የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ተጋርቷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲደረጉ አዲስ አበባ ከተማ እና ልደታ ክፍለ ከተማ ሲያሸንፉ መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተፈትኖ አቻ ተለያይቷል።

\"\"

የመዲናይቱን ክለብ አዲስ አበባ ከተማ እና የምስራቁን ድሬዳዋ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚው መርሀግብር ነበር። በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የነበራቸው ቢሆንም ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ደርሶ በተጋጣሚ ላይ ጫናን በማሳደሩ የአሰልጣኝ አብዱራህማን ዑስማኑ ቡድን አዲስ አበባዎች በእጅጉ የተሻሉ ሆነው ቀርበዋል።

በእንቅስቃሴ ብቻ ተገድቦ ከነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ይበልጥ በጎል ሙከራዎች የደመቀው ሁለተኛው አርባ አምስት በተለይ አዲስ አበባ ከተማዎች የመረጡት የመስመር አጨዋወታቸው የኋላ ኋላ አዋጭ ሆኖላቸዋል። 

መሀል ሜዳ ላይ ብቻ ተከማችተው ቅብብሎች ከማድረግ ውጪ የአዲስ አበባን የተከላካይ ክፍል ለማስከፈት ውስንነቶች የሚታይባቸው ድሬዳዎች በመስመር በኩል በተደጋጋሚ በሚደረግባቸው ጥቃቶች ጎልን አስተናግደዋል። 60ኛው ደቂቃ ላይ ቤቴልሔም መንተሎ የግል ብቃቷን በሚገባ ተጠቅማ ያቀበለቻትን ሰርካዲስ ጉታ ከመረብ በቀላሉ አገናኝታው ቡድኗን ቀዳሚ አድርጋለች። በተጋጣሚያቸው ደካማ የጨዋታ አቀራረብ የተነሳ ከመስመር አጨዋወት በተጨማሪ ኪፊያ አብዱራህማንን ቀይረው በማስገባት መሀል ሜዳው በእጃቸው ያስገቡት አዲስ አበባ ከተማዎች 75ኛ ደቂቃ በፈጠሩት ጫና ሰርካዲስ ጉታ ለራሷም ለቡድኗም ሁለተኛ ጎል አክላ ጨዋታው 2-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

\"\"

ከቀትር በኋላ ጠንካራ ፉክክርን ያስመለከተን ሊጉን እየመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገናኘው ጨዋታ በበርካታ ተመልካቾች ታጅቦ የእንስት ፈረሰኞቹን አስገራሚ ብቃት አስመልክቶን የተጠናቀቀ ሆኗል። በመጀመሪያው አርባ አምስት ኳስን ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በአንድ ሁለት በመቀባበል የንግድ ባንክን ስህተት ተጠቅመው ጎል ለማስቆጠር ጊዮርጊሶች ተደጋጋሚ ጥረቶች ያልተለያቸው ሲሆን በአንፃሩ ከወትሮ አቅማቸው በአጋማሹ በእጅጉ የተቀዛቀዙት ንግድ ባንኮች እምብዛም ስኬታማ ቆይታን ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። በእንቅስቃሴ ብልጫ የነበራቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያደረጉትን ጥረት ተከትሎ ወደ መልበሻ ክፍል ጨዋታው ሊያመራ ሁለት ያህል ደቂቃ እየቀረው እየሩስ ወንድሙ የፈጠረችላትን ዕድል ተጠቅማ ገብርኤላ አበበ በጥሩ አጨራረስ ኳስ እና ከመረብ አገናኝታለች።

ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያው አጋማሽ በቅዱስ ጊዮርጊስ ለመበለጥ የተገደዱት እና ጎልንም ሊያስተናግዱ የቻሉት ንግድ ባንኮች አከታትለው የተጫዋች ለውጥን ካደረጉ በኋላ ጨዋታውን በአመዛኙ መቆጣጠር ቢችሉም ተጫዋችን ማርክ በማድረግ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት በሚሞክሩት የአሰልጣኝ ራውዳ አሊው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመፈተን ወደ ኋላ አላሉም። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊገባደድ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው በተጫዋች የአቋቋም ስህተት መነሻነት የተገኘችን ዕድል ሎዛ አበራ ከሳጥን ውጪ አክርራ በመምታት ጎል አስቆጥራ በመጨረሻም 1-1 ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።

የ10ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሀግብር የሆነው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ እና ልደታ ክፍለ ከተማ ጨዋታ ደብዛዛ ለዕይታ ብዙም ሳቢ ያልነበረን 90 ደቂቃ አሰመልክቶን የተጠናቀቀ ነበር። ረጃጅም ኳሶች በተበራከቱበት የሁለቱ ቡድኖች ሁለት የጨዋታ አጋማሾች 31ኛ ደቂቃ ላይ ሔርሜላ ይገዙ ላፍቶን መሪ ማድረግ ብትችልም አለሚቱ ድሪባ እና መሠረት ምክሬ ከመረብ ያገናኟቸው ሁለት የመጀመሪያው አጋማሽ ጎሎች ልደታ ክፍለ ከተማ 2-1 አሸናፊ ሆኖ ጨዋታው ተደምድሟል።