ቻን | በቻን ውድድር ላይ ኢትዮጵያዊው አልቢትር በዳኝነት ይሳተፋል

ከጥር 5 ጀምሮ በአልጄሪያ በሚከናወነው የቻን ውድድር ላይ የሀገራችን ዳኛ ተሳትፎ እንደሚኖረው ታውቋል።

በሀገር ውስጥ ሊግ ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት የቻን ውድድር ከቀናት በኋላ በኤልጄሪያ እንደሚደረግ ይታወቃል። ለሦስተኛ ጊዜ በዚህ ውድድር ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከነገ ጀምሮ ተጫዋቾችን በመሰብሰብ ዝግጅቱን እንደሚከውን ይጠበቃል። የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ ይህንን የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮን ሺፕ ውድድር የሚመሩ ዳኞችን ዝርዝር ይፋ ሲያደርግ የኢትዮጵያዊው ባምላክ ተሰማ ስም መኖሩን አስተውለናል።

በዚህም ውድድሩን የሚመሩ 19 ዋና፣ 21 ረዳት እንዲሁም 12 የቪ ኤ አር ዳኞች ስም ዝርዝር ይፋ ሲሆን ባምላክ ተሰማ በውድድሩ በቪ ኤ አር ዳኝነት ተሳትፎ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።

ሊዲያ ታፈሰ እና በላይ ታደሰ ከሀገራችን ተመርጠው በቻን የአልጄሪያ ቆይታ በዳኝነት ለማገልገል ከዚህ ቀደም ቅድመ ስልጠና ወስደው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻው ዝርዝር ውስጥ ግን ሳይካተቱ ቀርተዋል።