የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ የረፋድ ውሎ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር \”ዘርፈ ብዙ የግምገማ ጥናት እና የልማት ፍኖተ ካርታ\” በሚል ርዕስ ባስጠናው ጥናት ዙርያ የተዘጋጀው የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ ዛሬ ረፋድ በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል መደረግ ጀምሯል።

ይጀመራል ከተባለበት ሰዓት በተወሰነ መልኩ ዘግይቶ በተጀመረው የውይይት መድረኩ የኢፊድሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ የሆኑት አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዲሁም በኢፊድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጤና እና ማህበራዊ ልማት እና ስፖርት ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሮ ወርቅሰው ማሞ ጨምሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፅህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ባህሩ ጥላሁንን እና ከሁሉም የክልል እግር ኳስ ፌደሬሽኖች እና የፕሪምየር ሊግ ተካፋይ ክለቦች አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።

\"\"

መርሃግብሩን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ክፍሌ ሰይፈ ይህ ቀን ለአክሲዮን ማህበሩ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን እና ለመጪው ዘመን በሀገራችን እግር ኳስ ላይ ለሚሰሩ ስራዎች መነሻ የሚሆን ቁልፍ ሰነድ እንደሆነ ገልፀዋል።

በንግግራቸውም ይህ አንድ ዓመት ከስድስት ወር የፈጀው የጥናት ውጤት ለአክሲዮን ማህበሩ ሆነ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑን ጨምሮ ለሌሎች የእግር ኳሱ ባለ ድርሻ አካላት በቀጣይ እንደ መነሻ የሚሆኑ ምክረ ሀሳብ የቀረቡበት ስለመሆኑ አስረድተዋል።

በማስከተል መድረኩን ተረክበው የመክፈቻ ንግግራቸውን ያሰሙት የአክሲዮን ማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ይህ ጥናት እንደ ሌሎች ጥናቶች ከውይይት በኃላ በመደርደርያ ላይ የሚቀመጥ አለመሆኑን ጠቅሰው ፤ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ሆነ አክሲዮን ማህበሩን ጨምሮ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ለተግባራዊነቱ ተነሳሽነት እንዲያሳዩ ጥሪያቸውን አስተላለፈዋል።

በተጨማሪም በንግግራቸው ከዚህ ጥናት ውይይት በኃላ በፍጥነት ወደ ተግባር የማይገባ ከሆነ እና አሁን እየተጓዝንበት በምንገኘው መንገድ የምንቀል ከሆነ አይደለም በአህጉርአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ክለቦችን መፍጠር ይቅርና የክለቦቻችን ህልውናን እንኳን ለማስቀጠል የመቻላችን ነገር በጣም አሳሳቢ ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።

በመርሃግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ኢፊድሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ የሆኑት አምባሳደር መስፍን ቸርነት ቀጥለው ባደረጉት ንግግር የጥናት ውጤቶች የእግር ኳሱን መሰረታዊ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ እግር ኳሱን በማዘመን ረገድ ስለሚኖራቸው ትልቅ ሚና አውስተው መሰል ጥናቶች መበራከት ይገባቸዋል ሲሉም ገልፀዋል።ንግግራቸውንም ሲቋጩ ለ3ኛ ጊዜ በቻን አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ወደ አልጀርያ ያቀናው ብሔራዊ ቡድናችን መልካም ምኞታቸውንም በመግለፅ ነበር።

በመጨረሻም መርሃግብሩ ወደ ሻይ ዕረፍት ከማምራቱ አስቀድሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና ፀሀፊ የሆኑ አቶ ባህሩ ጥላሁን ባደረጉት አጭር ንግግር ለአክሲዮን ማህበሩ ለረጅም ጊዜ የለፉበት ጥናት እዚህ ደርሶ በማየታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትም ይህን ፈለግ መከተል እንደሚገባቸው ገልፀዋል።በመጨረሻም ጥናቱ በተለይ በአክሲዮን ማህበሩ እና በፌደሬሽኑ መሃል ስለሚኖረው የሚና ልዮነት እና ግንኙነት ግልፅ ሀሳብ ይኖረዋል የሚል እምነት አንዳላቸውምገልፀዋል።

መርሃግብሩ ከሻይ ዕረፍት ሲመለስ ጥናቱን ያከናወነው ፊት ኮርነር አማካሪ ድርጅት ቡድን መሪ የሆኑት እና በስፖርት እና ቢዝነስ ማማከር እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በታውንሰንድ ዩኒቨርስቲ በማስተማር ላይ የሚገኙት አቶ ጋሻው አብዛ በጥናቱ ዙርያ ጥቅል ገለፃን አድርገዋል። በዚህም የጥናቱ መነሻ ሀሳቦች ፣ ዝርዝር ዓላማዎችን እና የምርምር ዘዴዎችን ጨምሮ ሌሎች በጥናቱ ላይ ወሳኝ ናቸው ያሏቸው ጉዳዮችን አብራርተዋል።

\"\"

በማብራሪያቸውም ጥናቱ በመነሻነት በአክሲዮን ማህበሩ በኩል ለአጥኚው ቡድን በቀረቡ አምስት መሰረታዊ ዓላማዎችን መነሻ በማድረግ ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች ላይ ብቻ የተደረገው ስለመሆኑ ገልፀው በጥናቱ በአጠቃላይ 90 ከሚሆኑ የእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት ጋር ከአንድ ሰዓት በላይ በተደረጉ ቃለመጠይቆች እና ሰነዶች ላይ በተሰበሰቡ መረጃ እና ማስረጃዎች መሰረት የቀረበ መሆኑን ገልፀው የጥናት ውጤቱ 400 ገፆች ያሉት መሆኑን እና በጥናቱም መሰረት 46 ምክረ ሃሳቦች እና 6 አማራጭ መንገዶች የቀረቡበት ስለመሆኑ አጥኚው አቶ ጋሻው አብዛ ተናግረዋል።

በማስቀጠል ጥቅል ሀሳቦች ዙርያ ከተሳታፊዎች ሀሳብ እና አስተያየቶች ከተሰጡ በኃላ ውይይቱ ለምሳ እረፍት ተብትኗል።