ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ወደ ድል ተመልሷል

የ7ኛ ሳምንት ተስተካካይ የኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በቡናማዎቹ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ ቡና ባለፈው ጨዋታ ላይ በመድን ካስተናገደው ሽንፈት በሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን አድርጓል። ወልደአማኑኤል ጌቱን በኩዋኩ ባህ ፣ ሔኖክ ድልቢን በአብዱልሀፊዝ ቶፊክ ሲተኩ ድሬዳዋን ከረታው ስብሰባቸው አንፃር አዳማ ከተማዎች አድናን ረሻድ በዊሊያም ሰለሞን ብቸኛ ቅያሪያቸው አድርገው ለጨዋታው ቀርበዋል።

ጨዋታውን የዕለቱ ዳኛ ተፈሪ አለባቸው አስጀምረው አንድ ደቂቃ ብቻ እንደተቆጠረ ጎል አስመልክቶናል። ጨዋታውን ኢትዮጵያ ቡናዎች አስጀምረውት የአዳማ ከተማ ተከላካዮች ጋር ኳስ ደርሳ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች ከግብ ክልላቸው በአግባቡ ኳስን ማፅዳት ባለመቻላቸው አማካዩ አብዱልሀፊዝ ቶፊክ በፍጥነት ነጥቋቸው ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው አጥቂው ብሩክ በየነ ሰጥቶት ተጫዋቹም በጥሩ የአጨራረስ ቅልጥፍና በሳጥን ውስጥ የደረሰውን ኳስ ወደ ጎልነት ለውጦ ቡናማዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። 

ግብ ካስተናገዱ በኋላ አዳማ ከተማዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ በይበልጥ በኢትዮጵያ ቡና ላይ ጫናን ለማሳደር በግብ ክልላቸው አካባቢ መድረስ ቢችሉም ግልፅ የሆኑ አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ ረገድ ግን ደካሞች ነበሩ።

ጎል ቀድመው ማስቆጠራቸው የጠቀማቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች የኋላ መስመራቸውን በሚገባ በመዝጋት ጥንቃቄ አዘል የጨዋታ መንገድ መርጠው በፈጣን መልሶ ማጥቃት ሽግግር የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ ተጨማሪ ጎልን ለማግኘት ጥረቶችን ሲያደርጉ ተስተውሏል። አዳማ ከተማዎች 24ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ከግቡ ትይዩ የተገኘን የቅጣት ምት አቡበከር ወንድሙ መቶ ግብ ጠባቂው ሕዝቄል ሞራኬ አድኖበታል። ኳስን ይዘው የተሳካ ቅብብሎችን ባያደርጉም ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛ ክፍል ለመግባት በእጅጉ ድክመት የሚታይባቸውን አዳማ ከተማዎች ሁለተኛ ጎል ተቆጥሮባቸዋል።

ከእንቅስቃሴ አንፃር በተጋጣሚያቸው ላይ ያን ያህል ብልጫን ባያሳዩም መሀል ሜዳውን በአግባቡ ተቆጣጥሮ በተነሳሽነት ሲጫወቱ በመስተዋሉ 36ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ የአዳማ የግብ አካባቢ ኢትዮጵያ ቡናዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ኃይለሚካኤል አደፍርስ አሻምቶ የደረሰውን ኳስ በተከላካዮች መሀል የተገኘው መሐመድኑር ናስር በግንባር ገጭቶ ከመረብ በማገናኘት ኢትዮጵያ ቡና አጋማሹን 2-0 በሆነ ውጤት ማጠናቀቅ እንዲችል አስችሎ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ አዳማ ከተማዎች ፈጣን ቅያሪን በማድረግ ጀምረዋል። በዚህም አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ አማኑኤል ጎበና ፣ አቡበከር ወንድሙ እና ቢኒያም አይተንን በማስወጣት ዮሴፍ ታረቀኝ ፣ አድናን ረሻድ እና አብዲሳ ጀማል በምትኩ ወደ ሜዳ ጀምረዋል። ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ድል ያደረጉት አዳማ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ከወትሮ አጨዋወታቸው የታየባቸውን የጨዋታ ክፍተት ለማረም ያለመ እንቅስቃሴን አድርገዋል። 58ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ውስጥ የገቡት አዳማ ከተማዎች ተቀይሮ በገባው አጥቂ አብዲሳ ጀማል አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራን አድርገው ግብ ጠባቂው ሕዝቄል ሞራኬ መልሶበታል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ጎሎችን ለማስተናገድ የተገደዱት አዳማዎች በአጋማሹ ጎሎችን በተጋጣሚ መረብ ላይ ለማሳረፍ ያላሰለሰ የማጥቃት ትጋትን ማድረግ ቢችሉም የቡናን የተከላካይ ክፍል አስከፍቶ ለመግባት ውስንነቶች ይንፀባረቅባቸው ነበር። ሁለት ጎሎችን በጊዜ ወደ ካዝናቸው የከተቱት ቡናማዎቹ በጥልቅ መከላከል መስፍን ታፈሰ እና መሀመድኑር ናስርን ላይ ያነጣጠሩ ተሻጋሪ ኳሶችን እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን ተጠቅሞ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረትን አድርገዋል። ከአዳማ ከተማ በተሻለ ከጎል ጋር የመቆራኘት ዕድላቸው በጨዋታው የሰፋላቸው ቡናማዎች 75ኛ ደቂቃ ሦስተኛ ግባቸውን አግኝተዋል። በመልሶ ማጥቃት የተገኘን ኳስ አብዱልከሪም ወርቁ በጥሩ ዕይታ ያሻገረለትን ከተከላካዮች መሀል መሀመድኑር ናስር አፈትልኮ ወጥቶ ጋናዊው ግብ ጠባቂ ክዋሜ ባህ ባጠበበት ቦታ መሬት ለመሬት መትቶ ከመረብ አዋህዶ የጎል መጠኑን ወደ ሦስት ከፍ አድርጓል።

አዳማ ከተማዎች በመጨረሸዎቹ ደቂቃዎች የማስተዛዘኛ ጎልን ለማግኘት በተለይ በአብዲሳ ጀማል አማካኝነት አግኝተው የነበረ ቢሆንም ጨዋታው በቡናማዎቹ የ3-0 ድል አድራጊነት ተደምድሟል።

ያጋሩ