የአቡበከር ናስር ጉዳት ወቅታዊ ሁኔታ…

ለደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውስ እየተጫወተ የሚገኘው አቡበከር ናስር በገጠመው ጉዳት ለምን ያህል ጊዜ ከሜዳ እንደሚርቅ ጠቁሟል።

\"\"

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የምንግዜም ከፍተኛ ጎል አግቢ በመሆን ባለታሪክ የሆነው አቡበከር ናስር ወደ ደቡብ አፍሪካው ክለብ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ካቀና በኋላ ጎሎችን በማስቆጠር መልካም የሚባል ጅማሮ አሳይቶ ነበር። ሆኖም ከዚህ ቀደም ባጋጠመው ከበድ ያለ ጉዳት ምክንያት ለወራት ከሜዳ ለመራቅ ተገዶ ቆይቷል።

አቡበከር ባሳለፍነው ሳምንት ሙሉ ለሙሉ ከጉዳቱ አገግሞ ክለቡ ሰንዳውንስ ከኦርላንዶ ፓይረስ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ዳግም ወደ ሜዳ ቢመለስም ሜዳ ላይ መቆየት ችሎ የነበረው ለአርባ አምስት ደቂቃ ብቻ ነበር። የኦርላንዶ ፓይረሱ የግብ ዘብ ቁርጭምጭሚቱ ላይ ባደረሰበት ከበድ ያለ ጉዳት ምክንያት ተቀይሮ ሊወጣ ችሏል። ሶከር ኢትዮጵያም ጉዳቱ ከተከሰተ በኋላ ያለበትን የጤና ሁኔታ ስትከታተል ቆይታለች።

\"\"

ጉዳቱ ከገጠመው በኋላ የኤም አር አይ ምርመራ ለማድረግ እብጠቱ እስኪቀንስ የተወሰኑ ቀናት መቆየት የነበረበት አቡበከር አሁን ላይ ምርመራውን አድርጎ ውጤቱን አውቋል። በዚህም መሰረት የደረሰበት ጉዳት ከአራት እስከ ስድስት ሳምንታት ከሜዳ ሊያርቀው እንደሚችል ከተጨዋቹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በተጨማሪም የቁርጭምጭሚት ስፔሻሊስት ዶክተር ጋር ቀርቦ እንደሚታይም ጨምሮ ነግሮናል።