ከፍተኛ ሊግ | የ8ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በሦስቱ ምድቦች በተደረጉ 11 ጨዋታዎች ሲቀጥል ቤንች ማጂ ቡና እና ሻሸመኔ ከተማ የየምድቦቻቸውን መሪነት ያስቀጠሉ ድሎች አስመዝግበዋል።

በቶማስ ቦጋለ እና ጫላ አቤ

የጠዋት ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ ቤንች ማጂ ቡና እና ሀላባ ከተማን ባገናኘው ቀዳሚ ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ሀላባዎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ግን አደገኛ እና ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቁት ቤንች ማጂዎች የተሻሉ ነበሩ። 11ኛው ደቂቃ ላይም ዘላለም በየነ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር አቦሎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። በኳስ ቁጥጥሩ እንደወሰዱት ብልጫ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ሀላባዎች በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራ 39ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ዘኪ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ሀላባዎች ተሻሽለው ሲቀርቡ 58ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ከማቀበል አማራጭ ጋር ለማስቆጠር ምቹ አጋጣሚ ያገኘው አቡሽ ደርቤ በደካማ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በአምስት ደቂቃዎች ልዩነት ግን ቡድኑን አቻ ያደረገች ግብ ረጀብ ሚፍታ ሙሉቀን ተሾመ ላይ በሰራው ጥፋት ከተገኘ የፍጹም ቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የቀረቡት አቦሎቹ ባልታሰበ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ሀላባዎች ትኩረት ባጡበት ቅፅበት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ግብ ጠባቂው መስፍን ሙዜ በረጅሙ የመታውን ኳስ ያገኘው የሀላባው ተከላካይ ሞገስ ቱምቻ  በጭንቅላቱ ወደኋላ በመግጨት ለግብጠባቂ ሲያቀብል እጅግ አስደናቂ በሆነ ፍጥነት ኳሱን አቋርጦ ያገኘው እሱባለው ሙሉጌታ ድንቅ በሆነ አጨራረስ አስቆጥሮ ክለቡን የ 2-1 ድል እንዲቀዳጅ አስችሏል። በዚህም ውጤት ምድቡን በ20 ነጥቦች መምራቱን ቀጥሏል።

\"\"

ጅማ ላይ በምድብ \’ለ\’ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሀን እና ካፋ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ ለ69 ደቂቃዎች 0-0 ቢዘልቅም ከዚያ በኋላ ግን አራት ግቦችን አስተናግዷል። ካፋ ቡናዎች ገዛኸኝ ፍቃዱ 69ኛው እንዲሁም ዮናታን ከበደ 76ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠሯቸው ግቦች ጨዋታውን ለማሸነፍ ቢቃረቡም ሰሜን ሸዋዎች ተመሳሳይ ማላሽ ሰጥተዋል። በዚህም 79ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ብርሀኑ እንዲሁም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ መስፍን ኪዳኔ ኳስ እና መረብን አገናኝተው ጨዋታው 2-2 ተጠናቋል።

በምድብ \’ሐ\’ ዘግየት ብሎ 04:00 ላይ ቀዳሚው ጨዋታ ሲከናወን ስልጤ ወራቤ እና የነገሌ አርሲ ተጋጣሚዎቹ ነበሩ። በመጀመሪያው አጋማሽ ፈጣን እና ለዐይን ማራኪ የሆነው ጨዋታ በዛ ያለ የግብ ሙከራዎች ያየንበት እና በጨዋታው እስከ 30 ደቂቃ ባመዛኙ የስልጤ ወራቤ የበላይነት የታየበት ነበር። በዚህም አጨዋወት በ28ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል እና በነጌሌ አርሲዎች የተከላካይ ክፍል መሀል የተሻገረውን ኳስ የስልጤ ወራቤ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ማታያስ ኤልያስ በማስቆጠር ስልጤ ወራቤን መሪ ማድረግ አስችሏል። ብዙም ሳይቆይ ነጌሌ አርሲዎች ግብ ለማስቆጠር ጥረት እያደረጉ ሳለ በ32ኛው ደቂቃ በስልጤ ወራቤ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ያሬድ መሀመድ ሰብሮ ለማለፍ ሲጥር በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት በራሱ በያሬድ መሀመድ አማካኝነት በማስቆጠር ነጌሌ አርሲን አቻ ማድረግ ችሏል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ቅያሬ አድርገው የገቡት ነጌሌ አርሲዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የተመለከትን ሲሆን በአንፃሩ ስልጤ ወራቤዎች ቀዝቀዝ ባለ መልኩ ጨዋታቸውን ሲያከናውኑ ተስተውሏል። ሁለተኛው አጋማሽም ምንም ግብ ሳይቆጠር ቡድኖቹ በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች ነጥብ ተጋርተው ሊወጡ ችለዋል። ወጤቱን ተከትሎ ስልጤ ወራቤ ለአራተኛ ግዜ ነጥብ ተጋርቶ መውጣት የቻለ ሲሆን በነጌሌ አርሲ በኩል ከሦስት ተከታታይ ድል በኋላ ነጥብ ሊጋራ ችሏል።

የ05:00 ጨዋታዎች

ረፋድ ላይ በባህር ዳር ንግድ ባንክ እና ወሎ ኮምቦልቻ ሲገናኙ ብርቱ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት ወሎ ኮምቦልቻዎች 11ኛው ደቂቃ ላይ ሲሳይ አቡሌ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይረጋጋ መትቶት ባባከነው ኳስ የጨዋታውን የተሻለ የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። 28ኛው ደቂቃ ላይ የንግድ ባንክ ተጫዋቾች ትኩረት ባጡበት ቅፅበት ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው ሰለሞን ጌዲዮን ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል። ይሄም በኮምቦልቻዎች በኩል ትልቁ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።

\"\"

በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ንግድ ባንኮች 31ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። የወሎው ግብጠባቂ አቤል አራጋው አቤል ማሙሽ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ልዑልሰገድ አስፋው ማስቆጠር ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተደጋጋሚ በሚከሰቱ አካላዊ ንክኪዎች ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በኮምቦልቻዎች በኩል ሰለሞን ሀብቱ በግራ መስመር የተገኘውን  የቅጣት ምት በጠበበው የግቡ ቋሚ ሲሞክር ግብ ጠባቂው መቆጣጠር ቢሳነውም ወደ ውጪ የወጣው በንግድ ባንኮች በኩል ደግሞ 92ኛው ደቂቃ ላይ ከዓባይነህ ፊኖ ኳስ የተቀበለው ሀይከር ዶዋሞ ከጨዋታ ውጪ ነኝ ብሎ በማሰብ እና ዘግይቶም ደካማ ሙከራ በማድረግ ያባከነው ትልቅ የግብ ዕድል በአጋማሹ የተፈጠሩ ግልፅ የግብ ዕድሎች ነበሩ። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ንግድ ባንክ መሪው ቤንች ማጂ ቡናን በሦስት ነጥብ ርቀት መከተሉን ቀጥሏል።

\"\"

በምድብ ለ ጅማ ላይ ንብ ተከታታይ ድል ያሳካበትን ውጤት አስመዝግቧል። ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ መምጣት የቻለው ቡድኑ ጂንካ ከተማን 2-0 መርታት የቻለ ሲሆን ናትናኤል ሰለሞን እና ኤልያስ እንድሪስ ግብ አስቆጣሪዎቹ ሆነዋል።

የ08:00 ጨዋታዎች

ከምሳ መልስ በምድብ ሀ ቡታጅራ ከተማ እና ዱራሜ ከተማ ተገናኝተዋል። ቀዝቃዛ የነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል የጠሩ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። የቡታጅራው ክንዴ አብቹ 33ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት እና ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከክፍት ጨዋታ ያደረጋቸው ሙከራዎች በአጋማሹ የተሻሉ ሙከራዎች ነበሩ። በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ዱራሜዎች ቦታዎችን በመቃኘቱ እና እርስ በርስ በመግባባት በኩል ያላቸው ደካማ እንቅስቃሴ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ እንዲቸገሩ አድርጓል።

ከዕረፍት መልስም በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ ጥሩ ፉክክር ቢኖርም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ግን አላስመለከተንም። 72ኛው ደቂቃ ላይም ዱራሜዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሚፍታ መሐመድ ኪሩቤል ካሳ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ምሕረቱ አሼቦ ማስቆጠር ችሏል። ቡታጅራዎች በጨዋታው የተሻለውን ሙከራ 87ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ሔኖክ መርሹ ከረጅም ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ቢሞክርም የላዩን የግቡ አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶበታል። ጨዋታውም በዱራሜ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጅማ ላይ አዲስ አበባ ከተማ ራሱን በፉክክሩ ውስጥ ያስቀጠለበትን ድል አሳክቷል። ውጤቱን ተከትሎ በ13 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻለው ቡድኑ ሙሉቀን ታሪኩ እና አዲስዓለም ዘውዴ በሁለቱ አጋማሾች ባስቆጠራቸው ግቦች ሺንሺቾ ከተማን 2-0 አሸንፏል።

ሆሳዕና ላይ የዕለቱ የምድብ \’ሐ\’ ሁለተኛ እና ወሳኝ ጨዋታ የሆነው የገላን ከተማ እና የደሴ ከተማ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ የተካሄደበትና በዛ ያለ የግብ ሙከራ የተመለከትንበት ሲሆን በተስሎች ሳይመን የሚመራው የደሴ ከተማ የመሀል ሜዳ የበላይነት የታየበት እና የተሻለ ግብ ሙከራዎችን ያደረጉበት ነበር። ሆኖም ግን ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
\"\"

በሁለተኛው አጋማሽም ደሴ ከተማዎች በተወሰነ መልኩ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን በ65ኛው ደቂቃ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት በማናዬ ፋንቱ አማካኝነት በማስቆጠር መሪ መሆን ችለዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ መነቃቃት የታየባቸው ገላን ከተማዎች በ79ኛው በጥሩ ቅብብል ያገኙትን የግብ ዕድል በያሬድ ወንድማገኝ አማካኝነት ወደ ግብ በመቀየር ከሽንፈት ማዳን ችለዋል። ጨዋታውም በዛው ውጤት በመጠናቀቁ ቡድኖቹ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። ደሴ እና ገላን ነጥብ በመጋራታቸው ከመሪው ሀምበርቾ ጋር ያላቸውን ልዩነት መቀነስ ሳይችሉ በ13 ነጥቦች መከተላቸውን ቀጥለዋል።

የ10:00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ የሚደረገው የምድብ ሀ ውድድር ዛሬ በመጨረሻ ያስተናገደው የሰንዳፋ በኬ እና ባቱ ከተማን ጨዋታ ሆኗል። መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በቀጥተኛ ኳስ  የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ሲሞክሩ ቶሎ ቶሎ በሚቆራረጠው ቅብብላቸው የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረዋል። የባቱ ከተማው ዮናታን አምባዬ በግንባሩ የገጨውና ግብ ጠባቂው የመለሰበት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ፈታኝ ሙከራ  ነበር። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት እጅግ የተቸገሩት ሰንዳፋዎች በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራ 13ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ መሳይ ሰለሞን በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ግብ ሲመታ ግብጠባቂው መልሶበታል።

\"\"

ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ለተመልካች እጅግ አዝናኝ ሆኖ ሲቀጥል በሁለቱም በኩል ተቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት ሦስት ተጫዋቾች ግብ አስቆጥረዋል። በቅድሚያም ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ክንዳለም ፍቃዱ ከሳጥን ውጪ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ባቱ ከተማን መሪ ሲያደርግ በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ሂኒካ ሄይ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶት የላዩ አግዳሚ ሲመልሰው በድጋሚ አግኝቶት በማስቆጠር የአሳዎቹን መሪነት አጠናክሯል። በተደጋጋሚ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት ባቱዎች በሂኒካ ሄይ በተመስገን ቃቤቶ እና በተስፋዬ በቀለ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለውም ነበር።

በጨዋታው የመጨረሻ 20 ደቂቃዎች ሰንዳፋ በኬዎች ፍፁም የበላይነቱን መውሰድ ሲችሉ 81ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ጸጋዬ ያስቆጠራት ግብ ቡድኑን ለባዶ ከመሸነፍ ከማዳን የዘለለ ፋይዳ ሳይኖራት ጨዋታውም በባቱ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ባቱ ከተማ ነጥቡን 15 በማድረስ ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።

ጅማ ላይ የተደረገው የመጨረሻ ጨዋታ መሪው ሻሸመኔ ከተማ አንደኝነቱን ያስጠበቀበት ሆኖ ተጠናቋል። 15ኛ ደቂቃ ላይ የተቆጠረችው የአሸናፊ ጥሩነህ ጎል ሻሸመኔ ቦዲቲ ከተማን 1-0 እንዲያሸንፍ አድርጋለች። ይህንን ተከትሎም ቡድኑ ነጥቡን 19 በማድረስ ምድቡን መምራቱን ቀጥሏል።

በምድብ \’ሐ\’ የዕለቱ የመጨረሻ  ጨዋታ ዳሞት ከተማ እና የጅማ አባ ጅፋር ተገናኝተዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ትንቅንቅ የታየበትና የጅማ አባ ጅፋር የበላይነት ያመዘነበት ነበር። ጅማዎች ብዙ የግብ ዕድል የፈጠሩ ቢሆንም ያገኙትን ዕድል መጠቀም የተሳናቸው ሲሆን ዳሞት ከተማዎችም አልፎ አልፎ የሚያገኙትን የመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ይስተዋላል። በ38ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን የመዕዘን ምት የዳሞት ከተማ ተጨዋች የሆነው ኪዳነ ማሪያም ተስፋዬ ቀጥታ ከመዕዘን ምት መቶ ግሩም ግብ አሰቆጥሮ ዳሞት ከተማን መሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን በዚህም ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛ አጋማሸ ጅማ አባ ጅፋሮች ግብ ለማስቆጠር የበለጠ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን በአንፃሩ ዳሞት ከተማዎች በመጀመሪያ አጋማሽ ያገቡትን ግብ ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በ78ኛው ደቂቃ የዳሞት ግብ ጠባቂ ኳስን ከ6 ሰኮነድ በላይ በእጁ ላይ በማቆየቱ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በተሰጠው ሁለተኛ የቅጣት ምት ሚኪያስ ግርማ ቀጥታ በማስቆጠር ጅማ አባ ጅፋርን አቻ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ተጠናቋል።