“አሁን ባለን የቡድን ስብስብ የሊጉን ወይንም የጥሎ ማለፉን ዋንጫ እንደምናነሳ አልጠራጠርም።” – አቢኮዬ ሻኪሩ


ኢትዮጵያ ቡና የአጥቂ ችግሩን ለመቅረፍ ከውጪ ሃገር ካስፈረማቸው የፊት መስመር ተጫዋቾች አንዱ ነው። እግር ኳስን ከትውልድ ሃገሩ ናይጄሪያ እስከ መካከለኛው ምስራቋ ኦማን ድረስ ተጫውቶ አሳልፏል። ለእግር ኳሱ እጅግ ከፍተኛ ፍቅር አለው፤ “እግር ኳስ በተፈጥሮ ከፈጣሪ የተሰጠኝ ስጦታ ነው።” ይላል የዛሬው የሶከር ኢትዮጵያ እንግዳ አቢኮዬ አላዴ ሻኪሩ።

ሻኪሩ ሀምሌ 20 ቀን 1981 በቀድሞዋ የናይጄሪያ ዋና ከተማ ሌጎስ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰብ ነበር የተወለደው። በትውልድ ናይጄሪያዊ በዜግነት ቤኒናዊው አጥቂ እግር ኳስ ህይወት ጅማሬ ከአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች የተለየ አይደለም።
“እንደማንኛውም ናይጄሪያዊ ታዳጊ በሌጎስ ጎዳናዎች ላይ ኳስ በመጫወት ነው ያደግኩት። በልጅነቴ በጣም የማደንቃቸውን ብራዚላዊው አጥቂ ሮናልዶ እና ካሜሮናዊው ሳሙኤል ኤቶን ጥረት አደርግ ነበር። አንድ ቀን ሰፈር ውስጥ ስጫወት የተመለከቱኝ የፔፕሲ እግር ኳስ አካዳሚ መልማዮች ማሰልጠኛውን እንድቀላቀል ጥያቄ አቀረቡልኝ። የእግር ኳስ ህይወቴ የጀመረው በዚህ መልክ ነበር።”

ትውልደ ናይጄርያዊው ሻከሩ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለፕሮፌሽናል ተጫዋችነት ህይወት እንዲበቃ ቤተሰቦቹ፣ በተለይም ወላጅ እናቱ ያደርጉለት የነበረው ድጋፍ ወሳኝ እንደነበር ይናገራል።
“ቤተሰቦቼ በእግር ኳሱ የተሻለ ደረጃ እንድደርስ በማደርገው ጥረት ሁሉ ይደግፉኝ ነበር። እስካሁን የማይረሳኝ ፔፕሲ አካዳሚን ከተቀላቀልኩኝ በኋላ የማደርገው ጫማ ባልነበረኝ ወቅት ሁለት ጫማዎችን ገዝታ በመስጠት ያበረታታችኝ እናቴ ነበረች። እናቴ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቷ በጣም አዝናለሁ፤ እስካሁን በህይወት ብትቆይ ኖሮ በኳሱ በደረስኩበት ደረጃ ደስተኛ የምትሆን ይመስለኛል።”

በፔፕሲ እግር ኳስ ማሰልጠኛ ውስጥ ችሎታውን ማዳበር የጀመረው ታዳጊ በናይጄሪያ ፕሪምየር ሊግ የሚወዳደር ክለብ ለማግኘት ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። እ.ኤ.አ. በ2006 ዓ.ም. የክረምት የዝውውር መስኮት ስብስቡን ለማጠናከር ተጫዋቾችን እያሰሰ የነበረው ሰንሻይን ስታርስ በወጣቱ አጥቂ ችሎታ በመማረክ ክለቡን እንዲቀላቀል ጥያቄ አቀረቡለት፤ እሱም በደስታ ተቀበለው።

“ከወጣት ማሰልጠኛው ወደ ዋናው ቡድን ከተዘዋወርኩኝ በኋላ የነበረው የመጀመሪያው የውድድር ዓመት ለኔ ትንሽ ከብዶኝ ነበር። በችሎታዬ ራሴን ማሳመን መቻሌ እና ጠንክሬ መስራቴ ከአሰልጣኞቼ ካገኘሁት ድጋፍ ጋር ተጨምሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንድለምድ እና ጥሩ ብቃት እንዳሳይ አስችሎኛል።”

ሻኪሩ በ2008/09 የውድድር ዓመት ለዴልታ ፎርስ ክለብ በውሰት ተሰጥቶ ከመጫወቱ በኋላ ነበር ከሀገሩ ወጥቶ ለመጫወት ማቀድ የጀመረው፤ የመጀመሪያ ማረፊያው ደግሞ ኦማን ስፖርት ክለብ (Oman SC)። ነገሮች በኦማን እሱ እንዳሰበው የተመቻቹ አልነበሩም። ክለቡን ተቀላቅሎ ቡድኑ በኦማን ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ እንዲችል የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ቢችልም የአሰልጣኙ እና የክለቡ አመራሮች በአዲስ እንዲተኩ በመደረጋቸውና ከአዲሱ አሠልጣኝ ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር ባለመቻሉ በክለቡ የነበረው ቆይታ ከ6 ወር አላለፈም።

የሻኪሩ ቀጣይ የህይወት ምዕራፍ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ቤኒን ይወስደናል። በቤኒን ፕሪምየር ሊግ ለሚወዳደሩት ሬክዊንስ ዴል አትላንቲክ እና ቶኔሬ ድ አቦሜይ አጥቂው ድንቅ ብቃቱን ያሳየባቸው ክለቦች ናቸው። በቤኒን ሊግ ያሳየው ውጤታማ አቋም ዜግነቱን በመቀየር ኒጀር ላይ በተደረገው የ2010ሩ የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ህብረት (UEMOA) ውድድር ላይ የቤኒን ብሔራዊ ቡድንን ወክሎ እንዲሰለፍ አስችሎታል። በውድድሩም የቤኒን ብሔራዊ ቡድን እስከ ፍፃሜው ድረስ እንዲጓዝ ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል። ነገር ግን ሻኩሪ በቤኒን ብዙ መቆየት አልቻለም።

“በወቅቱ የቤኒን እግር ኳስ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ነበር። ሊጉ በመቋረጡም ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው ደሞዝ የሚከፍሉበት አቅም አልነበራቸውም። በዚህ ምክኒያት የቤኒኑን ክለብ በመልቀቅ ወደ ኦማን ሊግ በመመለስ ለሙስካት ክለብ ለ2 ዓመታት ተጫውቻለሁ። በቤኒን እግር ኳስ ውስጥ እጅግ አሳሳቢ የሆነ ችግር አለ። ጥሩ ያልሆነ አመራር እና የአሠልጣኝ እና ቴክኒክ ቡድን በተደጋጋሚ መቀያየር ብሔራዊ ቡድኑ እንኳን በአቅሙ የሚገባውን ውጤት እንዳያስመዘግብ አድርጎታል። እኔም ቢሆን ወደ ቤኒን ስመጣ በዚያ ለረጅም ጊዜ መቆየት አላሰብኩም ነበር፤ የተሻለ ክለብ ማግኘት እስክችል ድረስ አቋሜን ጠብቄ ለመቆየት ነበር ያቀድኩት።”

“ለኢትዮጵያ ቡና የፈረምኩት ባላሰብኩት መንገድ ነው። በአውሮፓዊቷ ሃገር ማልታ ሊግ ለሚወዳደር አንድ ክለብ ለመጫወት ተስማምቼ የነበረ ቢሆንም ክለቡ የስራ ፈቃዴን የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት ሊያስፈፅምልኝ አልቻለም። የውድድር ዓመቱን ልምምድ በመስራት ብቻ ከማሳለፍ ይልቅ ወደ ናይጄሪያ ሊግ ተመልሼ ለመጫወት እየተደራደርኩ ባለበት ሰዐት ከኢትዮጵያ ቡና የሙከራ ጥያቄ የደረሰኝ። የተሰጠኝን የሙከራ ጊዜ ማለፍ በመቻሌም ክለቡን ተቀላቅያለሁ።”

የ25 ዓመቱ አጥቂ እስካሁን በኢትዮጵያ ስላደረገው ቆይታ እንዲህ ይላል።
“ኢትዮጵያን በጣም ወድጃታለሁ። ከሃገሪቱ ምግብ፣ ቋንቋ፣ እና የሰዎች አመለካከት ጋር ለመለማመድም ጥረት በማድረግ ላይ ነኝ። የብቸኝነት ስሜት አይሰማኝም። በክለቤ እና በሌሎች ክለቦች ከሚገኙ ምዕራብ አፍሪካውያን ተጫዋቾች ጋር እንቀራረባለን። ከኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ጋርም መልካም ግንኙነት አለን። በጊዜ ሂደት ጥሩ ኢትዮጵያውያን ጓደኞች ይኖሩኛል ብዬ አስባለሁ። ጠንክሬ በመስራቴም በፍጥነት የኢትዮጵያ እግር ኳስን በመልመድ ላይ ነኝ። አዲስ አበባ ከባህር ወለል በላይ ያላት ከፍታ ትልቅ እንደሆነ አውቃለሁ። ይህም እንዳያስቸግረኝ እንደ ቡድን ከምንሰራው የልምምድ ክፍለ ጊዜ ውጪ በግሌ ትሬኒንግ እሰራለሁ።”
“እስካሁን ባለኝ ቆይታ ኢትዮጵያውያን እግር ኳስን በጣም እንደሚወዱ መመልከት ችያለሁ። በተለይ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ቡድናቸውን ለማበረታታት ያላቸው ተነሳሽነት ልዩ ነው። በዚህ አጋጣሚ የክለባችን ደጋፊዎችን በጣም እንደምወዳቸው ንገርልኝ።”

ሻኪሩ በኢትዮጵያ በተመለከተው የእግር ኳስ ደረጃ ደስተኛ መሆኑንም ይናገራል።
“ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ጥሩ የእግር ኳስ ችሎታ አላቸው፤ የአንዳንዶቹ የቴክኒክ ብቃትም አስገራሚ ነው። ነገር ግን በእግር ኳስ ረጅም ርቀት መጓዝ የምትችለው ባለህ ችሎታ ላይ ጠንክረህ ስትሰራ ነው። በኔ ግምት ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ከሀገር በመውጣት እና ወደተለያዩ ሀገራት ሄደው በመጫወት ልምድ ማግኘት ከቻሉ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መፍጠር ይቻላል።”

ቤኒናዊው ተጫዋች በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ግማሽ ፍፃሜ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ላይ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ባሳየው የደስታ አገላለፅ ምክንያት የተከሰተውን ሁሉም ሰው ያውቃል፡፡ ሻኪሩ ግን ሆን ብሎ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን ለማበሳጨት ያደረገው እንዳልነበር ይናገራል፡፡

“በካስቴል ዋንጫ በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ግብ ካስቆጠርኩኝ በኋላ ደስታዬን የገለፅኩበት ሁኔታ ሆን ብዬ ያደረግኩት አልነበረም። የእጅ ምልክቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ትርጉም እንዳለው ራሱ አላውቅም። በጥላ ፎቅ የነበሩ ደጋፊዎች ምልክቱን ሲያሳዩ በማየቴ ነው እነርሱን ለማስመሰል የሞከርኩት። ዳኛው በወሰኑት ውሳኔ ግን አልስማማም፤ እኔን ማስጠንቀቅ ፈልገው የነበረ ቢሆን እንኳን ቢጫ ካርድ በቂ ነበረ ይመስለኛል።”

በመጪው እሁድ ሁለቱ ባላንጣዎች በ6ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሲያደርጉ በርካታ ትኩረት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች አንዱ ሻኪሩ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ለደርቢው የተለየ ግምት የሰጠ አይመስልም፡፡

“በኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መሀል ከፍተኛ የተፎካካሪነት ስሜት እንዳለ ተገንዝቤያለሁ። ነገር ግን እንደዚህ ያሉ ከባድ ጨዋታዎች ለኔ አዲስ አይደሉም። ቤኒን እያለሁ በሬክዊን እና ድራገን ክለቦች መሀል በሚደረገው የሀገሪቱ ትልቁ ጨዋታ ላይ በርካታ ግቦችን ማስቆጠር ችያለሁ። በኦማን በነበረኝ ቆይታም የኦማን ክለብ እና ሙስካት ክለብ ፍልሚያ ላይ የሁለቱንም ክለቦች ማሊያ በመልበስ ተሳትፊያለሁ። በትውልድ ሃገሬ ናይጄሪያ ሊግም ቢሆን ሰንሻይን ስታርስ ከሹቲንግ ስታርስ በሚያደርጉት ‘የደቡብ-ምዕራብ ደርቢ’ ተጫውቻለሁ። እንደምታየው ታላቅ ተቀናቃኝ ባላቸው ታላቅ ክለቦች ውስጥ የመጫወት ልምዱ አለኝ።”
ኢትዮጵያ ቡናም ሆነ አጥቂው ሻኪሩ በሲቲ ካፑ ያሳዩትን አቋም በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ላይ ሊደግሙት አልቻሉም፡፡ የመጀመርያዎቹን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ሲሸነፉ ቤኒናዊው ከተጠባባቂ ወንበር ጨዋታዎችን የጀመረባቸው ጨዋታዎች አሉ፡፡ እንደ ሻኪሩ እምነት ግን የውድድር ዘመኑ ለኢትዮጵያ በና የተሳካ አንደሚሆን ነው፡፡
“በሊጉ የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት ከንግድ ባንክ እና ሙገር ሲሚንቶ ጋር ባደረግናቸው ጨዋታዎች ያገኘነው ውጤት ለኛ የሚገባን አልነበረም። በሁለቱም ጨዋታዎች ጥሩ መንቀሳቀስ ችለናል፤ ተጋጣሚዎቻችንንም በኳስ ቁጥጥሩ በልጠናል። ነገር ግን አሸናፊ ሊያደርጉን የሚችሉ ግቦችን ለማስቆጠር አልታደልንም። አንዳንዴ በእግር ኳስ ጥሩ ከመጫወት አልፎ እድለኛ መሆን ግድ ይልሃል። ከነዚህ ጨዋታዎች ብዙ ተምረናል፤ ከዳሽን ቢራ እና አርባምንጭ ከነማ ጋር ያደረግናቸውን ግጥሚያዎች በድል መወጣታችን ለዚህ ግልፅ ማሳያ ነው። የውድድር ዓመቱ ገና መጀመሩ ነው፤ ቀጣይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ እንደምንመለስ እርግጠኛ ነኝ።”

“ኢትዮጵያ ቡናን በተቀላቀልኩበት የመጀመሪያ ውድድር ዘመን ከቡድኑ ጋር አንድ ነገር መስራት እፈልጋለሁ። አሁን ባለን የቡድን ስብስብ የሊጉን ወይንም የጥሎ ማለፉን ዋንጫ እንደምናነሳ አልጠራጠርም። በግሌም ክለቡ ውጤታማ እንዲሆን የተቻለኝን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ።”

ሻኪሩ በመጨረሻም በፍጥነት ኢትዮጵያን እንዲለምድ የረዱት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች መልእከቱን አስተላልፏል፡፡
“አድናቂዎቼ እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ከኔ በርካታ ጎሎች ከቡድኑም መልካም ጨዋታ እንዲጠብቁ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ። ምንጊዜም ቡና!”

ያጋሩ