ከፍተኛ ሊግ | የ8ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ዛሬ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ የምድብ ሦስት መሪው ሀምበርቾ ዱራሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጥብ ጥሏል።

በቶማስ ቦጋለ እና ጫላ አቤ

የ04:00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ የምድብ \’ሀ\’ ጨዋታዎች አዲስ ከተማ ክፍለከተማ እና ሰበታ ከተማን ባገናኘው ፍልሚያ ጀምረዋል። ሁለት ዓይነት መልክ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ሰበታዎች በጥሩ ቅብብል በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ችለው ነበር። በተለይም 25ኛው ደቂቃ ላይ ገዛኸኝ ባልጉዳ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ በዘገየ ውሳኔ ያመከነው ኳስ በአጋማሹ የፈጠሩት ትልቁ የግብ ዕድል ሲሆን ዮናስ ሰለሞን ከዓለምአንተ ካሳ የተሻገረለትን ኳስ በአየር ላይ እንዳለ መትቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ይዞበታል። በቀሪ 15 ደቂቃዎች ግን አዲስ ከተማዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ጨዋታውን መቆጣጠር ችለዋል። 41ኛው ደቂቃ ላይም አሸናፊ በቀለ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ዕይታ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ አዲስ ከተማዎች በተሻለ የጨዋታ ስሜት አጋማሹን መርተው እንዲወጡ አስችሏል።

\"\"

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ሰበታዎች ተሻሽለው በመቅረብ ብልጫውን ቢወስዱም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ግን መቸገራቸውን ቀጥለዋል። 59ኛው ደቂቃ ላይ ምትኩ ጌታቸው  ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ ሲወጣበት 73ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ግርማ በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ሞክሮት ግብጠባቂው አስወጥቶበታል። የነበራቸው የጨዋታ ግለት ቀስ በቀስ እየጠፋባቸው የሄዱት አዲስ ከተማዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በተረጋጋ አጨዋወት ውጤቱን ለማስጠበቅ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ጨዋታውን በአዲስ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

ጅማ ላይ የምድብ \’ለ\’ ቀዳሚ ጨዋታ ያልተጠበቀ ውጤት ተመዝግቦበታል። የመጨረሻ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረው ጉለሌ ክፍለከተማ በጁንዴክስ አወቀ ብቸኛ ግብ ነቀምት ከተማን 1-0 መርታት ችሏል። በመሆኑም ነቀምት ከመሪው ሻሸመኔ ከተማ ጋር ያለው ልዩነት ወደ አራት ነጥቦች እንዲሰፋ ተገዷል።

ሆሳዕና ላይ የምድብ \’ሐ\’ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ መሪው ሀምበሪቾ ዱራሜ እና የኮልፌ ክፍለከተማን አገናኝቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ እንደተለመደው ጨዋታቸውን በርከት ባሉ ደጋፊዎች የጀመሩት ሀምበሪቾ ዱራሜዎች በተወሰነ መልኩ የተሻለ አጨዋወት ያደረጉበት እና ኮልፌ ክ/ከተማም ጥሩ እንቅስቃሴ የታየበት ቢሆንም ብዙ የሚባል የግብ ሙከራ ያልታየ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽ ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ጥሩ የሚባሉ እንቅስቃሴዎች እና የግብ ሙከራዎች የተመለከትንበት ሲሆን ቀድመው ግብ ማስቆጠር የቻሉት ኮልፌዎች በ53ኛው ደቂቃ ከርቀት አክርረው የተመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲመለስ የኮልፌው ተጫዋች የሆነው ፊሊሞን ገ/ፃዲቅ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ነገር ግን ኮልፌዎች መሪ መሆን የቻሉት ለአንድ ደቂቃ ብቻ ሲሆን በ54ኛው ደቂቃ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች የፈጠሩትን የግብ ዕድል ልማደኛው ዳግም በቀለ በማስቆጠር በፍጥነት አቻ ማድረግ ችለዋል። ጨዋታውም ሌላ ግብ ሳይታይበት በአቻ ውጤት መጠናቀቅ ችሏል። የጨዋታውን ውጤት ተከትሎ ኮልፌ ክ/ከተማ ከነበረው ነጥብ ላይ አንድ ነጥብ በመጨመር ነጥቡን ከፍ ማድረግ ሲችል መሪው ሀምበሪቾ ዱራሜ የማሸነፍ ጉዞው ቢገታም አሁንም በመሪነቱ ቀጥሏል።

የ08:00 ጨዋታዎች

ጋሞ ጨንቻ እና ጅማ አባ ቡና በምድብ \’ሀ\’
የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ተገናኝተዋል። በጨዋታው መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ጋሞ ጨንቻዎች ከወትሮው በተለየ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ተዳክሞ ታይቷል። በአንፃሩ አስፈሪ ያልሆነ ግን በተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት አባ ቡናዎች 22ኛው ደቂቃ ላይ ቴድሮስ ገ/እግዚአብሔር ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶት የግቡን የቀኝ ቋሚ ታክኮ በወጣው ኳስ በጨዋታው የተሻለውን የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። 27ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታውን መምራት የሚችሉበትን ትልቅ አጋጣሚ አባክነዋል። ሰይፉ ታከለ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ  የመታው ኳስ ከግብጠባቂው ቢያልፍም አማኑኤል ተፈራ በእጁ መልሶበታል። ይህ ድርጊቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወገድ ሲያደርገው የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ግሩም ኩሩጌታ ሲመታ የግቡ የላዩ አግዳሚ መልሶበታል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ በተጫዋች ቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ጋሞ ጨንቻዎች ከተጠበቁት በላይ ፈታኝ ሆነው ሲቀርቡ የነበራቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ እየተዳከመ የሄደባቸው ጅማዎች በአንፃሩ 56ኛው ደቂቃ ላይ ተምክን ፈቱ ከረጅም ርቀት አክርሮ መትቶት ግብ ጠባቂው ከያዘው ኳስ ውጪ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረዋል። ጋሞዎች 68ኛው ደቂቃ ላይ የጅማው ተከላካይ ርሆቦት ሰላሎ በግንባሩ በመግጨት ለግብ ጠባቂው ለማቀበል ሲሞክር ኳሱን አቋርጦ ያገኘው ፍስሐ ቶማስ ከግብጠባቂው ከፍ አድርጎ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ሬዳውና ሸሪፍ በፍጥነት ደርሶ ኳሱን በግንባሩ በመግጨት አስወጥቶታል። ጨንቻዎች በተደጋጋሚ የተጋጋሚ የግብ ክልል ሲደርሱ 90ኛው ደቂቃ ላይ ታደለ ታንቶ ፈታኝ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ሌሊሣ ታዬ በጥሩ ቅልጥፍና በእግሩ መልሶበታል። ጨዋታውም ያለግብ ተጠናቋል።

\"\"

በምድብ \’ለ\’ የከሰዓት ጨዋታ ቂርቆስ ክፍለከተማ እና አምቦ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ ቂርቆስ አሸናፊ ሆኗል። አምቦ ጫላ ከበደ በመጀመሪያው አጋማሽ ማብቂያ ላይ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ ቢሆንም ቂርቆሶች 79ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልመጂድ ሁሴን አቻ ሲያደርጋቸው ክብሮም ፅደቅ በጭማሪ ደቂቃ ጋር ከመረብ ባገናኛው ሌላ ጎል 2-1 መርታት ችሏል።

ሆሳዕና ላይ የየካ ክፍለከተማ እና የሶዶ ከተማ ጨዋታ 08:00 ላይ ተደርጓል። የመጀመሪያ አጋማሽ ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት እና በአብዛኛው የየካ ክ/ከተማ የበላይነት የታየበት ሲሆን በግብ ሙከራም ቢሆን የየካ ክ/ከተማ የበላይነት ታይቷል። በ15ኛው ደቂቃ በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ሲያደርግ የነበረው የየካ ክ/ከተማው ተጫዋች ፉዐድ መሐመድ ግብ በማስቆጠር መሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ በ19ኛው ደቂቃ ዲንግ ኪር ግብ በማስቆጠር የካ ክ/ከተማን በሁለት ግብ ልዩነት እንዲመራ ማድረግ ችሏል። ከሁለተኛው ግብ መቆጠር በኋላ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት እና የግብ ሙከራ በሁለቱም በኩል የተመለከትን ቢሆንም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በየካ ክ/ከተማ መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ የካ ክፍለከተማዎች የያዙትን ውጤት ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አፈግፍገው የሚያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ተስተውሏል። ሶዶ ከተማም ግብ ለማስቆጠር ተጭነው ለመጫወት የሞከሩ ቢሆንም ምንም ግብ በሁለቱም ክለብ ሳየቆጠር በመጀመሪያው አጋማሽ ውጤት ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል። የውጤት ቀውስ ውስጥ የገባው ሶዶ ከተማ በዛሬው ዕለት ስድስተኛ ሽንፈቱን በማስተናገድ የደረጃው ግርጌ ላይ ለመቆየት ተገዷል። በአንፃሩ የካ ክ/ከተማ የዛሬውን ድል ተከትሎ ነጥቡን ወደ 12 ከፍ ማድረግ ችሏል።

የ10:00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ የምድብ \’ሀ\’ የስምንተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በአቃቂ ቃሊቲ እና ወልዲያ መካከል ተደርጓል። በመጀመሪያው አጋማሽ ወልዲያዎች የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ይቸገሩ እንጂ በተደጋጋሚ ከተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ መድረስ ችለው ነበር። 23ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር የተሻማውን የማዕዘን ኳስ ተጨርፎ ያገኘው ፀጋዬ ባልቻ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም ዒላማውን ስቶበታል። የመሃል ሜዳው ላይ በተረጋጋ የኳስ ቅብብል ዝግ ባለ ሂደት የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የፈለጉት አቃቂዎች ለአጥቂዎቻቸው የግብ ዕድል ለመፍጠር እጅግ ሲቸገሩ ተስተውሏል። 15ኛው እና 36ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ያለው ከረጅም ርቀት አክርሮ በመምታት ድንቅ ሙከራዎችን ቢያደርግም የግቡን የግራ ቋሚ ታክከው ወጥተውበታል።

\"\"

ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ዳኝነት ላይ በሚቀርቡ ቅሬታዎች ታጅቦ ሲቀጥል በሁለቱም በኩል ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። በወልዲያዎች በኩል በሦስት አጋጣሚዎች የፍፁም ቅጣት ምት ይገባናል ከፍተኛ ቅሬታዎች ሲቀርቡ የጨዋታው ግለት እና ውጥረቱ እየጨመረ ሲሄድ ወልዲያዎች 84ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ያደረገቻቸውን ግብ አስቆጥረዋል። በቀኝ መስመር የተሰጠውን የቅጣት ምት ወንድማገኝ ሌራ ሲያሻማ ያገኘው ፀጋ ማቲዎስ ማስቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ግቡ ተገቢ አይደለም በሚል በአቃቂ ቃሊቲዎች በኩል እጅግ ከፍተኛ ተቃውሞ ተሰምቷል። ጨዋታውም በወልዲያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጅማ ላይ ከምሳ በኋላ በተደረገው ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡና እንጅባራ ከተማን 2-1 ማሸነፍ ችሏል። ውጤቱን ተከትሎ ቡድኑ ነጥቡን 15 በማድረስ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሆሳዕና ላይ በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሮቤ ከተማ እና የቡራዩ ከተማ ሲገናኙ ትንቅንቅ እና አልሸነፍ ባይነት የታየበት ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ ፈጣን እንቅስቃሴ እና ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የመድረስ እንቅስቃሴ አሳይቶናል። በ14ኛው ደቂቃ የሮቤ ከተማ ተጫዋች የሆነው ዮናስ ታዬ በጥሩ ቅብብል የተገኘውን የግብ ዕድል በማስቆጠር ሮቤ ከተማን መሪ ማድረግ ችሎ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

የሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ፉክክር የታየበት እና በዛ ያሉ ግቦች የተመለከትንበት አጋማሽ ሲሆን ቡራዩ ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር በተወሰነ መልኩ ተጭነው ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበረ ሲሆን በ49ኛው ደቂቃ የቡራዩ ከተማ ተጨዋቹ እንዳለማው ታደሰ አስደናቂ ግብ አስቆጥሮ አቻ አድርጓል። ብዙም ሳይቆይ በ67ኛው ደቂቃ ላይ ሶፊያን ገለቱ ሮቤ ከተማ ላይ በተሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ሮቤ ከተማን በድጋሚ መሪ አድርጓል። የጨዋታው መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ቡራዩ ከተማ በፈጠሩት ጫና የሮቤ ከተማ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ፍቃዱ አስፋው አስቆጥሮ ቡራዩ ከተማን ከሽንፈት መታደግ ችሏል።