ሪፖርት | 30 ሙከራዎች የተስተናገዱበት ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል

ጥሩ ፉክክር የተደረገበት የፋሲል ከነማ እና ወልቂጤ ከተማ ፍልሚያ 0ለ0 በሆነ ውጤት ተደምድሟል።

በ12ኛ ሳምንት ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያዩት ፋሲል ከነማዎች በአሰላለፋቸው ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ የዛሬውን ፍልሚያ ሲቀርቡ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ከመቻል ጋር አንድ ለአንድ የተለያዩት ወልቂጤ ከተማዎች በበኩላቸው ተስፋዬ መላኩን በብርሃኑ ቦጋለ እንዲሁም አስራት መገርሳን በማቲያስ ወልደአረጋይ ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ከጅምሩ ጥሩ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ10ኛው ደቂቃ መሪ ሊያገኝ ነበር። በዚህም የተከላካይ አማካዩ ይሁን እንዳሻው ወደ ኋላ አቀብላለው ብሎ ያሳጠረውን ኳስ ጌታነህ ከበደ ደርሶበት ለአቡበከር ሳኒ ቢያመቻችለትም አቡበከር በወረደ አጨራረስ ወርቃማውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ወልቂጤዎች ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ከቀኝ መስመር ሌላ አጋጣሚ በየኋላሸት ሰለሞን አማካኝነት ፈጥረው ነበር።

የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የሞከሩት ፋሲሎች በተለይ በራሳቸው ሜዳ የሚፈፅሟቸው የቅብብል ስህተቶች ራሳቸው ላይ አደጋ እንዲጋብዙ እያስገደዳቸው ነበር። በዚህ ሂደት በ18ኛው ደቂቃ መናፍ ዐወል የተሳሳተውን ሌላ ኳስ ጌታነህ ተቀብሎት በድጋሜ ለአቡበከር ቢሰጠውም የመስመር አጥቂው ይህንንም አጋጣሚ መጨረሻውን ማሳማር ሳይችል ቀረ እንጂ ሊመሩ ነበር። ይህ ቢሆንም በ21ኛው ደቂቃ በአጋማሹ የመጀመሪያ እና የመጨረሻ የሆነው ሙከራቸውን አድርገው ተመልሰዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ሱራፌል ያሻማውን የመዓዘን ምት አምሳሉ ጥላሁን በግንባሩ ለመጠቀም ጥሮ ግብ ጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራ በጥሩ ቅልጥፍና መልሶታል።

ወደ ጎል በመድረሱ ረገድ አሁንም የተሻሉት ወልቂጤ ከተማዎች በ38ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከቀኝ መስመር ከአፈወርቅ ኃይሉ የደረሰውን ኳስ መሬት ለመሬት ሞክሮት ቀዳሚ ለመሆን ጥረዋል። በተቃራኒው ፋሲሎች በጨዋታው እምብዛም የጠሩ ዕድሎችን መፍጠር ተስኗቸው ከብቸኛው የ21ኛ ደቂቃ ሙከራ ውጪ አንድም ስል ጥቃት ሳይሰነዝሩ ቀርተዋል። አጋማሹም ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በወልቂጤ ከተማ ጥቃት የተሟሸ ነበር። በ47ኛው ደቂቃ ተመስገን በጅሮንድ ከጌታነህ ከበደ የተቀበለውን ኳስ ሳጥኑ መግቢያ ላይ ሆኖ ቢሞክረውም ዒላማውን ስቶበታል። በማጥቃትም ሆነ በመከላከል ወቅት ሲቸገሩ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው በ55ኛው ደቂቃ ሱራፌል ራሱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት በመጠቀም ቀጣዩን ሙከራ አድርገዋል። በ58ኛው ደቂቃ ደግሞ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርግ የነበረው አቡበከር በወልቂጤ በኩል የአጋማሹን የጠራ እና ሦስተኛ ሙከራ አድርጓል።

በአንፃራዊነት በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በማጥቃቱ ረገድ መሻሻል ያሳዩት ፋሲሎች በ68ኛው ደቂቃ አምሳሉ ጥላሁን ከግራ መስመር ወደ ግብ ልኮ አግዳሚው በመለሰበት አጋጣሚ ሮበርትን ፈትነዋል። በ79ኛው ደቂቃ ደግሞ የመሐል ተከላካዮቹ በተዘናጉበት ቅፅበት ናትናኤል መናፍ ያሻማውን ኳስ በመጠቀም የፈጠረውን ዕድል ራሱ ናትናኤል እና ዓለምብርሃን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ዓለምብርሃን ለማሻማት በሚመስል መልኩ የመታው ሌላ ኳስ መረብ ላይ ለማረፍ ከጫፍ ቢደርስም ንቁ የነበረው ሮበርት ወደ ውጪ አውጥቶታል። ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታውም ያለ ግብ አቻ ፍፃሜውን አግኝቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የፋሲል ከነማው አሠልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ቡድናቸው በመነሳሳት እና በማጥቃቱ ረገድ ጥሩ እንዳልነበር ጠቅሰው በድሬዳዋ የገጠማቸው የውጤት ማጣት ጫና ቢፈጥርም ጫና ውስጥ ሆኖ መጫወት ይባስ ውጤት እያበላሸባቸው እንደሆነ ተናግረዋል። የወልቂጤ ከተማው አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸው በማጥቃቱ አጨዋወት ደስተኛ ቢሆኑም አለመጠቀማቸው ግን እንዳሳዘናቸው አመላክተው የድሬዳዋ ቆይታቸው ጥሩ የሚባል እንደሆነና ማሸነፍ የሚገባቸውን ጨዋታዎች አለመርታታቸው ብቻ ቅር እንዳሰኛቸው ተናግረዋል።