የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቻን የምድብ የመጀመሪያ መርሐ-ግብር ከሞዛምቢክ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ በአንድ ቀን መገፋቱ ይፋ ሆኗል።
2009 ላይ የተጀመረው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮን ሺፕ ውድድር ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር አልጄሪያ እንደሚደረግ ይታወቃል። በ18 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የሚደረገው ይህ ውድድር ከጥር 5 እስከ 27 ድረስ በአራት የሀገሪቱ ከተሞች የሚደረግ ይሆናል። የውድድሩ አዘጋጅ ካፍ ከአስተናጋጁዋ ሀገር ጋር በጋራ የደመቀ ሥነ-ስርዓት እንዲኖር ሥራዎችን እየሰራ ሲሆን በአራቱ ከተሞች የሚገኙት አራት ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞችም የውድድሩን መጀመር እየተጠባበቁ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
መጀመሪያ በወጣው መርሐ-ግብር መሠረት በምድብ አንድ ከአልጄሪያ፣ ሞዛምቢክ እና ሊቢያ ጋር የተደለደለችው ሀገራችን ኢትዮጵያ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ጥር 5 እንደምታደርግ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም አሁን ይፋ በሆነ መረጃ ጥር 5 የመክፈቻው ሥነ-ስርዓት እንዲሁም በአልጄሪያ እና ሊቢያ መካከል የሚደረገው የውድድሩ የመጀመሪያ ጨዋታ ብቻ እንደሚደረግ ተጠቁሟል። ይህንን ተከትሎ በዚህ ቀን እንዲደረግ ታስቦ የነበረው የኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ ጨዋታ በቀጣዩ ቀን ጥር 6 በባራኪ እንዲከወን አዲስ መርሐ-ግብር ወጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ ጨዋታዎች የሚያደርግበት ቀን
* ጥር 6 ከሞዛምቢክ
* ጥር 9 ከአልጄሪያ
* ጥር 13 ከሊቢያ
የውድድሩ ሙሉ መርሐ-ግብር ከሥር በምስል ተያይዟል 👇