የምድብ ‘ሀ የመጀመሪያ ጨዋታ ሀላባ እና ባቱ ሲገናኙ በጨዋታው ባቱዎች የተሻሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ ሀላባዎች ከበፊት ሳምንቶች በወረደ የጨዋታ ስሜት ለጨዋታው ቀርበዋል። በተለይም ያልተረጋጋው የማጥቃት ክፍላቸው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግሯል። 32ኛው ደቂቃ ላይም በግራ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት አሸብር ውሮ ሲያሻማ ያገኘው እዩኤል ሳሙኤል በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ አሳዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ በርበሬዎቹ አንበላቸውን ሰዒድ ግርማ ቀይረው በማስገባት መሃል ሜዳው ላይ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ደካማ ነበሩ። ይባስ ብሎም 79ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ባቱዎች ተጫዋች ተስፋዬ በቀለ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ክንዳለም ፍቃዱ አስቆጥሮ የክለቡን መሪነት ማጠናከር ሲችል ጨዋታውም በባቱ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በተመሳሳይ ሰዓት ጅማ ላይ የተገናኙት ካፋ ቡና እና ቦዲቲ ከተማ ጨዋታቸውን ያለግብ አጠናቀዋል።

የሆሳዕናው ቀዳሚ ጨዋታ ነገሌ አርሲዎች አሰልጣኛቸውን ከቅጣት መልስ ያገኙበት የመጀመሪያ ጨዋታ እና ጅማ አባጅ ፋሮች ደግሞ አሰልጣኛቸውን ካሰናበቱ በኋላ ያደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ነበር። ጥሩ እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታ የነበረ ሲሆን በአርሲ ነገሌዎች የጨዋታ ብልጫ እና በጅማ አባ ጅፋር መልሶ ማጥቃት የታየበት እና በሁለቱም በኩል ጥሩ የሆነ የግብ ሙከራ የታጀበ የመጀመሪያ አጋማሽ ተመልክተናል። በ20ኛው ደቂቃ ከመዕዘን የተሻገረውን ኳስ ሱራፌል ፍቃዱ በማስቆጠር ጅማ አባ ጅፋርን መሪ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ነገሌ አርሲ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም በጅማ አባ ጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዮሐንስ በዛብህ አማካኝነት ማስቆጠር አልቻሉም። በ47ኛው ደቂቃ  የጅማ አባጅፋሩ አጥቂ ዳዊት ፍቃዱ ግብ በማስቆጠር መሪነታቸውን ማጠናከር ችሏል። በነጌሌ በኩል ሰለሞን ገመቹ ከፊት መስመር ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረጉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርግ የታየው አሚር አብዲ በ61ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ግብ በማስቆጠር የጅማ አባ ጅፋሮችን አሸናፊነት ማረጋገጥ ችሏል። ጅማ አባጅፋር በምክትል አሰልጣኛቸው በመመራት ርቋቸው የቆየውን ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።

የ08:00 ጨዋታዎች

በብርቱ የሜዳ ላይ ፉክክሮች እና አወዛጋቢ ትዕይንቶች በተሞላው የባህር ዳሩ ሁለተኛ የጋሞ ጨንቻ እና ቡታጅራ ከተማ ጨዋታ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ቡታጅራዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት ሲችሉ 7ኛው ደቂቃ ላይም ክንዴ አብቹ ባስቆጠራት ግብ መሪ መሆን ችለዋል። ይህ የበላይነታቸው ግን ብዙም አልቆየም ፤ የቡታጅራው ግብ ጠባቂ ሚስባ ሕያር ፍስሐ ቶማስ ላይ ጥፋት በመሥራቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምትም ራሱ ፍስሐ ቶማስ አስቆጥሮ ጋሞ ጨንቻን አቻ አድርጓል። በቀሪ ደቂቃዎች በጎዶሎ የተጫወቱት ቡታጅራዎች በጨዋታው እጅግ ሲፈተኑ በአንጻሩ ጋሞዎች በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ችለዋል። የመጨረሻ ኳሳቸው ግን ደካማ ነበር። ዳኝነት ላይ በሚነሱ ቅሬታዎች ታጅቦም አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ጋሞ ጨንቻዎች ፍጹም የበላይነቱን ሲወስዱ ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሴኮንዶች ውስጥ አማኑኤል ተፈራ ከቀኝ መስመር ያደረገው ሙከራ የላዩን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስ ከ ንክኪዎች በኋላ ያገኘው ለገሠ ዳዊት ወደግብ ሲሞክር ግብጠባቂው አስወጥቶበታል። ያንኑ ኳስ በግራ መስመር አማኑኤል ተፈራ ከማዕዘን ሲያሻማ ያገኘው ለገሠ ዳዊት አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ሲችል። በተሻለ የጨዋታ ስሜት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ጋሞዎች 82ኛው ደቂቃ ላይ ማሳረጊያውን ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ተቀይሮ የገባው ገረሱ ገላዬ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ድንቅ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በጋሞ ጨንቻ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የምድብ ‘ለ’ ሁለተኛ ጨዋታ ስድስት ግቦችን ያስተናገደ ነበር። ቂርቆስ ክፍለከተማን ከአዲስ አበባ ባገናኘው ጨዋታ ቂርቆሶች ከዕረፍት በፊት በአስናቀ ሞገስ እና ሆነልኝ ታሪኩ ከዕረፍት በኋላ ደግሞ በከድር ሳላህ እና ኡምራን ሱሊመኒ ግቦች 4-0 መምራት ችለዋል። አዲስ አበባዎች በመጨረሻ የጨዋታው ደቂቃዎች በዋለልኝ ገብሬ እና ከማል ሀጂ አማካይነት ሁለት ግቦች ቢያገኙም ውጤቱን 4-2 ከማድረግ ባለፈ ከጨዋታው ነጥብ ማግኘት አልቻሉም።

የ10:00 ጨዋታዎች

በምድብ ‘ሀ’ የመጨረሻ በነበረው እና የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ለመቀመጥ ብርቱ ፉክክር ያስተናግዳል ተብሎ በበርካቶች ዘንድ በተጠበቀው የባንክ እና ወልዲያ ጨዋታ በመጀመሪያ ደቂቃዎች የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበት ሲሆን የተሻለውን ሙከራ ለማሳየት 22 ደቂቃ ፈጅቷል። በዚህም መጣባቸው ሙሉ ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው አስወጥቶበታል። 44ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም ላንቃሞ በቀኝ መስመር በድንቅ ሁኔታ ገፍቶ በመውሰድ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው በድሩ ኑርሁሴን በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮት ወልዲያን መሪ ማድረግ ችሏል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ የዳኛ ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት ግን በግራ መስመር ላይ የነበረው አቤል ማሙሽ በግሩም ፍጥነት እና አጨራረስ ንግድ ባንክን ወደ ጨዋታው የመለሰች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ንግድ ባንኮች እጅግ ተሻሽለው ሲቀርቡ በአንጻሩ ወልዲያዎች መረጋጋት ተነስኗቸዋል። 60ኛው ደቂቃ ላይም እንዳለ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ልዑልሰገድ አስፋው በምርጥ አጨራረስ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ አድርጓል። ከግቧ መቆጠር በኋላ በሁለቱም በኩል የጠሩ የግብ ዕድሎች ሳይፈጠሩ ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2 – 1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ንግድ ባንክ በ10 ነጥብ የምድቡ መሪ መሆን ችሏል።

የምድብ ‘ለ’ የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ጂንካ ከተማን ከይርጋጨፌ ቡና ሲያገናኝ 14ኛው ደቂቃ ላይ ሥዩም ደሳሳ ያስቆጠራ ግብ ይርጋጨፌን የ1-0 ድል አጎናፅፋለች።

ሆሳዕና ላይ የዕለቱ የመጨረሻ የነበረው የገላን ከተማ እና የቡራዩ ከተማ ጨዋታ ሲሆን በጨዋታውም ቡራዩ ከተማ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ ተከታታይ ድል ማስመዝገብ ችሏል። በመጀመሪያ አጋማሽ  ጥሩ ትንቅንቅ እና አልሸነፍ ባይነት የታየበት ሲሆን ጨዋታው በጀመረ በ20 ደቂቃ የቡራዩ ከተማው የፊት መስመር ተጫዋች እንዳለማው ደሳለኝ ግሩም በሆነ አጨራረስ  ቡራዩ ከተማን አሸናፊ ያደረገች ግብ ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ጨዋታው በእንደዚህ ዓይነት መልኩ የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል መግባት ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽም በተመሳሳይ ውጥረት የበዛበት ጨዋታ ሲስተዋል ገላን ከተማ ከሽንፈት ለመዳን ጫና በማሳደር ግብ ለማግባት ሲሞክሩ ተስተውሏል። በአንፃሩ ቡራዩ ከተማ በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኘውን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አፈግፍጎ ሲጫወት ተስተውሏል። ሆኖም የገላን ከተማዎች ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ ሽንፈት ማስተናገድ ተገደዋል። ቡራዩም ጣፋጭ ሦስት ነጥቡን በተከታታይ ማሳካት ችሏል።