ሪፖርት | አርባምንጭ እና ሲዳማ ፍፁም ተቃራኒ በነበሩ አጋማሾች ነጥብ ተጋርተዋል

ማራኪ ፉክክር ያስመለከተን የምሽቱ የአርባምንጭ ከተማ እና ሲዳማ ቡና የ13ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ 3-3 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሲዳማ ቡና ከባህር ዳር ከተማ ጋር በመጨረሻው ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታው በሦስት ቀዳሚ ጀማሪዎች ላይ ለውጥን አድርጓል። በዚህም አንተነህ ተስፋዬ ፣ ሙሉቀን አዲሱ እና አቤኔዘር አስፋውን በማስወጣት ጊት ጋትኩት ፣ አበባየው ዮሐንስ እና ጉድዊን ኦባጄ ተክቷል። አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር በተመሳሳይ ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት አሰላለፍ አንፃር ይስሀቅ ተገኝ እና በላይ ገዛኸኝን በአቤል ማሞ እና ተመስገን ደረሰ ለውጠዋል።

ተቀራራቢ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የሚገኙትን ሁለቱን ክለቦች ያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ በረጃጅም ኳስ ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደመጀመሩ ጎልን ያስመለከተን ከዚሁ የጨዋታ እንቅስቃሴ ገና በጊዜ ነበር። 5ኛው ደቂቃ ላይ በግራ የሲዳማ የግብ አቅጣጫ መሀሪ መና ሙና በቀለ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት ራሱ ሙና ወደ ጎል ሲያሻማው የሲዳማ ቡና የተከላካይ ክፍል የአቋቋም ስህተት ታክሎበት አህመድ ሁሴን ከመሀል አፈትልኮ ወጥቶ በግንባር ኳስ እና መረብን በማገናኘት አዞዎቹን መሪ አድርጓል።

ረጃጅም እና ከመስመር የሚሻገሩ ኳሶች የበዙበት ቢሆንም ኳስን በራሳቸው ቁጥጥር ስር አድርገው መጫወትን ሲዳማ ቡናዎች ምርጫቸው ቢያደርጉም በቅብብል ወቅት የሚፈጥሩት ስህተቶች ለአርባምንጭ ከተማ ተጫዋቾች አመቺ ሆኖላቸው ታይቷል። ከቆመ ኳስ ፍሬው አሻምቶ መሀሪ ተፈጥሯዊ ባልሆነ እግሩ መትቶ አቤል ማሞ በቀላሉ የያዘበት ሙከራ የቡድኑ የመጀመሪያዋ ሙከራ ነበረች። የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ከሚሰሩት ስህተት በተጨማሪ ከተሻጋሪ ኳሶች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ትጋት ያልተለያቸው አርባምንጮች የሲዳማን ተከላካዮች ለሁለተኛ ጊዜ ተጠቅመው ሁለተኛ ግባቸውን ወደ ካዝናቸው አስገብተዋል። 17ኛ ደቂቃ ላይ አምበሉ ወርቅይታደስ አበበ በረጅሙ ከራሱ የግብ ክልል በረጅሙ የጣለውን ኳስ አህመድ ሁሴን በግንባር ገጭቶ ያቀበለውን ተመስገን በተመሳሳይ በግንባር ወደ ጎልነት ለውጧታል።

ሁለተኛ ጎልን ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት እጅጉን ተቸግረው መታየት የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች አሁንም የሚታይባቸውን ስህተት ማረም ባለመቻላቸው ሦስተኛ ጎል አስተናግደዋል። በዚህም አጋማሹ ሊጠናቀቅ አራት ያህል ደቂቃዎች እየቀሩት ኢማኑኤል ላርዬ ከአህመድ ጋር ተቀባብሎ ከቀኝ የሲዳማ ቡና የግብ አካባቢ ወደ ሳጥኑ ሲያሻግር ተመስገን ደርሳው ወደ ጎል ሲሞክር ያኩቡ ተደርቦ ኳሷ ስትመለስ ቡጣቃ ሻመና አግኝቷት በቀጥታ ወደ ጎልነት ቀይሮ በአርባምንጭ የ3-0 ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ በመጀመሪያው አጋማሽ በተጋጣሚያቸው ብልጫ ተወስዶባቸው የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች እንዳለ ከበደ እና አበባየሁ ዮሐንስን አስወጥተው ቡልቻ ሹራን እና ይስሀቅ ከኖን ተክተው ካስገቡ በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ በይበልጥ በማጥቃት ተሳተፎን በማድረግ በተጋጣሚያቸው ላይ ጫናን ማሳደር ጀምረዋል።

ከቀዳሚው አጋማሽ እንቅስቃሴያቸው መቀዛቀዞች በጉልህ የተንፀባረቀባቸው እና በመከላከሉ ረገድ የወረደ ተሳትፎን ያደርጉ የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች 54ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ከመረባቸው አርፏል። መሀሪ መና ከግራ አቅጣጫ ወደ ውስጥ አሻምቶ አቤል ማሞ በአግባቡ ባለ መቆጣጠሩ የለቀቀውን ኳስ ይገዙ ደርሶት ቡድኑን ወደ ጨዋታ መልሷል።

ኳስን የመቆጣጠር ድርሻው በሲዳማ ቡና ሊወሰድባቸው ግድ የሆነባቸው አርባምንጮች ተመስገን ደረሰ እና መሪሁን መስቀሌን በአሸናፊ ኤልያስ እና አቡበከር ሻሚል ለውጠው ባስገቡ በሰከንዶች ልዩነት ሁለተኛ ግብን ለሁለተኛ ጊዜ በአቤል ማሞ ስህተት ተቆጥሮባቸዋል። መነሻዋን ከሙሉዓለም መስፍን ያደረገች ተሻጋሪ ኳስ ጉድዊን ኦባጄ በግንባር ጨርፎ ያቀበለውን ይገዙ ቦጋለ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎልን አክሎ ሲዳማን በይበልጥ ወደ ጨዋታው መልሷል።

የሲዳማን ተሻጋሪ ኳሶችም ሆነ የሚመጣባቸውን ጥቃቶች ለመሰንዘር ከደቂቃ ደቂቃ ድክመቶቻቸው እያየሉ የመጡባቸው አርባምንጮች በ22 ደቂቃዎች ሦስተኛ ጎል ከመረብ አርፎባቸው አቻ ሆነዋል። መሀሪ መና በአንድ ሁለት ቅብብል ያገኘውን ኳስ ነፃ ቦታ ላይ ለተገኘው ቡልቻ ሹራ አቀብሎት ተጫዋቹም ቡድኑን 3-3 ያደረገች ግብ አስገኝቷል። ሳይጠበቅ ወደ አቻነት የመጡት አርባምንጮች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አሸንፎ ለመውጣት በአሸናፊ እና አህመድ አማካኝነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ጨዋታው 3-3 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ተጋጣሚያቸው በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ እንደነበሩ እና በመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች የሚቆጠሩባቸው ጎሎች አሁንም መቅረፍ እንዳልቻሉ በተከላካይ ስህተትም ጎል እንደ ተቆጠረባቸው ገልፀው በዕረፍት ሰዓት መልበሻ ቤት ውስጥ ውጤቱ እንደሚቀለበስ ተነጋግረው ገብተው በመጨረሻም በለፉት ልክ እንዳገኙ ተናግረዋል። የአርባምንጭ ከተማው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም እየመሩ ጎል እንደገባባቸው ጠቁመው በቡድናቸው ላይ ጎል ሲቆጠር ቡድኑ እንደሚረበሽ እና ሦስት ጎሎችን አስቆጥረው መርተው ማስጠበቅ እየተቻሉ አቻ መሆናቸው በሥነ ልቦና ክፍተት የመጣ በመሆኑ ቡድኑ በዚህ ረገድ ማደግ እንዳለበት ጠቁመው የዛሬውን ጨዋታ እንደተሸንፉ እንደሚቆጥሩት በመናገር ሀሳባቸውን አክለዋል።