የግብ ሙከራዎች ባልበረከቱበት የ7ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና እና ፋሲል ከነማ ፍልሚያቸውን በአቻ ውጤት አገባደዋል።
በ13ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያለ ግብ የተለያየው ሀዲያ ሆሳዕና ፍሬዘር ካሣን በቃለአብ ውብሸት እንዲሁም ራምኬል ሎክን በፀጋዬ ብርሃኑ ተክቶ ወደ ሜዳ ሲገባ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ተመሳሳይ ውጤት አስመዝግቦ ለዛሬው ጨዋታ የቀረበው ፋሲል ከነማ በበኩሉ ይሁን እንዳሻው እና ሀብታሙ ገዛኸኝን አሳርፎ አቤል እያዩ እና ታፈሰ ሰለሞንን ወደ ሜዳ አስገብቷል።
ያለ ዋና አሠልጣኛቸው ኃይሉ ነጋሽ ወደ ሜዳ የገቡት ፋሲል ከነማዎች የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ሰንዝረዋል። በዚህም ሱራፌል ዳኛቸው ከመሐል ሜዳ የላከውን ኳስ የመስመር ተከላካዩ ሔኖክ አርፊጮ በሚገባ መቆጣጠር ሳይችል ሽመክት ጉግሳ ደርሶበት ለአለምብርሃን ይግዛው ያመቻቸለት ሲሆን አለምብርሃንም አጥብቆ የመታው ኳስ መዳረሻው መረብ ሊሆን ሲል የግብ ዘቡ ፔፔ ሰይዶ እንደምንም ወደ ውጪ አውጥቶታል። ለዚህ ጥቃት አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ያሰቡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከመልስ ውርወራ የተገኘን ኳስ በመጠቀም ሪችሞንድ ኦዶንጎ በደረቱ በማብረድ በሞከረው ኳስ በራሳቸው በኩል የመጀመሪያውን ጥቃት ሰንዝረዋል።
በጅምሩ ሁለት ጥሩ ሙከራዎችን ያስመለከተን ጨዋታው እስከ 25ኛው ደቂቃ ሌላ ሙከራ አላስተናገደም። እስከ ተጠቀሰው ደቂቃ ፋሲል ከነማዎች በተሻለ ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ቢያስቡም የቅብብሎቻቸው ስኬት የወረደ መሆኑና ሂደቱ እስከመጨረሻው ያልጠበቀ በመሆኑ አደጋ መፍጠር አልቻሉም። በአንፃሩ የተሻለ ብልጫ ወስደው ጫና ለማሳደር ተሻጋሪ እና ረጃጅም ኳሶችን ማዘውተር የያዙት ሀዲያዎች በ25ኛው ደቂቃ ብርክ ማርቆስ ከርቀት አክርሮ በመታው የቅጣት ምት ኳስ ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። በ33ኛው ደቂቃ ደግሞ ታፈሰ ሰለሞን በተቃራኒ አቅጣጫ ሌላ ሙከራ አድርጎ በግብ ጠባቂው ወጥቶበታል። አጋማሹም ያለ ግብ ተጠናቋል።
የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ የባሰ ግልፅ ዕድሎች የተፈጠሩበት አይደለም። ኳስም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ቶሎ ቶሎ ስትቆራረጥ የነበረ ሲሆን በተደራጀ ሁኔታ የተደረገ የማጥቃት እንቅስቃሴ አልተስተዋለም። ከዚህ ባለፈም አጥቂዎችን በአጭሩ ለማግኘት የሚደረጉ የረጃጅም ኳሶች ምት በተደጋጋሚ ሰደረግ ነበር።
ከጫና የመነጨ በሚመስል መልኩ የተረጋጋ እና የተናበበ አጨዋወት መከተል የተሳናቸው ፋሲሎች አሁንም ከኳስ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ቢያስቡም ሦስተኛው የሜዳ ሲሶ በቀላሉ መግባት አልቻሉም። በአንፃራዊነት ሽመክት ጉግሳ ቦታዎችን እየቀያየረ ለቡድኑ አንዳች ነገር ለማግኘት ቢጣጣርም ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻለም። ሀዲያዎች በአንፃሩ ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥተው ግባቸው እንዳይደፈር እየጠቀሩ በመልሶ ማጥቃት የሚፈጠሩ ዕድሎችን መጠባበቅ ይዘዋል።
ቡድናቸውን እየመሩ የሚገኙት ምክትል አሠልጣኙ ሙሉቀን በመጨረሻዎቹ የጨዋታው ደቂቃዎች የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በመለወጥ አንዳች ነገር ለማግኘት ሞክረዋል። ነገርግን በ88ኛው ደቂቃ ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበው ነበር። በዚህም ሀዲያ ከላይ በጠቀስነው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ፀጋዬ ብርሃኑ ለፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ያቀበለው ኳስ ለቡድኑ በአጋማሹ ለግብነት የቀረበች አጋጣሚ ብትሆንም ፍቅረየሱስ በወረደ አጨራረስ አምክኖታል። ጨዋታውም የወረደ ፉክክር አስመልክቶ ያለ ግብ ተደምድሟል።