“ተጫዋቾቻችን ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ ነበሩ ፤ የሚችሉትን ለማድረግ ጥረት አድርገዋል። ውጤቱ ይገባናል ብዬ አስባለሁ።” ደግአረገ ይግዛው
“በምንፈልገው ደረጃ የግብ ዕድሎችን አልፈጠርንም” መሳይ ተፈሪ
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህርዳር ከተማ
ስለ ጨዋታው…
ጨዋታው እንደታየው አርባምንጭ ወደ ላይ ለመምጣት እኛ ደግሞ ያለንበትን የመሪነት ቀጠና ላለመልቀቅ እጅግ ፈታኝ ጨዋታ ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ ከሽንፈት ነው የመጣነው። ባለፈው ያስተናገድነው ሽንፈት ትንሽ ከባድ ነበር ፤ ተጫዋቾቹ ቶሎ አገግመው ወደ ውጤት መመለሳቸው ደሞ እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው። ተጫዋቾቹ ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ ነበሩ ፤ የሚችሉትን ለማድረግ ጥረት አድርገዋል። ውጤቱ ይገባናል ብዬ አስባለሁ።
በሁለተኛው አጋማሽ ስለመቀዛቀዛቸው…
እውነት ነው። ስንገባም በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ጨዋታውን ጨርሶ ለመውጣት ነበር ያቀድነው። እንዳሰብነውም ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ችለናል ፤ ግን አልተጠቀምንባቸውም። 1-0 ሆነን ነው ለዕረፍት የወጣነው እና ይዘነው የወጣነው ውጤት በሁለተኛው አጋማሽ በጥንቃቄ እንድንጫወት ትምህርት ሰጥቶናል። ከሲዳማ ቡና ጋር በነበረን ጨዋታ መጨረሻ በጭማሪ ደቂቃ በላይ ግብ አስተናግደን የወጣነው ትንሽ ስሜት ውስጥ ይከት ነበር። ዛሬ ይህ ጨዋታ ለኛ እጅግ በጣም አስፈላጊያችን ነው። ተገቢውን ዕረፍት አድርጎ በቀጣይ ለመመለስ በሥነልቦናም ረገድ ተጫዋቾቻችን ከፍ ብሎ ለመምጣት ውጤቱ በጣም ያስፈልገን ስለነበረ ጥንቃቄን መርጠናል። ከጥንቃቄ ባሻገር ግን በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶች አድርገናል። ከሞላ ጎደል ያሰብነውን አሳክተናል ማለት እችላለሁ።
ስለ ድሬዳዋ ቆይታቸው…
እንግዲህ በድሬዳዋ ቆይታችን ውጤታማ ነን ማለት ይቻላል። ድሬዳዋ በነበረን ቆይታ 17 ነጥቦችን ሰብስበናል። ከኛ ጋር ተመሳሳይ ነጥብ የሰበሰበው ወላይታ ድቻ ነው። ስለዚህ ትልቁን ነጥብ ነው ሰብስበን ከድሬዳዋ የወጣነው እና የነበረን ቆይታ እጅግ በጣም አስደሳች ነው። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ጠንክረን ሠርተን ይህን ውጤት አዳማ ላይ ለማስቀጠል እንፈልጋለን። በሊጉ ላይም ተፎካካሪ ሆኖ መቆየት ዕቅዳችን አድርገን እየሠራን ነው። አሁን ያለንበት ሂደት ጤናማ ነው ብዬ አስባለሁ።
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ
ስለ ጨዋታው…
ጫና ላይ ነበርን በዚህ አጋጣሚ እነሱ ተጭነው ጎሎችን አስቆጥረዋል። ከዕረፍት በኋላ እኛም ለመውጣት ሞከርን ግን በምንፈልገው ኃይል ማጥቃት አልቻልንም። ግን ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ዕድል ለማምጣት ጥረት አድርገናል። በተወሰነ መልኩ መሃል ሜዳ ላይ አንዳንዴ የሚቆራረጡ ኳሶች ነበሩ ፤ ኳሶችን በማቀበል ችግር ሁለተኛው ግብ ተቆጥሮብናል። በሁለተኛው አጋማሽ ከእንቅስቃሴ አኳያ ለውጥ ነበረን።
በሁለተኛው አጋማሽ ስለወሰዱት ብልጫ .
ኳሶችን ተቆጣጥሮ በመሄድ እና በሁለተኛ አማራጫችን ደግሞ ለማጥቃት ነው ጥረት ያደረግነው እነሱ ወደራሳቸው የሜዳ ክፍል ጥቅጥቅ ብለው ሲከላከሉ የነበሩት። ያም ቢሆን በምንፈልገው ደረጃ የጎል ዕድሎችን አልፈጠርንም።
ስለ ድሬዳዋ ቆይታቸው…
ሰባት ጨዋታ ሳንሸነፍ ነበር የመጣነው ፤ ዛሬ ተሸንፈናል። አጠቃላይ ያለንን ነገር ባህር ዳር ላይ ከነበረው ጨዋታም ጭምር ገምግመን ማሻሻል እንፈልጋለን።