በትናንትናው ዕለት ከአይቮሪኮስት ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያደረገችው ሊቢያ ሽንፈት ስታስተናግድ የፊታችን እሁድ ደግሞ ሌላ ብቃቷን የምትፈትሽበት ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ ይዛለች።
በሀገር ውስጥ ውድድሮች የሚሳተፉ ተጫዋቾች የሚካፈሉበት የቻን ውድድር ከጥር 5 ጀምሮ እንደሚደረግ ይታወቃል። በዚህ ውድድር ላይ ከሚሳተፉ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የሊቢያ ቡድንም በምድብ አንድ ከኢትዮጵያ፣ አልጄሪያ እና ሞዛምቢክ ጋር ተደልድሏል።
ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ አሉታዊ ዜናዎች ሲሰሙበት የነበረው ብሔራዊ ቡድኑ ችግሮቹን ፈትቶ ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በትናንትናው ዕለትም ከአይቮሪኮስት የቻን ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጎ በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠረበት ግብ አንድ ለምንም ተረቷል።
ቱኒዚያ ላይ ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ የፊታችን እሁድ ደግሞ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር የመጨረሻ የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ ወቅታዊ አቋሙን ከገመገመ በኋላ ጥር 3 ወደ አልጄሪያ ለማምራት ዕቅድ እንደያዘ ተሰምቷል።
የሊቢያ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ከኢትዮጵያ ጋር የምድብ የመጨረሻ ፍልሚያውን ጥር 13 ላይ የሚያደርግ ይሆናል።