በባህር ዳር ከተማ ሲሰጥ የሰነበተው የካፍ \’ሲ\’ ላይሰንስ ሥልጠና ዛሬ ተጠናቋል

ካፍ ባወጣው አዲሱ ስምምነት መሠረት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከአማራ ክልል የእግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በባህር ዳር ከተማ ያዘጋጁት የካፍ \’ሲ\’ ላይሰንስ ሥልጠና ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ባወጣው ስምምነት መሠረት የተቀመጡ የኮርስ ርዕሶችን በመሸፈን አሰልጣኞቹ ሳይንሳዊ መሠረት እና ተከታታይነት ያለው በዕውቀት የታገዘ ሥልጠና መስጠት እንዲችሉ የማገዝ እና ብቁ የማድረግ ዓላማን ይዞ ለሦስት ወራት ያህል ሲሰጥ የሰነበተው ሥልጠና ዛሬ የአማራ ክልል ወጣትና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዕርዚቅ ኢሳ ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ለሠልጣኞቹ የምስክር ወረቀት በመስጠት ተጠናቋል።

\"\"

ሥልጠናው ሦስት ሞጁሎችን ይዞ እያንዳንዱ ሞጁል ለሰባት ቀናት ሲሰጥ በየሳምንቱ ሃምሳ ስድስት (56) ሰዓታትን በፅንሰ ሀሳብ እና ተግባር ትምህርቶች ተሸፍኗል። አንደኛው ሞጁል ተሰጥቶ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ከመምጣታቸው በፊት ሁሉም ሰልጣኞች በሚገኙበት አካባቢ የሚሠሩትን ሥራ ሠርተው ሲመጡ ሁለተኛውንም ወስደው ሦስተኛውን ምዕራፍ ከመምጣታቸው በፊት እንዲሁ የቤት ሥራ ተሰጥቷቸው በየክለቡ ፣ በየአካባቢው ወይም በየፕሮጀክቱ የሠሩትን ሥራ ሪፖርታቸውን ይዘው የሚቀርቡበት ሲሆን ትምህርቱ ከተግባር ጋር እየተዛመደ የዕለት ከዕለት ክትትል ግምገማ እንደሚካሄድበት ተጠቁሟል።

በእያንዳንዱ ሞጁል የአንድ ወር ቆይታ በአጠቃላይ ሦስት ወራትን በፈጀው ሥልጠና በአብዛኛው የተሟሉ ትምህርቶችን መሰጠታቸው ሲገለጽ ከኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በተጨማሪ ኢንስትራክተር ዳንኤል ፣ ኢንስትራክተር ሰላም ዘርዐይ ፣ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ትምህርቱን ሲሰጡ ኮርሱን በማስተባበር የተሳካ እንዲሆን ደግሞ የፌዴሬሽኑ የትምህርት እና ስልጠና ኃላፊ አቶ ደረሰ መሳተፋቸው ተገልጿል። ከእግርኳሱ ሙያ ውጪ ላሉ ትምህርቶች ዶክተር ተስፋዬ ፤ ዳኝነትን በተመለከተ ደግሞ  ኢንተርናሽናል ዳኛ ዶክተር ኃይለየሱስ ባዘዘውም ተሳትፎ ማድረግ ችለዋል። ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ \”የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ፈርማ ወደ ሥራ እንድንገባ ማድረግ በመቻላቸው እና ላደረጉት የቅርብ ክትትል ማመስገን እፈልጋለሁ\” በማለትም ሀሳባቸውን አጠናቅቀዋል።

ኮርሱ ሲጀመር ለ ሠላሳ (30) ሰዎች ተፈቅዶ የነበር ሲሆን በስምምነቱ መሠረት ጥቂት ሠልጣኞች በተለያዩ ምክንያቶች ያላሟሉ ስለነበሩ ከታህሣሥ 19 እስከ ታህሣሥ 26 ድረስ የተሰጠውን የመጨረሻ ስልጠና 22 ሰልጣኞች መጨረሳቸው ሲገለጽ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በተሰጠው መመዘኛ መሠረት የሚያልፉት ሪፖርቱ ለካፍ ከተላከ በኋላ የሚታወቅ ይሆናል።

\"\"

ይሄ ሥልጠና ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በተጨማሪ ከተባበሩ አካላት መካከል ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንስትራክተሮችን የሆቴል እና መስተንግዶ ወጪ  በመሸፈን እገዛ ሲያደርግ የባህር ዳር ከተማ እግርኳስ ክለብ ደግሞ ለሥልጠናው የሚያስፈልጉ የሥልጠና ማቴሪያሎችን በመስጠት እና ለሰልጣኞች ሁለት ዓይነት ዩኒፎርም ማዘጋጀታቸው ተገልጾ ምስጋና ቀርቦላቸዋል።

ሠልጣኞች ስልጠናውን ለሰጧቸው አካላት በገዳም አባቶች የተሠሩ የባህል አልባሳትን በስጦታ መልክ አበርክተው መርሐግብሩ ተጠናቋል።