ከመጫወቻ ሜዳ አለመመቸት ጋር ተያይዞ ተራዝመው የነበሩት የ7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ እና ሰኞ ሲደረጉ የሳምንቱን መጨረሻ ሁለት ፍልሚያዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰባስበናል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከፋሲል ከነማ
ያለፉትን ሁለት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች በተመሳሳይ የአቻ ውጤት ፈፅመው ነገ የሚገናኙት ሀዲያ እና ፋሲል ከረጅሙ የሊጉ እረፍት በፊት ድል አድርገው በቅደም ተከተል 3ኛ እና 5ኛ ደረጃን መያዝን እያሰቡ የሚያደርጉት ፉክክር ተጠባቂ ነው።
ሳይጠበቅ በደረጃ ሰንጠረዡ የላይኛው ፉክክር የተገኘው ሀዲያ ሆሳዕና አጠቃላይ ያለበት ቁመና የሚደነቅ ቢሆንም ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች በወጥነት አዎንታዊ ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም ፤ ከስድስቱ ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ነው ያሳካው። እርግጥ ቡድኑ ያጋጠመው የተጫዋቾች ጉዳት፣ ህመም እና ቅጣት ለዚህ ዋነኛውን ድርሻ ቢወስድም በእነዚህ ወረድ ያለ ብቃት ባሳየባቸው ስድስት ጨዋታዎች ግን ከአንድ ጊዜ በላይ አለመረታቱ ደግሞ መልካም የሚባል ነው። ይህ ቢሆንም ግን ባሳለፍነው ሳምንት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር በእንቅስቃሴ ደረጃ ተሽሎ በአጨራረስ ድክመት ብቻ ያመከናቸው በርከት ያሉ ኳሶች ወደ አናቱ በደንብ እንዳይጠጋ እንዳደረገው ይታመናል።
በደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ቦታ የሚገኘው ፋሲል ከነማ በውጤትም ሆነ በእንቅስቃሴ ረገድ እየተጓዘበት ያለው መንገድ ደጋፊዎቹን እያስደሰተ አይገኝም። ሦስት ነጥብ ካገኘ አራት ጨዋታዎች ያለፉት ቡድኑ በማጥቃትም ሆነ በመከላከል ያለበት ክፍተት በጨዋታዎች ተፅዕኖ እንዳያሳርፍ እያደረገው ነው። በተለይ በማጥቃቱ ረገድ ያለው አጨዋወት እና አፈፃፀም ለተጋጣሚ ተከላካዮች እጅግ ቀላል እየሆነ የመጣ ሲሆን ባለፉት አራት ጨዋታዎችም ከአንድ በላይ ግብ ማስቆጠር አልቻለም። ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ከውጤት መጥፋት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ጫና እንደሆነ አሠልጣኙ በተደጋጋሚ ሲገልፁ የሚሰማ ሲሆን የነገ ተጋጣሚያቸው በጥብቅ መከላከል የሚታወቅ ስለሆነ ድል ለማግኘት ይህንን ጫና አራግፈው በተሻለ ቁመና መገኘት የግድ ይላቸዋል።
ድሬዳዋ ላይ በምትከሰተዋ የደንጊ በሽታ የተነሳ ብርሀኑ በቀለ እና ፀጋዬ ብርሀኑን በነገው ጨዋታ የማያገኘው ሀዲያ በተጨማሪም ቤዛ መድህንን በጉዳት ባዬ ገዛኸኝን ደግሞ በቅጣት አይሰለፉም። እንዳለ ደባልቄ እና መለሰ ሚሻሞ ግን ከጉዳታቸው መመለሳቸው ተጠቁሟል። በፋሲል ከነማ በኩል ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ የራቀው ሀብታሙ ተከስተ ብቻ በጨዋታው ተሳትፎ አያደርግም።
ቡድኖቹ ነገ በሊግ ታሪካቸው ለአምስተኛ ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን ከዚህ ቀደም በተደረጉት አራት ጨዋታዎች ፋሲል ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ቀሪውን ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ፋሲል ስድስት ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ሦስት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።
ይህን ጨዋታ ዳንኤል ግርማይ በመሀል ዳኝነት ሲመራው ሰብስቤ ጥላዬ እና ኤልያስ መኮንን በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በአራተኛ ዳኝነት ተሳትፎ ያደርጋሉ።
አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና
እኩል አስራ አራት ነጥቦችን በመያዝ በግብ ክፍያ ብቻ ተበላልጠው አስራ አንደኛ እና አስራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና በምሽቱ ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይታመናል።
ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ብቻ በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ የሊጉ ጨዋታዎች በድምሩ የሰበሰባቸውን ውጤቶች ያገኘው አዳማ ከተማ ከነበረበት የውጤት ድባቴ የወጣ ይመስላል። እርግጥ ድል ማሳካት ባልቻለባቸው ጨዋታዎችም ለትችት የሚዳርገው ነገር ባያስመለክትም በስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች 17 ነጥቦችን ጥሎ ወደ አሸናፊነት መንገድ መምጣቱ መልካም የሚባል ነው። ባሳለፍነው ሳምንት በተከናወነው የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ደግሞ በጊዜ ግብ በማስቆጠር በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በነፃነት ተጫውቷል። በነገው የተስተካካይ ፍልሚያም ይህንን ድል ደግሞ ወደ መቀመጫ ከተማው የሚያደርገውን ጉዞ ለማሳመር ይንቀሳቀሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ክረምት ላይ ከአሠልጣኝ ቅጥር ጀምሮ በርካታ ተጫዋቾችን አስፈርሞ አዲስ የቡድን ግንባታ የጀመረው ኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዓመቱ በቀላሉ እየተከወነለት አይገኝም። ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፈው ክለቡ ከዋና አሠልጣኙ ተመስገን ዳና ጋር ተለያይቶ የ13ኛ ሳምንት ጨዋታውን ቢያደርግም ሦስት ነጥብ ማግኘት አልቻለም። ቡድኑ በጨዋታው ሽንፈት ቢያስተናግድም ባለፉት ጨዋታዎች የነበረበት የተነሳሽነት ችግር በመጠኑ ተቀርፎ ነበር። በማጥቃቱም ረገድ የነበረው ውህደት እድገት አሳይቶ ከተጋጣሚው የበለጠ ሙከራዎችን በጨዋታው ሰንዝሯል። ይህ ቢሆንም ግን ከኳስ ውጪ በተለይ ከማጥቃት ወደ መከላከል ያለው ሽግግር መርዘም ለተጋጣሚ ምቹ እየሆነ ነው። ከዚህ የጨዋታ ምዕራፍ በተጨማሪም የቀኝ መስመሩ ዋነኛ መጠቂያው ስለሆነ ትኩረት ሰጥቶ ሊያሻሽለው ይገባል።
አዳማ ከተማ ነገም የዳዋ ሁቴሳ፣ ሰዒድ ሀብታሙ እና ፍሬድሪክ አንሳህን ግልጋሎት አያገኝም። ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አስራት ቱንጆ እና አማኑኤል ዮሐንስ ከጉዳታቸው እያገገሙለት ቢሆንም በነገው ጨዋታ እንደማይጠቀምባቸው ተመላክቷል።
የአንድ ሰዓቱ ጨዋታ በተፈሪ አለባቸው የመሀል ዳኝነት ሲከወን ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ክንዴ ሙሴ እና ባደታ ገብሬ በረዳትነት መለሠ ገብሬ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት እገዛ እንዲሰጡ ተመድበዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 40 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 22 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አዳማ ከተማ በበኩሉ 7 ጊዜ ድል ሲቀናው በ11 ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። በሁለቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ቡና 70 ፤ አዳማ 35 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
ነገ እና ከነገ በስትያ የሚደረጉት ተስተካካይ ጨዋታዎች የዲ ኤስ ቲቪ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንደማይኖራቸውም ተጠቁሟል።