ቻን | የዋልያዎቹ ተጋጣሚዎች የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች አድርገዋል

በኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙት አልጄሪያ፣ ሊቢያ እንዲሁም ሞዛምቢክ ትናንት እና ከትናንት በስትያ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች አድርገዋል።

\"\"

የፊታችን ዓርብ የሚጀምረው የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒየን ሺፕ ውድድር ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአልጄሪያ፣ ሞዛምቢክ እና ሊቢያ ጋር የተደለደለች ሲሆን ለውድድሩም የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅቷን ሞሮኮ ላይ እያደረገች ትገኛለች። ብሔራዊ ቡድናችንም በትናንትናው ዕለት ከሞሮኮ የቻን ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጎ በሁለተኛው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ በተቆጠረበት ግብ አንድ ለምንም ተሸንፏል።

በዚሁ ምድብ የምትገኘው ሊቢያ በሳምንቱ አጋማሽ ከአይቮሪኮስት ጋር ተጫውታ የተረታች መሆኑን ዘግበን ነበር። ቱኒዚያ ላይ የምትገኘው ሊቢያ ትናንት ደግሞ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ሌላ ጨዋታ አድርጋ 3ለ1 በሆነ ውጤት ተሸንፋለች።

ለውድድሩ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠችው አልጄሪያ በበኩሏ በውቡ ስታዲየሟ ትናንት ምሽት 1 ሰዓት ጋናን ገጥማ ያለ ግብ ተለያይታለች። በጨዋታው አልጄሪያ ግልፅ የግብ ማግባት ዕድሎችን በሚገባ መፍጠር አልቻለችም። ቡድኑም ተከታታይ ያደረጋቸውን የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች አለማሸነፉ ደጋፊዎችን ሀሳብ እንደገባ እየተጠቀሰ ይገኛል።

\"\"

ቀድማ የውድድሩ ስፍራ የደረሰችው ሞዛምቢክ ደግሞ ከትናንት በስትያ ከኤም ሲ አልጀርስ ክለብ ጋር ተጫውታ 3ለ1 በሆነ ውጤት የተረታች ሲሆን ዛሬ ደግሞ ከቤሉይዝዳድ ወጣት ሁለተኛ ቡድን ተጨማሪ ጨዋታ ታደርጋለች።