ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ይርጋጨፌ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል

በሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ8ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ይርጋጨፌ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ ወሳኝ ነጥብ ሲያገኙ አዲስ አበባ እና ልደታ በበኩላቸው ነጥብ ተጋርተዋል።

ይርጋጨፌ ቡና በአዳማ ከተማ ላይ የበላይነት በወሰደበት የረፋዱ ጨዋታ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ታግዞ ወሳኝ የሆነ ሶስት ነጥብን አግኝቷል።

በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ የማጥቃት ፍላጎት በማሳየት ጫና መፍጠር የጀመሩት ይርጋጨፌዎች የአዳማን የቅብብል መንገድ በማቋረጥ ረጃጅም እና ወደ መስመር በሚጣሉ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር በእጅጉ ጥረዋል። 44ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ሲደርስም በዕለቱ ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ዳግማዊት ሰለሞን የፈጠረችላትን ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅማ መስታወት አመሎ ግብ አስቆጥራ የአሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ቡድን መሪ ሆኗል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ቀጥሎ ከመጀመሪያው አጋማሽ የይርጋጨፌ ቡና የበላይነት ወደ ተመጣጠነ ፉክክር አድልቷል። መሀል ሜዳ ላይ በሚደረጉ ቅብብሎች አዳማ ከተማዎች ወደ አቻነት ለመምጣት ቢጥሩም ሁነኛ አጥቂ አለመኖሩ ዋጋ ሲያስከፍላችው ታዝበናል። ይሁን እንጂ ረጃጅም ኳስን በዚህኛው አጋማሽም ሲጠቀሙ የነበሩት ይርጋጨፌዎች 55ኛ ደቂቃ ላይ በዳግማዊት ሰለሞን ጎል ወደ 2ለ0 ተሸጋግረዋል። ሁለት ጎል ካስተናገዱ በኋላ በተለይ የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው መንቀሳቀስን የመረጡት አዳማ ከተማዎች ተቀይራ በገባችው ሄለን እሸቱ አማካኝነት ጎል ቢያስቆጥሩም ተጨማሪ ግብን ማከል ባለመቻላቸው የዓመቱ ስድስተኛ ሽንፈትን በይርጋጨፌ ቡና አስመዝግበዋል።

ሁለቱን የመዲናይቱን ክለቦች አዲስ አበባ ከተማ እና ልደታ ክፍለ ከተማን ያገናኘው የሳምንቱ አምስተኛ ጨዋታ ነጥብ በመጋራት ተጠናቋል።

ሜዳ ላይ ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክርን ያሳዩን ቡድኖቹ ከሙከራዎች ይልቅ የመረጡት የጨዋታ መንገድ አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች የተገደቡ እና የሚቆራረጡ እንደ ነበር አስተውለናል። የሆነው ሆኖ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት 15ኛው ደቂቃ ላይ ቤቴልሄም መንተሎ ጎል አስቆጥራ አዲስ አበባን ቀዳሚ አድርጋለች። ጨዋታው ጥሩ እና ሳቢ በሆነ መልኩ ቀጥሎ 35ኛው ደቂቃ ላይ አሰልጣኝ ፍቅሬ ቢሆነኝ ባደረገው አፋጣኝ ቅያሪ ወደ ሜዳ የገባችው ሜሮን አበበ ጎል በማስቆጠር ልደታን አቻ አድርጋለች። ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ቀጥሎ ቡድኖቹ አሸንፎ ለመውጣት የተጫዋች ለውጥ ጭምር አድርገው ቢገቡም ግብ ሳያስቆጥሩ 1ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

የሳምንቱ የማሳረጊያ መርሐ-ግብር የሆነው የአርባምንጭ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በበርካታ ተመልካቾች እና ዝናባማ በነበረ አየር ታጅቦ 10 ሰዓት ላይ ጀምሯል። የአርባምንጭ ከተማን የግብ ሙከራ እና አጠቃላይ የጨዋታ ብልጫ ያስመለከተን ሙሉ ደቂቃው አርባምንጮች ከወትሮ የረጃጅም ኳስ አጠቃቀማቸው በዚህኛው ጨዋታ ኳስን በመቆጣጠር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ለመግባት ሲጥሩ ተመልክተናል። በአንድ ሁለት ቅብብል 10ኛው ደቂቃ ላይ ትውፊት ካዲኖ በግምት ከ30 ሜትሮ ርቀት ጎል በማስቆጠር አርባምንጭን መሪ አድርጋለች። ተደጋጋሚ ፈጣን የኳስ ንክኪን እያደረጉ ማጥቃታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት አርባምንጭ ከተማዎች 28ኛው ደቂቃ ላይ በመሠረት ወርቅነህ አማካኝነት ሁለተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል።

አርባምንጭ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ የአጨዋወት መንገዳቸው መልቀቅ ባይችሉም በሁለተኛው አጋማሽ በድሬዳዋ እጅጉን ተፈትነዋል። በ71ኛው ደቂቃም ፎዚያ መሐመድ ለድሬዳዋ ጎል አስቆጥራ ቡድኗን ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥራለች። አርባምንጭ ከተማዎች ግብ ካስተናገዱ በኋላ ሶስተኛ ጎልን አስቆጥረው የነበረ ቢሆንም የዕለቱ ሁለተኛ ረዳት ዳኛ በአወዛጋቢ መልኩ ኳሷን ሽራው ጨዋታው በመጨረሻም 2ለ1 በሆነ የእንስት አዞዎቹ ድል ተጠናቋል።