ሪፖርት | ድንቅ ፉክክር በታየበት ጨዋታ የጦና ንቦቹ ድል አድርገዋል

ሰባት ግቦች በተስተናገዱበት ጨዋታ ወላይታ ድቻ ለገጣፎ ለገዳዲን በማሸነፍ አምስት ደረጃዎችን ያሻሻለበትን ውጤት አስመዝግቧል።

በ13ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ የአራት ለምንም ሽንፈት የደረሰባቸው ለገጣፎ ለገዳዲዎች ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ ሦስት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም ኪሩቤል ወንድሙ፣ አስናቀ ተስፋዬ እና ኢብሳ በፍቃዱ እንዲያርፉ ተደርገው ፍቅሩ አለማየሁ፣ ኦካይ ጁል እና አንዋር መሐመድ ወደ ሜዳ እንዲገቡ ተደርጓል። በተመሳሳይ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን ገጥመው አንድ እኩል የተለያዩት ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው በመጨረሻ ደቂቃ ከቅጣት ምት ግብ ያስቆጠረላቸውን ዮናታን ኤሊያስ በሀብታሙ ንጉሴ ብቻ ተክተው ጨዋታውን ቀርበዋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እስከ 33ኛው ደቂቃ ድረስ አንድም የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ አልተደረገበትም። በአንፃራዊነት በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የተቀመጠው ለገጣፎ ለገዳዲ ኳሱን በተሻለ በማንሸራሸር ክፍተቶችን ለመፍጠር ሲሞክር ወላይታ ድቻ በበኩሉ በሚታወቅበት ጥብቅ የመከላከል አጨዋወት በመንቀሳቀስ የሚያገኛቸውን ኳሶች ለቁመታሙ አጥቂ ስንታየሁ መንግስቱ እየላከ አንደኛ እና ሁለተኛ ኳስ በማሸነፍ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ወጥኗል። ከላይ በጠቀስነው ደቂቃም ምንም እንኳን ለግብ የቀረበ ባይሆንም ወላይታ ድቻ የቀኝ መስመር ተከላካዩ በረከት ወልደዮሐንስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ የመጀመሪያውን ጥቃት ሰንዝሯል።

የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ከተመለከትን ከደቂቃ በኋላ ጨዋታው ግብ አስተናግዷል። በዚህም ሙከራውን ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች ከመሐል ሜዳ በጥሩ ቅብብል ይዘውት የሄዱትን ኳስ ስንታየሁ መንገስቱ ከበኃይሉ ተሻገር ተቀብሎ ዐየር ላይ በግሩም አጨራረስ ግብ አድርጎታል። ከዚህ የድቻ ግብ በኋላ ጨዋታው መልኩን ለውጦ ከሳጥን ሳጥን ምልልሶች ተስተውለውበታል። ለገጣፎ ለገዳዲዎችም ከአምስት ደቂቃዎች መመራት በኋላ አማኑኤል አረቦ ከተፈራ አንለይ ሳጥን ውስጥ የደረሰውን ኳስ የግብ ዘቡ ቢኒያም ገነቱን አቅጣጫ አስቶ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ አድርጓል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ 10 ደቂቃዎች ሞቅ ብሎ ሁለት ግቦችን ያስተናገደው ጨዋታው ፉክክሩ በሁለተኛው አጋማሽም ይቀጥላል ቢባልም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቀዝቀዝ ብሎ መከወን ይዟል። ቡድኖቹም በቀደመ አቀራረባቸው መንቀሳቀስን መርጠው ታይተዋል። 61ኛው ደቂቃ ላይ ግን የአጋማሹ የመጀመሪያ ጥቃት ተሰንዝሮ እጅግ አስደናቂ ግብ ተቆጥሯል። በተጠቀሰው ደቂቃም ተፈራ አንለይ አናጋው ባደግን ተጭኖ የተቀበለውን ኳስ ካርሎስ ዳምጠው ተቀብሎ ገፍቶ በመሄድ ከሳጥን ውጨ በአስደናቂ ሁኔታ በግራ እግሩ አክርሮ በመምታት ከግቡ አግዳሚ ጋር አጋጭቶ መዳረሺያው መረብ አድርጎት ለገጣፎ ለገዳዲ ወደ መሪነት ተሸጋግሯል።

ወላይታ ድቻዎች ወደ አቻነት ለመሸጋገር ግን ከአስር ደቂቃ በላይ መጠበቅ አላስፈለጋቸውም። በ71ኛው ደቂቃም በኃይሉ ተሻገርን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዘላለም አባተ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ሳጥን ውስጥ በመግባት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ድቻ ይህንን ግብ ካስቆጠረ በኋላም ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ጫና በማሳደር ለመንቀሳቀስ ሞክሯል። ውጥኑ ሰምሮም በ75ኛው ደቂቃ ቃልኪዳን ዘላለም ከግራ መስመር ሰብሮ በመግባት ቡድኑን ዳግም መሪ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል።

አጀማመሩ ቀዝቀዝ ቢልም ቀስ እያለ እየተጋጋለ የመጣው ጨዋታው ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የጣፎን አፀፋዊ ምላች አስመልክቷል። በዚህም የተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ አማኑኤል አረቦ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ግብ አስገኝቷል። ነገርግን የጎል ፌሽታውን የቀጠለው ፍልሚያው በ82ኛው ደቂቃ ሌላ ግብ አስተናግዶ መሪ አግኝቷል። በዚህም የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ያደረገው በረከት ወልደዮሐንስ ከመስመር የተሻማን ኳስ በግንባሩ መረብ ላይ አሳርፎት የጦና ንቦቹን ለሦስተኛ ጊዜ የመሪነት ቦታን እንዲይዙ አድርጓል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ከ36 ጨዋታዎች በኋላ አራት ግቦች ባስቆጠሩት ወላይታ ድቻዎች አሸናፊነት ተጠናቋል።