የ13ኛ የጨዋታ ሳምንት አራተኛ ቀን መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልኩ ቀርበዋል።
ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር በሰንጠረዡ ሁለት ፅንፎች የሚገኙትን ለገጣፎ ለገዳዲዎችን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኛል።
በሊጉ ከ11 ጨዋታዎች በኋላ በ6 ነጥብ የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኙት አዲስ አዳጊዎቹ ለገጣፎ ለገዳዲዎች እስካሁን ባስቆጠራቸው(7) ሆነ በተቆጠሩባቸው የግብ ብዛትን(24) ለተመለከተ ቡድኑ ስለምን በግርጌ እንደተገኘ በሚገባ ያረዳል። በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ እጅግ ደካማ የሆነው ቡድኑ ነገሮች በፈለገው መንገድ እየሄዱለት አይደለም።
ባለልምዱን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ከቀናት በፊት ወደ ሀኃላፊነት አምጥተው የነበሩት ለገጣፎዎች አሰልጣኙ ግን የመጨረሻ ጨዋታቸውን በስታዲየም ታድመው እንዲሁም ለቀናት ልምምድ ካሰሩ በኋላ እስካሁን ግልፅ ባልሆነ ምክንያት የክለቡን ሆቴል ለቀው ወደ አዲስ አበባ ላይመለሱ የመምጣታቸውን ነገር ከቀናት በፊት ተሰምቷል። ይህን ተከትሎ አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ ዳግም በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ቡድናቸውን እንደሚመሩም ይጠበቃል።
በተጫዋቾች አደራደር ረገድ ወደ ዝርግ 4-4-2 የተጠጋ ቅርፅን ወደ መጠቀም የመጣ የሚመስለው ቡድኑ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ኳሶችን በማሸነፍ ለመጫወት ከፍተኛ ጥረቶችን ሲያደርጉ ብንመለከትም አሁንም ግን የማሸነፊያ መንገዱን ለማግኘት ተቸግረዋል።
በለገጣፎዎች በኩል እስካሁን በስድስት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ተሳትፎ ያደረገው ኢብሳ በፍቃዱ ፍፁም ደካማ በሆነው የቡድኑ ማጥቃት ላይ ተስፋ እየፈነጠቀ ይገኛል። ቡድኑ በመጨረሻ ካስቆጠራቸው ሦስት ግቦች ሁለቱን ማስቆጠር የቻለው አጥቂው ለገጣፎ ካለበት ስጋት ለማውጣት ከእሱ ብዙ ይጠብቃሉ። ለገጣፎዎች በነገው ጨዋታ ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት የፀዳ ስብስብን ይዘው ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።
የነገውን ግጥሚያን ጨምሮ ሁለት ጨዋታ በእጃቸው የሚገኘው ፈረሰኞቹ አሁን ላይ በ22 ነጥብ ከመሪው ኢትዮጵያ መድን በ4 ነጥብ ርቀው በሁለተኛ ደረጃ ቢገኙም ሁለቱን ጨዋታዎች በድል መወጣት ከቻሉ ወደ አንደኝነት የሚመለሱ በመሆኑ የዚህ ጨዋታ ድል አስፈላጊያቸው ነው።
ከተጋጣሚያቸው በተቃራኒ በሊጉ 24 ግቦችን በማስቆጠር ሆነ 7 ግቦችን ብቻ በማስተናገድ በሁለቱም መመዘኛዎች ምርጥ መሆናቸውን እያሳዩ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ነገው ጨዋታ ሲመጡ ከ16 ቀናት እረፍት በኋላ ነው። በእነዚህም ቀናት የተወሰነ እረፍት ለተጫዋቾቹ ሰጥቶ የነበረው ቡድኑ ላለፉት ቀናት በቢሾፍቱ ዝግጁቱን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ይህ እረፍት ቡድኑ ከጨዋታ ቅኝት እንዳያወጣው ግን ስጋቶች አሉ።
በፈረሰኞቹ በኩል ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ የነበሩት ዳዊት ተፈራ ፣ ሻሂዱ ሙስጠፋ ፣ ተመስገን ዮሐንስ ከጉዳታቸው በተሻለ መንንገድ እያገገሙ የሚገኝ ቢሆንም ለነገው ጨዋታ ግን እንደማይደርሱ ሲረጋገጥ በተመሳሳይ አማካዩ ጋቶች ፓኖም በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል።
10 ሰዓት ላይ ጅማሮውን የሚያደርገውን ጨዋታ ተፈሪ አለባቸው በዋና ዳኝነት ፣ ፍቅሬ ወጋየው እና አያሌው ማንደፍሮ በረዳትነት ፣ ባሪሶ ባላንጎ በአራተኛ ዳኝነት በጋራ ይመሩታል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና
የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ሁለት ድልን አጥብቀው የሚሹቱትን አርባምንጭ ከተማን ከሲዳማ ቡና ያገናኛል።
በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመሩት አርባምንጭ ከተማዎች ከ11 ጨዋታዎች በኃላ በ12 ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ቡና 2-0 ከተረቱበት ጨዋታ በኋላ ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ምንም ዓይነት ሽንፈት ያላስተናገዱት አርባምንጭ ከተማዎች በዚህ ሂደት አዳማን ከረቱበት ጨዋታ ውጭ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ግን ነጥብ መጋራት ችለዋል። በሊጉ እስካሁን ካደረጓቸው ጨዋታዎች ስድስቱን(54.54%) በሚሆኑት ነጥቦችን በመጋራት የደመደመው ቡድኑ አቻዎችን ወደ ድል መቀየር መጀመር ይኖርበታል።
ከአምና የቡድኑ ስኬት በስተጀርባ ቁልፍ ሚናን የተወጣው የቡድኑ አማካይ መስመር ዘንድሮ ላይ ግን በቀደመው ልክ ለመሆን የተቸገረ ይመስላል። የተለያዩ ጥምረቶችን እየተጠቀሙ የሚገኙት አርባምንጮች ከአማካይ መስመራቸው ዕድሎችን በመፍጠር ሆነ ለተከላካዮች ሽፋን በመስጠት ረገድ የሚጠብቁትን ግልጋሎት ከዚህ ክፍል እያገኙ አይገኝም።
ከዚህ ባለፈ ቡድኑ ከጨዋታ ጨዋታ ወጥ የሆነ ብቃት ለማሳየት የመቸገሩ ጉዳይም ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞም ቡድኑ ጥሩ በሚሆንባቸው የጨዋታ ደቂቃዎች ላይ ጨዋታዎችን መግደል ያለመቻሉ ጉዳይ ቡድኑን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል። አርባምንጮች በነገው ጨዋታ ከጉዳት ነፃ የሆነውን ስብስባቸውን ይዘው ይቀርባሉ።
በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ እየተመሩ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች 11 ጨዋታዎችን አድርገው በሰበሰቧቸው 11 ነጥቦች በወራጅ ቀጠና ውስጥ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ከጨዋታ ጨዋታ ፍፁም የተደበላለቀ ውጤት እያስመዘገቡ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች የመከላከላቸው ጉዳይ ግን እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ቀጥሏል።22 ግቦችን ያስተናገደው ቡድኑ አሁንም ከግለሰባዊ ሆነ መዋቅራዊ ስህተቶች መላቀቅ ያለመቻሉ ጉዳይ ግን በጣም አስጊ እውነታ ነው።
አነጋጋሪ በነበረው የባህር ዳር ከተማው ጨዋታ ቡድኑ ምንም እንኳን በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በሁለተኛው አጋማሽ ያሳዩት ጥረት እና አልሸነፍ ባይነት ስሜት ለአዲሱ የቡድኑ አሰልጣኝ ስዮም ከበደ ግን ጥሩ መነሻ የሚሆን ይመስላል። በመሆኑም ቡድኑ በቀጣይ ጨዋታዎች በባህር ዳሩ ጨዋታ በሁለተኛ አጋማሽ ያሳዩትን መንፈስ ከጨዋታዎች ጅማሬ አንስቶ ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።
በነገው ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች ከመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት በኃላ በጉዳት ምክንያት አጥተውት የነበረውን ሰልሀዲን ሰዒድን ዳግም ከጉዳት መልስ የሚያገኙት ሲሆን
በተቃራኒው ፀጋዬ አበራ ፣ አማኑኤል እንዳለ እና ሙሉቀን አዲሱ ግን በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።
ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም በሊጉ 16 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ጨዋታ (10) በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ሲሆን ከተቀሩት 6 ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ 4 እንዲሁም ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ 2 ጊዜ ባለድል መሆን ችለዋል።
የምሽቱን መርሃግብር ዳንኤል ግርማይ በመሀል ዳኝነት ፣ አማን ሞላ እና ባደታ ገብሬ ረዳት ዳኞች እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ አራተኛ ዳኛ ሆነው ይመሩታል።