ከፍተኛ ሊግ | የምድብ ለ ውሎ

ጅማ ላይ በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ሦስት ጨዋታዎች ተከናውነው ሁሉም ያለግብ ተጠናቀዋል።

በተመስገን ብዙዓለም

አምቦ ከተማ 0-0 ጉለሌ ክፍለከተማ

\"\"

የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ 04:00 ላይ ሲጀምር በቀዳሚው አጋማሽ ጉለሌዎች ኳስ ይዘው በመጫወት በተደጋጋሚ ወደ ተጋጠሚ ሜዳ ክልል መድረስ ቢችሉም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል። 26ኛው ደቂቃ ላይም ጁንዴክስ አወቀ በግንባሩ በመግጨት ያደረገውን ሙከራ የአምቦው ግብ ጠባቂ መልሶበታል። አምቦዎች በበኩላቸው ተከላክለው በመጫወት በሚያገኟቸው ኳሶች በግራ መስመር በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርሱ 30ኛው ደቂቃ ላይ በጫላ ከበደ አማካኘነት ኢላማውን የጠበቀ የመጀመሪያ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማየት ችለናል። አምቦ ከተማዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ መሀል ሜዳው ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ለአጥቂዎቻቸው በቂ የጎል ዕድል መፍጠር አልቻሉም። 76ኛው ደቂቃ ላይ የጉለሌ ተከላካይ ኳስ በእጅ ነክቷል በሚል የአምቦ የቡድን አባላት ከፍተኛ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ጉለሌዎች የተደራጀ የመከላከልና የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን በመልሶ ማጥቃት በተቃራኒ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም በአምቦ ከተማ ተከላካዮች በቀላሉ ኳስ ሲነጠቁ ታይተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ጉለሌ መሀል ሜዳው ላይ ደካማ ሆነው ሲታዩ በተቃራኒው የአምቦ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴዎች ጥሩ የሚባል ደረጃ ሲንቀሳቀስ ታይቷል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።

\"\"

ቦዲቲ ከተማ 0 – 0 ቂርቆስ ክፍለከተማ

ከምሳ መልስ በተደረገው ጨዋታ ቂርቆሶች ኳስን ከግብ ጠባቂ መስርተው በመጫወት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ቢደርሱም አጥቂዎች በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ በሆነ አቋቋም የግብ ዕድል ሲያባክኑ በአጋማሹ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ቦዲቲዎች የማጥቃት ኃይላቸውን በመስመር በኩል በማድረግ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም በቂርቆስ ተከላካዮች ጥንቃቄ በተሞላ መከላከል በተመሳሳይ ምንም የተሻለ ሙከራ ሳያደርጉ አጋማሹ ተጠናቋል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ቂርቆሶች ተሻሽለው ሲቀርቡ ኳሱን በሁሉም የሜዳ ክፍል በማንሸራሸር ብልጫ ቢወስዱም 87ኛው ደቂቃ ላይ አብዱከሪም ቃሲም በግሩም ሁኔታ ሞክሮት ግብጠባቂው የመለሰበት ኳስ ብቻ የተሻለው ሙከራቸው ነበር። ቦዲቲዎች በበኩላቸው በመከላከል ላይ አመዝነው በመጫወት በመልሶ ማጥቃት ወደ ቂርቆስ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም 70ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል አሊሳ ካደረገው ሙከራ በቀር የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታውም ያለግብ ተጠናቋል።

ከንባታ ሺንሽቾ 0-0 እንጅባራ ከተማ

በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የመጀመሪያ 25 ደቂቃዎች ከንባታዎች በተቃራኒ ሜዳ ኳስ በመጫወት የመሀል ክፍሉን በመቆጣጠር ብልጫ ቢወሰዱም የጎል ዕድል መፍጠር ሲቸገሩ በተቀሩት 20 ደቂቃዎች እንጅባራዎች ወደ ጨዋታው በመመለስ ብልጫ ተወስዶባቸው የነበረውን የመሀል ሜዳ እና የግራ መስመር እንቅስቃሴ መቆጣጠር ሲችሉ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ግን ለመፍጠር ተቸግረዋል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ እንጅባራዎች ተሻሽለው ሲቀርቡ በሁሉም ቦታ ላይ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። በዚሁ እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ከጨዋታ ውጪ በሆነ አቋቋም ላይ በነበሩት አጥቂዎቻቸው የግብ ዕድሎችን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ከንባታዎች በበኩላቸው ጥንቃቄ በተሞለው አጨዋወት ወደ መከላከሉ አመዝነው ታይተዋል። በመልሶ ማጥቃትም የጨዋታ መገባደጃ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ቢችሉም ጥፋት ተሰርቷል በሚል ጎሉ ተሽሮባቸዋል። በደቂቃ ልዩነትም ጥሩ ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው ተመልሶባቸዋል። ጨዋታም ያለ ግብ ተጠናቋል።