በቻን ውድድር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በምድብ 1 የተደለደለችው ሊቢያ በውድድሩ የምትጠቀማቸውን ተጫዋቾች ስታሳውቅ ዝግጅቷንም ቱኒዚያ ላይ ታደርጋለች።
የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮን ሺፕ በጥር ወር በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር አልጄሪያ እንደሚደረግ ይታወቃል። በዚህ ውድድር ለሦስተኛ ጊዜ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከትናንት በስትያ የ28 ተጫዋቾችን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን በዚሁ ምድብ የምትገኘው ሞዛምቢክም በውድድሩ ላይ ግልጋሎት አገኝባቸዋለው ያለቻቸውን ተጫዋቾች እንደለየች ዘግበን ነበር። አሁን ደግሞ ሌላኛዋ ሀገር ሊቢያ 26 ተጫዋቾችን መምረጧ ታውቋል።
በሚያዚያ ወር ሀቪየር ክሌመንትን ተክተው የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ የሆኑት ፈረንሳዊው ጎልማሳ ኮረንቲን ማርቲንስ በዚህ ውድድር ላይ የሚጠቀሙባቸውን አራት ግብ ጠባቂዎች፣ ስምንት ተከላካዮች፣ ስምንት አማካዮች እና ስድስት አጥቂዎች በድምሩ ሀያ ስድስት ተጫዋቾች ይፋ አድርገዋል። እነዚህ ተጫዋቾች ከትናንት በስትያ የተጀመረው የ9ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጠናቀቁ እንደሚሰባሰቡ የተገለፀ ሲሆን ማክሰኞም ወደ ቱኒዚያ አምርተው ከውድድሩ በፊት የ16 ቀን ዝግጅት የሚያደርጉ ይሆናል። በዚህ የዝግጅት ጊዜም ከማሊ እና ሱዳን ጋር ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ለማድረግ ቀጠሮ መያዙ ተመላክቷል።
በተያያዘ የቻን ዜና በዚሁ ምድብ የሚገኘው እና የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው አልጄሪያ ለውድድሩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተሰናዳ ይገኛል። የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ባሳለፍነው ወር ለሁለት ሳምንታት ያክል በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ዝግጅቱን አድርጎ ከሶሪያ (1-0 ድል)፣ ሴራ ሊዮን (3-0 ድል) እና ኩዌት (1-0 ሽንፈት) ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርጎ ወደ ሀገሩ የተመለሰ ሲሆን ሀገር ቤት ደግሞ 28 ተጫዋቾችን በመያዝ በሜዳው ከሞሪታኒያ (0-0) እና ሴኔጋል (2-2) ጋር ተጨማሪ ጨዋታዎችን ከውኗል።
በሌላ የውድድሩ ዜና ደግሞ ካፍ ከስፖርት ትጥቅ አምራች አጋሩ አምብሮ ጋር በመሆን በትናንትናው ዕለት ከስር የተቀመጠውን የውድድሩን መጫወቻ ኳስ ይፋ አድርገዋል።