በጭማሪ ደቂቃ የተቆጠረችው የዮናታን ኤልያስ ጎል ወላይታ ድቻ ከሀዋሳ ከተማ ጋር አቻ እንዲለያይ አድርጋለች።
ከድል መልስ ምሽት ላይ የተገናኙት ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ሦስት ነጥብ ካሳኩበት የ12ኛ ሳምንት ፍልሚያ በቅደም ተከተል ሁለት እና አንድ ተጫዋቾችን ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በለውጦቹም ወላይታ ድቻ ከድሬዳዋው ጨዋታ ዘላለም አባቴን በቃልኪዳን ዘላለም እንዲሁም መሳይ ኒኮልን በሀብታሙ ንጉሴ ሲተካ ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ ከኤሌክትሪኩ መርሐ-ግብር ዳዊት ታደሠን ብቻ በብርሃኑ አሻሞ ለውጦ ጨዋታውን ቀርቧል። ይህ ጨዋታ ገና በ21 ሰከንዶች ውስጥ ሁለት አስደንጋጭ ሙከራዎች ተደርገውበታል። በቅድሚያ የወላይታ ድቻው አጥቂ ስንታየሁ መንግስቱ ጨዋታውን እንዲጀምር የተሰጠውን ዕድል በቀጥታ አክርሮ በመምታት ፈጣኑን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርግ ከሰከንዶች በኋላ ደግሞ እዮብ አለማየሁ ከግብ ጠባቂ የተላከውን ኳስ በተመሳሳይ ከርቀት ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ነበር።
በአንፃራዊነት የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሳቸው አድርገው ሲጫወቱ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች ጠጣሩን የድቻ የኋላ መስመር በቀላሉ ማስከፈት ባይችሉም ከርቀት ሙከራ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። በ16 እና 19ኛው ደቂቃም በተጠቀሰው መልኩ ሁለት ተከታታይ ጥቃቶችን አድርገዋል። በተለይ የቡድኑ አምበል ዳንኤል ደርቤ የሞከረው ሁለተኛ ኳስ በተሻለ ለግብነት የቀረበ ነበር። በቀጣዩ ደቂቃ ግብ አስቆጥረው ከጨዋታ ውጪ በሚል የተሻረባቸው ወላይታ ድቻዎች በ29ኛው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶባቸዋል። በዚህም ኤፍሬም አሻሞ ደጉ ደበበ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ በመምታት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።
ወላይታ ድቻዎች ግብ ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ መጣራቸውን ቀጥለዋል። በ40ኛው ደቂቃም አበባየሁ ሀጂሶ በሞከረው ኳስ አቻ ሊሆኑ ነበር። አጋማሹ ሊገባደድ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ግን ዓሊ ሱሌይማን ከእዮብ አለማየሁ በተቀበለው ኳስ ሁለተኛ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር።
ሁለተኛው አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች በተሻለ ወደ ፊት ጠጋ በማለት የሀዋሳን የግብ ክልል መጎብኘት የያዙበት ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ሀዋሳ ከተማ የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ አድርጓል። በዚህም በ50ኛው ደቂቃ አብዱልባሲጥ ከማል በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከነበረው እዮብ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ የቡድኑን ሁለተኛ ጎል ለማስገኘት ተቃርቦ ነበር። ከዚህ ሙከራ በኋላ ግን ወላይታ ድቻ ሦስት ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን ፈጥረዋል።
በቅድሚያ በ58ኛው ደቂቃ በረጅሙ የተመታን ኳስ ስንታየሁ የመጀመሪያውን ፍልሚያ አሸንፎ ሲጨርፈው ቃልኪዳን ዘላለም ለመጠቀም ጥሮ ዒላማውን ስቶበታል። ከደቂቃ በኋላም ይሁ አጥቂ በተራው ለስንታየሁ የግብ ዕድል ፈጥሮ ቁመታሙ አጥቂ በወረደ አጨራረስ መረብ ላይ ሳያሳርፈው ሲቀር በ63ኛው ደቂቃ ደግሞ ቃልኪዳን ከግራ የሳጥኑ ክፍል ሌላ ዕድል ፈጥሮ ተከላካዮች አምክነውበታል።
በዚህ አጋማሽ ጫናዎች የበረከተባቸው ኃይቆቹ ጨዋታውን ቶሎ ለመግደል በ70ኛው ደቂቃ ሙከራ አድርገው ነበር። በዚህም ቸርነት አውሽ ከዳንኤል ደርቤ የተረከበውን ኳስ ሞክሮት የነበረ ቢሆንም ወደ ውጪ ወጥቶበታል። አሁንም የአቻነት ግብ ፍለጋ የታተሩት የጦና ንቦቹ በ81፣ 82 እና 83ኛው ደቂቃ አበባየሁ ሀጂሶ፣ ዮናታን ኤሊያስ እና ደጉ ደበበ በሞከሯቸው ተከታታይ ኳሶች አስደንጋጭ ጥቃት ፈፅመዋል። ከሁሉም በላይ ግን ሙሉ የጨዋታ ክፍለጊዜው መገባደጃ ላይ ቃልኪዳን የተከላካዮችን የትኩረት ማነስ እና የግብ ጠባቂውን የወረደ ውሳኔ በመጠቀም የፈጠረው አጋጣሚ በድቻ በኩል አስቆጪ ነበረች። ይህ ቢሆንም በጭማሪው ደቂቃ አቤኔዘር ኦቴ ኳስ በእጅ ነክቶ የተሰጠን የቅጣት ምት በኃይሉ ተሻገርን ቀይሮ የገባው ዮናታን ኤሊያስ በድንቅ ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎት ቡድኑን አቻ አድርጓል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
የወላይታ ድቻው አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በመጀመሪያው አጋማሽ በሀዋሳ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በሁለተኛው አጋማሽ ባደረጉት ለውጥ እስከ መጨረሻው በትዕግስት ተጫውተው አንድ ነጥብ ማግኘታቸውን ጠቅሰው አጠቃላይ እንቅስቃሴው ተመጣጣኝ እንደሆነ ገልፀዋል። የሀዋሳ ከተማው አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው ባለቀ ሰዓት የተሰጠባቸው የቅጣት ምት እንዳላሳመናቸው አመላክተው ኳሱን ተቆጣጥረው እንደመጫወታቸው ማሸነፍ እንደሚገባቸው አስረድተው በብስለት ጨዋታውን መጨረስ ይገባቸው እንደነበር ሲገልፁ ተደምጧል።