የወቅቱ የቻን ውድድር አሸናፊ የሆነው የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ከቀናት በኋላ በሚጀምረው የቻን ውድድር ላይ የሚሳተፈው ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ሲሟላ መሆኑን ይፋ አደረገ።
በሀገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት የአህጉሪቱ ውድድር ከቀናት በኋላ በአልጄሪያ እንደሚከናወን ይታወቃል። በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጉዟቸውን አጠናቀው በምድብ የተደለደሉ 18 ሀገራትም ዝግጅታቸውን እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን በሰሜን-ምዕራብ አፍሪካ የምትገኘው ሞሮኮ በውድድሩ መቃረቢያ ያሰማችው መረጃ ውድድሩን እንዳያጠለሽ ተሰግቷል።
ከእግርኳሱ ውጪ ባለ የአልጄሪያ እና ሞሮኮ የፖለቲካ ግንኙነት አልጄሪያ በዐየር ክልሏ የሞሮኮ የዐየር የትራንስፖርት አማራጮች እንዳይገቡ መከልከሏ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ ከሞሮኮ ወደ አልጄሪያ በቀጥታ የሚደረጉ በረራዎች የሉም። በዚህ የቻን ውድድር የሚሳተፈው የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድንም ከሀገሩ ራባት ወደ አልጄሪያ ኮንስታንቲን ልዑካኑን ይዞ የሚጓዝ ልዩ በረራ ካልተፈቀደ እንደማይሳተፍ ይፋ አድርጓል።
አልጄሪያ 2021 መስከረም ወር ላይ በሞሮኮ የተመዘገቡ የመንገደኞች እና የጦር አውሮፕላኖች በዐየር ክልሏ መከልከሏ ይታወሳል።