ሪፖርት | ፈረሰኞቹ የድሬዳዋ ቆይታቸውን በጎል ተንበሽብሸው ጨርሰዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ በፍጹም የበላይነት ለገጣፎ ለገዳዲ ላይ የ4-0 ድል ተቀዳጅቷል።

10፡00 ላይ የለገጣፎ ለገዳዲ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ሲደረግ ለገጣፎዎች በ12ኛው ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር 1-1 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ኪሩቤል ወንድሙ ፣ መዝገቡ ቶላ እና አማኑኤል አረቦ በታምራት አየለ ፣ አንስዋር መሐመድ እና ያብቃል ፈረጃ ተተክተው ገብተዋል። የ12ኛ ሳምንት ጨዋታቸው በይደር የተያዘላቸው ፈረሰኞቹ በ11ኛው ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያለ ምንም ግብ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በተመሳሳይ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ሄኖክ አዱኛ ፣ ምኞት ደበበ እና ናትናኤል ዘለቀ የአማኑኤል ተርፉ ፣ ሱለይማን ሃሚድ እና ጋቶች ፓኖምን ቦታ ተክተው ገብተዋል።

አስደናቂ አጀማመር ያደረጉት ፈረሰኞቹ የለገጣፎ ተጫዋቾችን ዝግጁ አለመሆን ተጠቅመው በአራት ንክኪ ብቻ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። መሃል ሜዳ ላይ አጎሮ ያስጀመረውን እና ፍሪምፖንግ ሜንሱ በረጅሙ ያሻማውን ኳስ ያገኘው ቀኝ መስመር ላይ የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል ሲያሻማ ሳጥን ውስጥ በፍጥነት የተገኘው ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በግንባሩ በመግጨት ክለቡን መሪ አድርጓል ፤ ግቧ 9ኛው ሴኮንድ ላይ ነበር የተቆጠረችው።

በፍጹም የጨዋታ ብልጫቸው የቀጠሉት ፈረሰኞቹ በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ሲችሉ 15ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ያገኘው ቢኒያም በላይ በግንባሩ በመግጨት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡ የላዩ አግዳሚ መልሶበታል። 21ኛው ደቂቃ ላይም ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቸርነት ጉግሳም ያደረገው ሙከራ የግቡን የግራ ቋሚ ተጠግቶ ወጥቶበታል።

ባልተደራጀ እና በተቆራረጡ ቅብብሎች የታጀበ አጨዋወት የቀጠሉት ለገጣፎዎች የመጀመሪያውን ሙከራቸውን 23ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። ኢብሳ በፍቃዱ በግሩም ዕይታ አመቻችቶ ያቀበለው ኳስ የደረሰው አማኑኤል አረቦ እጅግ ደካማ በሆነ አጨራረስ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። በአንድ ደቂቃ ልዩነትም ኢብሳ በፍቃዱ ከግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ጋር ተገናኝቶ ተጨማሪ የግብ ዕድል አባክኗል። ከዚህ ሙከራ በኋላም የጥላሁን ተሾመ ተጫዋቾች በመጠኑም ቢሆን ተነቃቅተው ታይተዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች የማጥቃት ኃይላቸውን ያለማቋረጥ ሲቀጥሉ ከለገጣፎ ለገዳዲ ተጫዋቾች ስህተት ከተገኘ ኳስ በቸርነት ጉግሳ እና ሀይደር ሸረፋ የጠሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። 44ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም በላይ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ ለቡድን አጋሮቹ ሲያቀብል ቸርነት ጉግሣ በጥሩ ቴክኒክ ሳይነካ የተወውን ኳስ ያገኘው ሀይደር ሸረፋ ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የላዩ አግዳሚ መልሶበታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ሀይደር ሸረፍ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ኦሮ አጎሮ በቀኙ የሳጥኑ ክፍል ይዞት ገብቶ በደካማ እግሩ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ወደ ውጪ አስወጥቶበታል። ያንኑ ኳስ ቢንያም በላይ በግራ መስመር ከማዕዘን ሲያሻማ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ የግብ ጠባቂው የጊዜ አጠባበቅ ስህተት እና የኪሩቤል ወንድሙ ኳሱን በትክክል አለማውጣት ተጨምሮበት ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 56ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ሄኖክ አዱኛ ሲያሻማ ያገኘው ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ሲያጠናክር ውጤት የመቀልበስ ስሜት የጠፋባቸው እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚታይባቸው ለገጣፎዎች በጨዋታው መቸገራቸውን ቀጥለዋል።

ይባስ ብሎም 72ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። ሀይደር ሸረፋ ከተጋጣሚ ሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በሽር ደሊል መልሶበታል። ከአንድ ደቂቃ በኋላ ጣፎዎች በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራቸውን ሲያደርጉ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ለማቀበል ሲሞክር በሰራው ስህተት ኳሱን ያገኘው በጨዋታው የተሻሉ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክር የሚታየው ኢብሳ በፍቃዱ ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መልሶበታል።

74ኛው ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ በጥሩ ቅብብል ወደፊት የወሰዱትን ኳስ ሃይደር ሸረፋ ለቸርነት ጉግሣ ሲያቀብል ቸርነት በተረጋጋ አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላም በሁለቱም በኩል ተጨማሪ የግብ ዕድሎችን ሳያስመለክተን ጨዋታው በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታው ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የለገጣፎ ለገዳዲው አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ የተጫዋቾቻቸው ትኩረት ማነስ ግብ እንዲቆጠርባቸው ምክንያት እንደሆነ በተጨማሪም የልምድ ማነስና ግብ ለማስቆጠር ያለው መጓጓት ድክመቻቸው እንደሆነ ሲገልጹ የተሻሉ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው በመቀላቀል ተሻሽለው ለመቅረብ እንደሚሞክሩ ተናግረዋል። የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው በተዘጋጁት ልክ ጨዋታውን እንደጀመሩት እና በጥቂት ንክኪዎች ከዚህ በፊትም ግብ እንዳስቆጠሩ እና በልምምድ ወቅት የሚሠሩት እንደሆነ በተጨማሪም የሚያባክኑት ኳስ ላይ ሥራ እንደሚጠብቃቸው ገልጸዋል።