ከፍተኛ ሊግ | የምድብ ሐ ውሎ

ዛሬ ሆሳዕና ላይ የተደረጉት የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ሦስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ የ1-0 ውጤት ሲጠናቀቁ ኮልፌ ቀራኒዮ እና ደሴ ከተማ ወደ መሪው ለመቅረብ የነበራቸውን ዕድል አምክነው ገላን ከተማ ወደ ሁለተኛነት መጥቷል።

በጫላ አቤ

\"\"

ኮልፌ ክ/ከ 0-1 ገላን ከተማ

04:00 ላይ የጀመረው የኮልፌ እና ገላን ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ለዓይን ሳቢ እና በሁለቱም በኩል ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት አጋማሽ ነበር። በስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ ባልተገባ ስፖርታዊ ባህሪይ በቅጣት ግብ ጠባቂያቸውን ያጡት ኮልፌ ክፍለ ከተማዎች በስንታየው ሰለሞን እና በብሩክ ሰሙ የሚመራው የፊት መስመር ጥሩ ግብ ማግባት ጥረት አና እንቅስቃሴ ያሳዩን ሲሆን በአንፃሩ የተሻለ የግብ እድል የመፍጠር እና የጨዋታ ብልጫ ያሳዩት ገላን ከተማዎች በበየነ ባንጃው እና በአፍቅሮት ሰለሞን እየተመሩ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እና የግብ ዕድል በመፍጠር ተሽለው ታይተዋል። በዚህ ሁኔታ የቀጠለው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው በ43ኛው ደቂቃ ገለን ከተማዎች ከግቡ ወደ 20 ሜትር ርቆ ያገኙትን የቅጣት ምት ዕድል በሱፍቃድ ነጋሽ ግሩም በሆነ ሁኔታ አስቆጥሮ በገላን ከተማ መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ አርገዋል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ኮልፌዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ተነቃቅተው እና የተጫዋች ቅያሬ በማድረግ በሙሉ ፍላጎት ሲጫወቱ እና ግብ ለማስቆጠር ሲረባረቡ ተመልክተናል። በገላን ከተማ በኩል ከመጀመሪያው አጋማሽ በተወሰነ የመረጋጋትና የወሰዱትን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ከፊት መስመር ተሰልፈው የነበሩትን ሦስት ተጫዋቾች በመቀየር ግባቸውን ለማስጠበቅ ሲጥሩ ተስተውለዋል። ሆኖም አጋማሹ ምንም ግብ ሳይቆጠርበት በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረች ብቸኛ ግብ ገላን ከተማ በጠባብ ግብ በማሸነፍ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችሏል። ውጤቱን ተከትሎም ገላን ከተማ ነጥቡን 12 በማድረስ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።

ደሴ ከተማ 0-1 ነገሌ አርሲ

ከምሳ መልስ 08:00 ላይ በጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት እና ፈጣን እንቅስቃሴ የተስተዋለበት ነበር። ሁለቱም ተጋጣሚዎች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ሲጥሩም ይታይ ነበር። የነገሌ አርሲ ቡድን ኳስን በመያዝ በዛ ባለ ቅብብል ወደ ግብ ለመድረስ ሲጥሩ ታይቷል። በአንፃሩ በደሴ ከተማ በኩል በአብዛኛው ግብ ላይ ለመድረስ በአነስተኛ ቅብብል እና ረዥም ኳሶችን በመጠቀም ወደ ግብ ለመድረስ ሲጥሩ ተመልክተናል። በ15ኛው ደቂቃ የነጌሌ አርሲው ተጫዋች ሰለሞን ገመቹ ያገኘውን ግልፅ የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ፈጣን እንቅስቃሴ የነበረው ሲሆን የነገሌ አርሲው የፊት መስመር ተጫዋች ትንሳኤ ኑራ እና ያሬድ መሀመድ የደሴ ከተማ የከላካይ ስፍራ ተጫዋቾችን ሲያስጨንቁ ተመልክተናል። በደሴ ከተማ በኩል የመስመር ተጫዋች የሆነው አብዱሰላም የሱፍ በተደጋጋሚ ተሻጋሪ ኳሶችን በመስጠት የግብ ዕድሎችን ሲፈጥር ተስተውሏል። ጨዋታው በዚህ ዓይነት ፉክክር ቀጥሎ ሊጠናቀቅ 4 ደቂቃዎች ሲቀሩት በ86ኛው ደቂቃ ላይ ነገሌ አርሲዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት ያሬድ መሀመድ ያሻገረውን ኳስ አብረሀም ዓለሙ በማስቆጠር ነጌሌ አርሲዎችን መሪ እና አሸናፊ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውም በነጌሌ አርሲዎች 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

ቡራዩ ከተማ 0-1 ዳሞት ከተማ

10:00 ላይ በጀመረው የዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ እና በአመዛኙ የቡራዩ ከተማ መጠነኛ የበላይነት የታየበት ነበር። ቡድኑ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ሲሆን በዳሞት ከተማ በኩል በረጃጅም ኳሶች በመጠቀም ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ተስተውሏል። ሆኖም ግን እንቅስቃሴው በተወሰነ መልኩ ቀዝቀዝ ያለ እና የተቆራረጠ ኳሶች አልፎ አልፎ ይስተዋሉበት ነበር።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተወሰነ መልኩ መነቃቃት የታየበት ሲሆን ቡራዩ ከተማ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ ሆኖ በተደጋጋሚ የተቃራኒ ግብ ክልል በመድረስ የግብ ሙከራ ማድረግ ቢችልም ወደ ውጤት መቀየር ሲሳነው ተስተውሏል። በዳሞት ከተማ በኩል ትኩረቱን በመከላከል ላይ አድርጎ በተገኘው አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ዕድሎችን ለመጠቀም ሲጥሩ ተመልክተናል። በዚህም ሂደት በ72ኛው ደቂቃ ላይ ቡራዩ ከተማዎች የተገኙትን የመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድል በጨቡ ማትያስ አማካኝት በማስቆጠር ዳሞት ከተማን አሸናፊ ማድረግ ችሏል። ዳሞት ከተማም የውድድሩ ሁለተኛ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል።