ከፍተኛ ሊግ | የምድብ ለ ውሎ

ጅማ ላይ በተደረጉ የ7ኛ ሳምንት የምድብ ለ አራት ጨዋታዎች በመሪዎቹ መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ ብሏል።

\"\"

በተመስገን ብዙዓለም

ነቀምቴ ከተማ 3-1 ጅንካ ከተማ

ነቀምቴ ከተማና እና ጅንካ ከተማን ባገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ለተመልካች ሳቢ ያልነበረ ሲሆን 20ኛው ደቂቃ ላይ ምኞት ማርቆስ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተመስገን ዲባ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይሯታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ላይ ደግሞ ቦና ቦካ ድንቅ ግብ አስቆጠሮ ጨዋታው በነቀምቴ ከተማ 2-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

\"\"

በሁለተኛ አጋማሽ በተጀመሩ ደቂቃዎች ውስጥ የነቀምቴ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ባለመናበብ የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ተቀይሮ የገባው ጎሣዬ ብርሃኑ በ50ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥሮ ጅንካን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥሯል። በቀሩት ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ ፉክክር ሲደረግበት ቆይቶ ነቀምቶች ባደረጉት ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ 80ኛው ደቂቃ ላይ በአሸናፊ ኃይለማርያም አማካኝነት ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ጨዋታውም በነቀምት ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዚህም ቡድኑ ነጥቡን 15 በማድረስ ከመሪው ሻሸመኔ ጋር ያለውን ርቀት ወደ አንድ ነጥብ ዝቅ ማድረግ ችሏል።

አዲስ አበባ ከተማ 0-1 ደብረብርሃን ከተማ

05:00 ላይ በጀመረው አዲስ አበባ እና ደብረብርሀን ሲገናኙ በመጀመሪያው አጋማሽ አዲሰ አበባዎች በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነት ቢኖራቸውም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል። 35ተኛ ደቂቃ ላይ ሙሉቀን ታሪኩ የሞከረውና የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ በአጋማሹ የተሻለው የቡድኑ ሙከራ ነበር። ደብረብርሃኖች በአንፃሩ በሚያገኙት ኳስ ቀጥተኛ አጨዋወትን በመምረጥ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው አጋማሹ ያለግብ ተጠናቋል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ በሁለቱም በኩል ጥሩ ፉክክር ሲያስመለክተን 47ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ አበባው ግብ ጠባቂ የመለሰውን ኳስ ያገኘው ያሬድ ብርሀኑ ወደ ግብነት ቀይሮት ደብረብርሃንን መሪ ማድረግ ችሏል። አዲስ አበባ ከተማዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በተለይም በቀኙ የሜዳ ክፍል ጥረት ቢያደርጉም የመጨረሻ ኳሳቸው ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። በጥንቃቄ በመጫወት ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ጥረት ያደረጉት ደብረብርሀኖች ተሳክቶላቸው ጨዋታውን 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

\"\"

ንብ 4-0 ከፋ ቡና

በዕለቱ ሦስተኛ ጨዋትታ የመጀመሪያ አጋማሽ ንቦች ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት እና ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ብልጫ ሲኖራቸው ኢዮብ ደረሰ 14ኛው እና 33ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራቸው ግቦች 2-0 እየመሩ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ለተመልካች እጅግ አዝናኝ ሆኖ ሲቀጥል ንቦች ፍፁም የበላይነቱን መውሰድ ችለዋል። 62ኛው እና 84ኛ ደቂቃ ላይ ናትናኤል ሰለሞን እና ኤልያስ እንድሪስ ተጨማሪ ግቦችን አስቆጥረው ጨዋታው በንብ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

ይርጋጨፌ ቡና 0 – 0 ሻሸመኔ ከተማ

10:00 ሲል በጀመረው የመጨረሻው ጨዋታ ሁለት ተቃራኒ አጋማሾች በነበሩበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ብርቱ የማሸነፍ ፍላጎት ሲስተዋልበት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ ግን ይርጋጨፌዎች የተሻሉ ነበሩ። በአንጻሩ ሻሸመኔ ከተማዎች የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።

ከዕረፍት መልስ ሻሸመኔ ከተማዎች እጅግ ተሻሽለው ሲቀርቡ በተደጋጋሚ ከተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ግብ ለማስቆጠር አልቻሉም። ይርጋጨፌዎች በበኩላቸው የራሳቸው የሜዳ ክፍል ውስጥ በቁጥር በዝተው በመገኘት በሚያገኙት ኳስ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ቢሞክሩም ውጤታማ ሳይሆኑ ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል። በዚህም ሻሸመኔ ከተማዎች በ16 ነጥቦች ምድቡን መምራት ቀጥለዋል።

\"\"