የ2022 የቻን ውድድር አስተናጋጅ ሀገር የሆነችው እና በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው አልጄሪያ ስድስተኛ የአቋም መለኪያ ጨዋታዋን ለመከወን ቀጠሮ ይዛለች።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት 7ኛ የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒየን ሺፕ ውድድር በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር አልጄሪያ ከጥር 5 ጀምሮ ይካሄዳል። ለመጀመሪያ ጊዜ 18 ቡድኖችን በማሳተፍ የሚካሄደው ውድድር ከመጀመሩ በፊት ተሳታፊዎች ዝግጅታቸውን እየከወኑ የሚገኝ ሲሆን የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችንም እያደረጉ ነው። በቀጣዩ ሳምንት ወደ ሞሮኮ አምርቶ ዝግጅቱን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ራባት ላይ ከሞሮኮ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ ሲጠበቅ በምድቡ የሚገኘው አልጄሪያ ደግሞ የዛሬ ሳምንት ታኅሣሥ 29 ከውድድሩ በፊት ስድስተኛ የወዳጅነት ጨዋታውን ለማድረግ ቀጠሮ ይዟል።
የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ከሁለት ወር በፊት ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ አምርቶ ለሁለት ሳምንት ዝግጅቱን አድርጎ ሦስት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አድርጎ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ ሁለት ተጨማሪ ፍልሚያዎችን መከወኑን መዘገባችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ የመጨረሻ እንደሆነ የተገለፀውን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከውድድሩ መጀመር አንድ ሳምንት አስቀድሞ በሜዳው ከጋና አቻው ጋር በኦራን ያደርጋል።