ያለፉትን ሳምንታት በጊዜያዊ አሰልጣኞች ሲመራ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በቋሚነት አሰልጣኞችን ሾሟል።
በ2014 ከከፍተኛ ሊግ ተሳትፎው ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዳግም የመሳተፍ ዕድልን አግኝቶ በያዝነው የውድድር ዓመት በሀገሪቱ ትልቁ ሊግ ላይ እየተካፈለ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአሳዳጊ አሰልጣኙ ክፍሌ ቦልተና ጋር እስከ ስምንተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ድረስ ቆይቷል። ሆኖም ውጤቱ ያልሰመረለት ክለቡ ከአሰልጣኙ ጋር በመለያየት ክለቡን በረዳት አሰልጣኝነት ሲመሩ የነበሩትን ገዛኸኝ ከተማ እና በክለቡ የቴክኒክ ቡድን ውስጥ የነበረውን ስምዖን አባይን ጊዜያዊ ዋና እና ረዳት አሰልጣኝ በማድረግ ቀጣዮቹን አምስት ጨዋታዎችን እንዲመሩ አድርጓል። አሁን ደግሞ የክለቡ ቦርድ ባደረገው ስብሰባ ሁለቱን አሰልጣኞች በይፋ ዋና አሰልጣኝ እና ረዳት በማድረግ በቋሚነት ስለመሾሙ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ እጅጉ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
በሊጉ ካደረጋቸው አስራ ሦስት ጨዋታዎች በ8 ነጥቦች 15ኛ ላይ የተቀመጠው ክለቡ ቀሪ የዓመቱን ጨዋታዎች በተሻለ ውጤት አጠናቆ በሊጉ ለመቆየት ያልማል።