ከፍተኛ ሊግ | የምድብ ሀ ውሎ

በከፍተኛ ሊጉ 7ኛ ሳምንት ባህር ዳር ላይ ከተደረጉ የምድብ ሀ ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ አቃቂ ቃሊቲ ብቸኛውን የዕለቱን ድል አሳክቷል።

\"\"

ጅማ አባ ቡና 1-1 አዲስ ከተማ ክፍለከተማ

ለተመልካች አዝናኝ በነበረው የ03:00 ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል በርካታ ሙከራዎች ሲደረጉ በመጠኑም ቢሆን ጅማ አባ ቡናዎች የተሻሉ ነበሩ። በመጀመሪያ ደቂቃዎች አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት አዲስ ከተማዎች ተሳክቶላቸዋል 5ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ አብዱ ባስቆጠራት ግብ መሪ መሆን ሲችሉ 33ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው አህመድ አብዱ ኳስን ከግብ ጠባቂው ማሳለፍ ችሎ መረቡ ላይ ያርፋል ተብሎ ሲጠበቅ የአባ ቡናው ተከላካይ ሬድዋን ሸሪፍ በፍጥነት ደርሶ ኳሱን ማስወጣት ችሏል።

\"\"

ከረጅም ርቀት በሚደረጉ ሙከራዎች ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ጅማ አባ ቡናዎች 42ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ዘላለም አበበ ከሳጥን አጠገብ  በውጨኛው እግሩ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በአዲስ ከተማዎች በኩል 63ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ በቀለ ራሱ የወሰደውን ኳስ ከቀኝ መስመር በድንቅ ሁኔታ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ያስወጣበት ኳስ በጅማ አባቡናዎች በኩል ደግሞ 74ኛው ደቂቃ ላይ ብዙዓየሁ እንደሻው ከግራ መስመር ያሻገረውን እና ቴድሮስ ገ/እግዚአብሔር ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሰይፉ ታከለ አስቆጠረው ሲባል ያባከነው ኳስ በሁለቱም በኩል በአጋማሹ የተሻሉ የግብ ዕድሎች የነበሩ ሲሆን ጨዋታውም 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ባቱ ከተማ 2-2 ጋሞ ጨንቻ

ብርቱ ፉክክር በታየበት እና የሳምንቱ ምርጥ በነበረው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ጋሞ ጨንቻዎች ጨዋታውን በአስደናቂ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ሰለሞን 15 ሰከንድ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በጠበበው የቀኙ የግብ ቋሚ በኩል በድንቅ አጨራረስ ግብ ማስቆጠር ችሏል። የውድድር ዘመኑን ከጀመሩበት አስደናቂ ብቃት ቀስ በቀስ እየወረዱ የመጡት ባቱዎች እዩኤል ሳሙኤል 9ኛው ደቂቃ ላይ የግቡ የቀኝ ቋሚ በመለሰበት እና በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት አክርሮ መትቶት ግብ ጠባቂው በመለሰው ኳስ ፈታኝ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። እንደ ቡድን ጠንካራ የሆኑት ጨንቻዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ ምትኩ በንዳ በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠራት ግብ መሪነታቸውን ማጠናከር ሲችሉ 39ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ባቱዎች ግብ አስቆጥረዋል። ከረጅም ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ሀቢብ ጃለቶ ሲመታ ያገኘው ዮናታን አንባዬ በግንባሩ በመግጨት ማስቆጠር ችሏል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽም ተመጣጣኝ ፉክክር ሲያስተናግድ 51ኛው ደቂቃ ላይ የጨንቻው ለገሠ ዳዊት ከሳጥን ውጪ ድንቅ ሙከራ ቢያደርግም የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ተፈራ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ምትኩ በንዳ በግንባሩ በመግጨት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው አስወጥቶበታል። ያንኑ ኳስም ከቀኝ መስመር ከማዕዘን አሻምተውም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ሲታትሩ የነበሩት አሳዎቹ ተሳክቶላቸው 59ኛው ደቂቃ ላይ አብዱላዚዝ አማን ከቅጣት ምት ሞክሮት በተጫዋቾች ተጨርፎ በገባው ኳስ አቻ መሆን ችለዋል። ከዚህ ሙከራ በኋላም ባቱዎች ነጥቡን ለማስጠበቅ ጨዋታውን በማረጋጋት ሲቀጥሉ ጨዋታውም 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ዱራሜ ከተማ 0-1 አቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ

ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ 3ኛው ደቂቃ ላይ የዱራሜው አለኝታ ማርቆስ ከቅጣት ምት ባደረገው እና ግብ ጠባቂው በእግሩ በመለሰው ኳስ ሙከራዎችን ማስተናገዱን ሲጀምር በኳስ ቁጥጥሩ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለማስመለስ ጥረት ማድረግ የቀጠሉት አቃቂዎች 19ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም በረከት ዳንኤል ኪሩቤል ይጥና ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በኃይሉ ወገኔ ማስቆጠር ችሏል። የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ከተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ በቁጥር በመብዛት ጫና ማድረግ የጀመሩት ዱራሜዎች 23ኛው ደቂቃ ላይ ወንዱ ፍሬው እና አብርሃም አልዲ ከፈጠሩት የግብ ዕድል ውጪ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።

\"\"

ጨዋታው ከዕረፍት መልስ እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በኳስ ቁጥጥሩ ዱራሜዎች የተሻሉ ቢመስሉም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን አቃቂዎች የተሻሉ ነበሩ። 66ኛው ደቂቃ ላይ በኪሩቤል ይጥና እና 90+2 ላይ በእሸቱ ጌታሁን አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ጠባቂው ማፑቱ ይስሃቅ መልሶባቸዋል። የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ዱራሜዎች ከዕረፍት መልስ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"