መረጃዎች | 52ኛ የጨዋታ ቀን

ሊጉ በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት ወደ እረፍት ከማምራቱ በፊት የሚደረጉትን ሁለት ተስተካካይ የ7ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፍ ቀርበዋል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ወላይታ ድቻ

የዕለቱ ቀዳሚው መርሃግብር የዝውውር መስኮቱን እየተጠባበቁ የሚገኙትን ለገጣፎ ለገዳዲዎችን የድሬዳዋ ቆይታቸውን በድል ማጠናቀቅ ከሚያስቡት ወላይታ ድቻዎች ያገናኛል።

በስድስት ነጥቦች በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ለገጣፎ ለገዳዲዎች አሰልጣኝ ጥላሁን ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ አሰቃቂ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ እንዳረጋገጡት በሁለተኛው ዙር ተሻሽሎ ለመቅረብ የክለቡ አመራሮች ስብስባቸው በጥራት ለማሳደግ ጥረቶች ስለመጀመራቸውን ተናግረዋል።

በብዙ መመዘኛዎች ከሊጉ ፍላጎት አንፃር በቂ በሚባል ደረጃ ላይ የማይገኘው ቡድኑ በአሁናዊ የሰንጠረዡ አቀማመጥ መሰረት ከ13ኛ ደረጃ በ7 ነጥብ ርቀው ይገኛሉ በመሆኑም ይህን ርቀት ለማጥበብ መስኮቱን እየተጠባበቀ የሚገኘው ቡድኑ በነገው ጨዋታም ላለመሸነፍ ቅድሚያ ሰጥተው ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በነገው ጨዋታ ለገጣፎ ለገዳዲዎች ከጉዳት ሆነ ከቅጣት ነፃ በሆነ ስብስብ የሚቀርቡ ይሆናል።

በ16 ነጥቦች በሰንጠረዡ 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች በብዙ መልኩ የመሻሻል ምልክቶችን ባሳዩበት ድሬዳዋ ከተማ አጨራረሳቸውን እያሳመሩ ያሉ ይመስላል። በመጨረሻ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦችን ማሳካት ሲችሉ ነገም ቀዳሚ የማሸነፍ ግምት አግኝተው በሚጀምሩት ጨዋታ ድሬዳዋን በድል ለመሰናበት ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመከላከሉ ረገድ እጅግ ጠንካራ የሆነው ቡድኑ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ አሁንም ውስንነት ቢኖርበትም የስንታየሁ መንግሦቱ መመለስ ግን ለማጥቃቱ የጨመረው ነገር ስለመኖሩ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች እየተመለከትን እንገኛለን። ከዚህ ባለፈ ቡድኑ ከተጠባባቂ ወንበር በሚነሱ ተጫዋቾች ውጤቶችን እየያዘ መውጣቱን ተያይዞታል በመጨረሻውም ጨዋታ ተቀይሮ የገባው ዮናታን ኤልያስ በተጨማሪ ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ከሃዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል። ይህም ቡድኑ ከመጀመሪያ ተሰላፊዎች ባለፈ ከተጠባባቂነት እየተነሱ ጨዋታ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ተጫዋቾች ባለቤት መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ይህም ለአሰልጣኙ ይበልጥ የተጫዋቾች ምርጫ ነፃነት የሚሰጣቸው ይሆናል።

በነገው ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ ከሰነበቱት ቢኒያም ፍቅሬ እና አንተነህ ጉግሳ በተጨማሪ ሳሙኤል ተስፋዬንም እንዲሁ ግልጋሎት አያገኙም።

10 ሰዓት ሲል የሚጀምረውን የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ መለሰ ንጉሴ በመሀል ዳኝነት ሲመራው ፣ አማን ሞላ እና ደስታ ጉራቻ በረዳትነት ፣ ባሪሶ ባላንጎ በአራተኛ ዳኝነት ይህን ጨዋታ በጋራ ይመሩታል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

የምሽቱ ሁለተኛ ጨዋታ ደግሞ በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት ባልተጠበቁ መልኩ ነጥብ ጥለው የመጡትን አርባምንጭ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማን ያገናኛል።

ከቀናት በፊት በማጥቃቱ የሚታሙት አዞዎች ባልተጠበቀ መልኩ በመጀመሪያ አጋማሽ ሦስት ግቦችን አስቆጥረው ሲዳማ ቡናን መምራት ቢችሉም በሁለተኛው አጋማሽ ግን በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከሚሰለጥን አንድ ቡድን በማይጠበቅ መልኩ ሦስት ግቦችን አስተናግደው ሦስት አቻ መለያየት ችለዋል።

በማጥቃቱ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ የነበራቸውን ጥረት እና አፈፃፀም ቡድኑ በነገው ጨዋታ ማስቀጠል የሚኖርበት ሲሆን በመከላከሉ ረገድ ግን የተመለከትናቸው ግለሰባዊ እና መዋቅራዊ ግድፈቶችን አርመው መቅረብ ይኖርባቸዋል። አርባምንጮች እንደ ሲዳማው ጨዋታ ሁሉ ለነገው ጨዋታ ከጉዳትም ሆነ ቅጣት ነፃ የሆነ ስብስብን ይዘው ይቀርባሉ።

የአሰልጣኝ ደግዓረግ ይግዛው ባህር ዳር ከተማ ከአስደናቂ ግስጋሴያቸው ማግስት ካደረጓቸው የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ብቻ ያሳኩ ሲሆን በተለይ በመጨረሻ ጨዋታቸው ለማሳመን እየተቸገረ በሚገኘው መቻል ያስተናገዱት ሽንፈት ያልተጠበቀ ነበር።

አስደናቂ ግስጋሴውን ለማስቀጠል እየተቸገረ የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ አሁንም ቢሆን ከመሪው ኢትዮጵያ መድን በአራት ነጥቦች ብቻ አንሰው በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሲሆን ነገም ድል የሚቀናቸው ከሆነም ዕረፍቱን በሰንጠረዡ ሁለተኛ ሆነው የሚያሳልፉ ይሆናል።

በመከላከሉ ረገድ የተሻለ ጊዜን እስከ መቻሉ ጨዋታ ድረስ እያሳለፉ የነበሩት ባህር ዳር ከተማዎች ከጥንካሬያቸው በስተጀርባ ወሳኝ ሚና የሚወጣው እና በመቻሉ ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ የወጣው ያሬድ ባየህ በነገው ጨዋታ መግባቱ አጠራጣሪ ሆኗል። በተጨማሪም ረዘም ያለ ጊዜ በጉዳት እያሳለፉ የሚገኙት ፋሲል አስማማው እና ፍቅረሚካኤል ዓለሙም ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ቡድኖቹ በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ሁለት ግንኙነታቸውን ያደረጉ ሲሆን አርባምንጭ ከተማዎች በድምሩ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር በሁለቱም ጨዋታዎች በበላይነት ማጠናቀቅ ችለዋል።

የምሽቱን መርሃግብር ኤፍሬም ደበሌ በመሀል ዳኝነት ሲመሩት ዘመኑ ሲሳዬነው እና ኤልያስ መኮንን ረዳቶች ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት እንዲመሩ ተመድበዋል።