ቻን | ዋልያዎቹ የአቋም መፈተሻ ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት ቀን ታወቀ

ለቻን ውድድር የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅቱን ሞሮኮ ላይ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁለት ቀናት ልዩነት ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ያደርጋል።

\"\"

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአልጄሪያ አስተናጋጅነት የሚከናወነው የዘንድሮ የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒየንሺፕ ውድድር ላይ እንደሚካፈል ይታወቃል። የቡድኑ አለቃ ከመረጧቸው ሀያ ስምንት ተጫዋቾች ሀያ ስድስቱን በማግኘት የሀገር ቤት ዝግጅታቸውን እየከወኑ የሚገኝ ሲሆን የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅታቸውን ለ8 ቀናት በሞሮኮ ለማድረግ ደግሞ ነገ ጉዞ ያደርጋሉ።

ከዚህ ቀደም ቡድኑ በሞሮኮ በሚኖረው ቆይታ ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን እንደሚያደርግ መገለፁ የሚታወስ ሲሆን አንደኛው ጨዋታ ከሀገሬው የቻን ቡድን ጋር እንደሆነ ተጠቁሞ ነበር። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በቲውተር ገፃቸው ይፋ እንዳደረጉት ከሆነ ቡድኑ ሁለተኛውንም ጨዋታው ከሞሮኮ ጋር ያደርጋል።

\"\"

የመጀመሪያው የቡድኑ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ታኅሣሥ 29 ሲደረግ ሁለተኛው ደግሞ ከሁለት ቀናት በኋላ ጥር 1 እንደሚከወን ዋና ጸሐፊው አመላክተዋል።