ቻን | የዋልያዎቹ ተጋጣሚ የወዳጅነት ጨዋታዋን አቋርጣ ወጥታለች

የፊታችን ቅዳሜ በቻን ውድድር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋን የምታደርገው ሞዛምቢክ ከጋና ጋር እያደረገች የነበረችውን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አቋርጣ ወጥታለች።

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት የሚከናወነው 7ኛው የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒየንሺፕ ውድድር ከሁለት ቀናት በፊት በ18 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ይደረጋል። አብዛኞቹ ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ውድድሩ ስፍራ እየገቡ የሚገኝ ሲሆን በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ሞዛምቢክም ከሁሉም ቡድኖች ቀድማ አልጄሪያ ገብታ ዝግጅቷን እያደረገች ትገኛለች። ከቀናት በፊት እዛው አልጄሪያ ከሚገኙ ክለቦች ጋር ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አድርጋ ሽንፈት ያስተናገደችው ሞዛምቢክም ትናንት አመሻሽ ከጋና ጋር የመጨረሻ የአቋም መለኪያ ፍልሚያ ለማድረግ ቀጠሮ እንደያዘች ዘግበን ነበር።

\"\"

ምሽት 12 ሰዓት ላይ በጁላይ 5 1962 ኦሎምፒክ ስታዲየም የተጀመረው ጨዋታ በ39ኛው ደቂቃ በአማዱ አማካኝነት በተቆጠረ ግብ ሞዛምቢክ ግብ አስቆጥራ መሪ በመሆን ፍልሚያው ቢቀጥልም ከ72ኛው ደቂቃ በላይ ግን አልተጓዘም። በተጠቀሰው ደቂቃ የዕለቱ ዳኛ የሞዛምቢክ ተከላካይ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ ተነክቷል በሚል የፍፁም ቅጣት ምት ለጋና ቢሰጡም የሞዛምቢክ ተጫዋቾች እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ተቃውሟቸውን አስምተዋል። ተቃውሞው አይሎም የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ቼኪኒዮ ኮንዴ ተጫዋቾቻቸው ሜዳውን ለቀው እንዲወጡ በማዘዝ ጨዋታው ተቋርጧል። ዳኞች እና በስፍራው የነበሩ የጋና ብሔራዊ ፌዴሬሽን አመራሮች ሞዛምቢኮችን አስማምተው ጨዋታውን እንዲቀጥሉ ለማግባባት ቢጥሩም ሞዛምቢኮች ሀሳባቸው ሳይቀይሩ በውሳኔቸው ፀንተው ቀርተው ጨዋታው በአወዛጋቢ ሁኔታ ተቋርጧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቅዳሜ 10 ሰዓት ከሞዛምቢክ አቻው ጋር የቻን የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል።

\"\"