ዛሬ በከፍተኛ ሊጉ 9 ጨዋታዎች ሲደረጉ ነቀምቴ ከተማ እና ሀምበርቾ ዱራሜ ወደ መሪነት መጥተዋል።
የ04:00 ጨዋታዎች
ባህር ዳር ላይ አቃቂ ቃሊቲ ከ ቤንች ማጂ ቡና በተገናኙበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም በኩል በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ፉክክር ቢያደርጉም የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን እጅግ ደካማ ነበሩ። ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀርብ 58ኛው ደቂቃ ላይ የአቃቂው በኃይሉ ወገኔ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ማዕሩፍ መሐመድ ያደረገውን ሙከራ የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞታል።
ቤንች ማጂዎች በተረጋጋ አጨዋወት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ 74ኛው ደቂቃ ላይ ጄይላን ከማል ረጅም ርቀት ላይ ከተገኘ የቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው አስወጥቶበታል። ያንኑ ኳስ ጅብሪል ናስር በግራ መስመር ከማዕዘን ሲያሻማ ያገኘው ሀሰን ሁሴን በግንባሩ በመግጨት ግብ ለማስቆጠር ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል። የማጥቃት ሚዛናቸውን በኃይሉ ወገኔ ላይ የደፉት አቃቂዎች ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም ፈታኝ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ ተስተውሏል። 87ኛው ደቂቃ ላይም ሙሉዓለም በየነ ተቀይሮ በገባ በአምስት ደቂቃ ውስጥ በተረጋጋ አጨራረስ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በቤንች ማጂ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ጅማ ላይ በምድብ ‘ለ’ ቀዳሚ ጨዋታ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሀን ተከታታይ ድል ያሳካበትን ሦስት ነጥብ አግኝቷል። እንጅባራ ከተማን የገጠመው ቡድኑ ገናናው ረጋሳ 2ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁም ሀብታሙ ረጋሳ 82ኛ ደቂቃ ላይ ባስቆጠሯቸው ግቦች ነው 2-0 ያሸነፈው።
በምድብ ‘ሐ’ ሆሳዕና ላይ የተገናኙት ሮቤ ከተማ እና ሥልጤ ወራቤ ጨዋታቸውን 1-1 በሆነ ውጤት ጨርሰዋል። ወንድምአገኝ ታደሰ ሮቤን በ17ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ቢያደርግም የሥልጤ ወራቤው አብዲ ራህመቶ 32ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑን አቻ አድርጓል። የጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
የ08:00 ጨዋታዎች
በምድብ ‘ሀ’ ሁለተኛ ጨዋታ በሰበታ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ መካከል ብርቱ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ ወሎ ኮምቦልቻዎች ገና በሁለተኛው ደቂቃ መሪ ሊሆኑ ነበር። ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ያገኘው ሰለሞን ጌድዮን በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል። ሰበታዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ውስጥ የነበረው ኪዳኔ አሰፋ አመቻችቶ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ገዛኸኝ ባልጉዳ አስቆጥሮት በድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ኮምቦልቻዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር የተሻለ ተጭነው ሲጫወቱ 23ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል በለጠ ጨርፎ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሰለሞን ጌድዮን ደካማ በሆነ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በሁለቱም በኩል ረፍት የለሽ እንቅስቃሴ መደረግ ሲቀጥል አጋማሹ ሊጠናቀቅ የዳኛ ፊሽካ ሲጠበቅ የኮምቦልቻው ሀብታሙ ወርቁ ወደግብ የሞከረውን ኳስ የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል። በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ ከግራ መስመር ያገኙትን የማዕዘን ምት አዳነ ተካ ሲያሻማ በጨዋታው ዕድለኛ ያልነበረው ሰለሞን ጌዲዮን በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም በድጋሚ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ኮምቦልቻዎች የበላይነቱን ወስደዋል። ሰበታዎች ጨዋታውን በማረጋጋት ውጤቱን ለማስጠበቅ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በተደጋጋሚ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ወሎዎች በጨዋታው 95ኛ ደቂቃ ላይ አቻ መሆን ችለዋል። ተቀይሮ የገባው ፋሲል ተስፋዬ ድንቅ የቅጣት ምት ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ጅማ ላይ ከምሳ በኋላ በተደርረገው ጨዋታ ነቀምቴ ከተማ ምድቡን ወደ መምራት የተመለሰበትን ድል በንብ ላይ አሳክቷል አሳክቷል። ቦና ቦካ ፣ ምኞት ማርቆስ እና ቦና ቦካ የነቀምቴን ግቦች ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ሲሆኑ ጨዋታው በነቀምቴዎች 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በምድብ ‘ሐ’ የተደረገው የኮልፌ ክፍለከተማ እና ደሴ ከተማ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል። በዚህም ሁለቱም ቡድኖች በማሸነፍ ምድቡን መምራት ይችሉ የነበረበትን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
የ10:00 ጨዋታዎች
በምድብ ‘ሀ’ የመጨረሻ ጨዋታ ባቱ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲገናኙ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ሲደረግ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ግን ባቱዎች የተሻሉ ነበሩ። 23ኛው ደቂቃ ላይ የባቱው ተስፋዬ በቀለ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ያገኘው ዮናታን አንባዬ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና መልሶበታል። ጨዋታው የዳኛን ውሳኔ ባለመቀበል በሚደረጉ ጭቅጭቆች ታጅቦ ሲቀጠል ወደ ዕረፍት ሊያመሩ በተጨመሩ ደቂቃዎች ውስጥ የባቱው ፍፁም ዓለማየሁ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።
ከዕረፍት መልስ ከተጠበቁት በላይ ተሻሽለው የቀረቡት አሳዎቹ 58ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። እንዳለ ዘውገ ኳሱን ለመቆጣጠር ሲሞክር ኳሱን በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አሸብር ውሮ ማስቆጠር ችሏል። የተጋጣሚን ቡድን በቁጥር ማነስ ያልተጠቀሙት ንግድ ባንኮች በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራ ያደረጉት 61ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን አቤል ማሙሽ የግብጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከፍ አድርጎ የሞከረው ኳስ የግቡን የላዩ አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል።
ከዚህ ሙከራ በኋላም በሁለቱም በኩል የጠሩ የግብ ዕድሎች ሳይፈጠሩ ጨዋታው በባቱ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም ጨዋታውን የመሩት ዳኞች በተለይም ዋና ዳኛ ሙሉቀን ያረጋል ከተመልካቾች አድናቆት ተችሯቸዋል።
የሳምንቱ የምድብ ‘ለ’ ጨዋታ በቦዲቲ ከተማ እና ጂንካ ከተማ መካከል የተደረገ ነበር። በውጤቱም ቦዲቲ በናትናኤል ዳንኤል እና አቦነህ ገነቱ ግቦች 2-0 መርታት ችሏል።
ሆሳዕና ላይ በተደረገው የምድብ ‘ሐ’ የመጨረሻ ጨዋታ ገላን ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን 2-0 ረቷል። በየነ ባንጃ እና አፍቅሮት ሰለሞን ለገላን ከተማ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ሆነዋል።