የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የቀጥታ ስርጭት ያልጀመረበት ምክንያት ተጠቆመ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ከያዝነው ዓመት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከፊፋ ፕላስ ጋር በመተባበር ለማስተላለፍ አቅዶ ተግባራዊ ሳይደረግ የቆየ ሲሆን የገጠመው ችግር ተፈቶ በቅርቡ ለማሰራጨት መታሰቡ ተገልጿል።

የ2015 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ከተማ እየተደረገ ዘጠኝ የጨዋታ ሳምንትን አሳልፏል። 12ኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው የሊጉ ውድድር በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የበላይነት የሚተዳደር ሲሆን ከያዝነው የውድድር ዓመት ጀምሮ ፌድሬሽኑ ከፊፋ ፕላስ ጋር በተዋዋለው ውል መሰረት የተመረጡ ጨዋታዎችን በፊፋ አፕሊኬሽን እገዛ ለማስተላለፍ መታሰቡ ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ ለክለቦች ተገልፆ ነበር።

\"\"

ሆኖም እስከ አሁን ሰዓት ድረስ ግን በእንስቶቹ መካከል የሚደረገው የሊጉ መርሀግብር የቀጥታ የምስል ስርጭት እያገኘ አለመሆኑን ተከትሎ በውድድሩ ተሳታፊ የሆኑ በርካታ ክለቦች ጉዳዩን ሲጠይቁ ሰንብተዋል።

በትናንትናው ዕለት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና ምክትሉ ዶ/ር ዳኛቸው ንገሩ በሀዋሳ ተገኝተው ከሴት ክለብ አሰልጣኞች እና ቡድን መሪዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን አመሻሽ ላይ በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል በነበረው የራት ግብዣ ላይ ስለቀጥታ ስርጭቱ ጉዳይ በአጭሩ አስረድተዋል። \”ለማስተላለፍ የተዋዋልነው ድርጅት ሀገር ውስጥ ባለው የፕሮዳክሽን አለመጣጣም የተነሳ ነው ስርጭቱ ሳይደረግ የቀረው። አንድ ጨዋታ ለማስተላለፍ ተሞክሮ ነበር ፤ ነገር ግን የኢንተርኔት ብሮድባንድ ችግሮች በአስተላለፊው ካምፓኒ ላይ ተከስቷል ፤ ይህን በቀጣይ ለመፍታት ታስቧል። በቀጣይ በሊጉ የሚደረጉ 20 ጨዋታዎች ይተላለፋሉ ብለን እናስባለን ለዚህም በሂደት ላይ እንገኛለን\” በማለት ፕሬዝዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ ተናግረዋል።

\"\"

የክለብ ተወካዮች የሁለተኛው ዙር የሚደረግበት ቦታ በጊዜ አለመገለፁን በጥያቄ ያነሱ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ በመልሳቸው በቅርቡ በሴቶች ልማት ኮሚቴ በኩል ምላሽ እንደሚሰጣቸውም ጭምር አክለው ተናግረዋል።